ኢሳይያስ 47:1-15

  • የባቢሎን መውደቅ (1-15)

    • ኮከብ ቆጣሪዎች ተጋለጡ (13-15)

47  አንቺ ድንግል የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፣+ወርደሽ አፈር ላይ ተቀመጪ። አንቺ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፣ዙፋን በሌለበት መሬት ላይ ተቀመጪ፤+ከእንግዲህ ሰዎች ቅምጥልና ሞልቃቃ ብለው አይጠሩሽምና።   ወፍጮ ወስደሽ እህል ፍጪ። መሸፋፈኛሽን አንሺ። ቀሚስሽን አውልቂ፤ ባትሽን ግለጪ። ወንዞቹን ተሻገሪ።   እርቃንሽ ይገለጣል። ኀፍረትሽም ይታያል። እኔ የበቀል እርምጃ እወስዳለሁ፤+ ማንም ሰው ሊያግደኝ አይችልም።*   “እኛን የሚቤዠንየእስራኤል ቅዱስ ነው፤+ስሙም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው።”   አንቺ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፣በዚያ ዝም ብለሽ ተቀመጪ፤ ወደ ጨለማም ግቢ፤+ከእንግዲህ የመንግሥታት እመቤት* ብለው አይጠሩሽም።+   ሕዝቤን ተቆጣሁ።+ ርስቴን አረከስኩ፤+አሳልፌም በእጅሽ ሰጠኋቸው።+ አንቺ ግን ምሕረት አላሳየሻቸውም።+ በሽማግሌው ላይ እንኳ ሳይቀር ከባድ ቀንበር ጫንሽ።+   አንቺም “ሁልጊዜ ብሎም ለዘላለም እመቤት* እሆናለሁ” አልሽ።+ እነዚህን ነገሮች ልብ አላልሽም፤ነገሩ ምን ፍጻሜ እንደሚኖረው አላሰብሽም።   በመሆኑም አንቺ ለሥጋዊ ደስታ ያደርሽ፣+ተማምነሽ የተቀመጥሽና በልብሽ “እኔ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።+ መበለት አልሆንም። በምንም ዓይነት የወላድ መሃን አልሆንም” የምትዪ ሴት ሆይ፣+ ይህን ስሚ።   ሆኖም እነዚህ ሁለት ነገሮች ይኸውም የወላድ መሃንነትና መበለትነት በአንድ ቀን በድንገት ይደርሱብሻል።+ በመተት ስለተሞላሽና ታላቅ ኃይል ባለው ድግምት ስለተዘፈቅሽ*+እነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንቺ ላይ ይደርሳሉ።+ 10  አንቺ በክፋትሽ ታምነሻል። “ማንም አያየኝም” ብለሻል። ያሳቱሽ ጥበብሽና እውቀትሽ ናቸው፤በልብሽም “እኔ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም” ትያለሽ። 11  ሆኖም ጥፋት ይመጣብሻል፤ደግሞም ከዚህ ሊያስጥልሽ የሚችል ድግምት የለሽም።* መከራ ይደርስብሻል፤ ልታስወግጂውም አትችዪም። አይተሽው የማታውቂው ጥፋት በድንገት ይደርስብሻል።+ 12  እንግዲያው ከልጅነትሽ ጀምሮ ስትደክሚበት የነበረውንድግምት ሁሉና ብዛት ያለው የጥንቆላ ድርጊት+ መፈጸምሽን ቀጥዪ። ምናልባት ይጠቅምሽ ይሆናል፤ሰዎችን ለማሸበር ይረዳሽ ይሆናል። 13  በመካሪዎችሽ ብዛት እጅግ ተዳክመሻል። በሰማያት ያሉ ነገሮችን የሚያመልኩ፣* ከዋክብትን በትኩረት የሚመለከቱ፣+አዲስ ጨረቃም ስትወጣበአንቺ ላይ ስለሚመጣው ነገር የሚተነብዩ ሰዎች፣እስቲ አሁን ተነስተው ያድኑሽ። 14  እነሆ፣ እነሱ እንደ ገለባ ናቸው። እሳት ያቃጥላቸዋል። ራሳቸውን* ከነበልባሉ ኃይል ማዳን አይችሉም። ይህ ሰዎች የሚሞቁት ፍምም ሆነበፊቱ ተቀምጠው የሚሞቁት እሳት አይደለም። 15  ከልጅነትሽ ጀምሮ አብረሻቸው ስትደክሚ የነበሩትድግምተኞች እንዲሁ ይሆኑብሻል። እያንዳንዳቸው የመረጡትን አቅጣጫ ተከትለው ይባዝናሉ።* አንቺን የሚያድን አይኖርም።+

የግርጌ ማስታወሻ

“ለማንም አልራራም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ንግሥት።”
ወይም “ንግሥት።”
“መተት ብታበዢና ታላቅ ኃይል ያለው ድግምት ብትደግሚም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በድግምት እንዴት እንደምታርቂውም አታውቂም።”
“ሰማያትን የሚከፋፍሉ፤ ኮከብ ቆጣሪዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሳቸውን።”
ቃል በቃል “ወደየአካባቢያቸው ለመመለስ ይባዝናሉ።”