ኢሳይያስ 49:1-26

  • ለይሖዋ አገልጋይ የተሰጠ ሥራ (1-12)

    • “ለብሔራት ብርሃን” (6)

  • ለእስራኤል የተነገረ ማጽናኛ (13-26)

49  እናንተ ደሴቶች ስሙኝ፤እናንተም በሩቅ ያላችሁ ብሔራት+ በጥሞና አዳምጡ። ይሖዋ ከመወለዴ በፊት* ጠርቶኛል።+ በእናቴ ማህፀን ከነበርኩበት ጊዜ አንስቶ ስሜን ጠርቷል።   አፌን እንደተሳለ ሰይፍ አደረገው፤በእጁ ጥላ ሥር ሰወረኝ።+ የሾለ ፍላጻ አደረገኝ፤በኮሮጆው ውስጥ ሸሸገኝ።   እሱም “እስራኤል ሆይ፣ አንተ ግርማዬን የምገልጥብህ+አገልጋዬ ነህ”+ አለኝ።   እኔ ግን “የደከምኩት በከንቱ ነው። ጉልበቴንም ያፈሰስኩት ከንቱ ለሆነና ምንም ፋይዳ ለሌለው ነገር ነው። ሆኖም የሚዳኘኝ ይሖዋ ነው፤*ደሞዜንም* የሚከፍለኝ አምላኬ ነው”+ አልኩ።   የእሱ አገልጋይ እንድሆን ከማህፀን ጀምሮ የሠራኝ ይሖዋ፣እስራኤል ወደ እሱ ይሰበሰብ ዘንድያዕቆብን ወደ እሱ እንድመልስ አዞኛል።+ በይሖዋ ፊት እከብራለሁ፤አምላኬም ብርታቴ ይሆናል።   እንዲህም አለ፦ “የያዕቆብን ነገዶች ዳግመኛ ለማቋቋምናጥበቃ ያገኙትን እስራኤላውያን መልሰህ ለማምጣትአገልጋዬ መሆንህ በቂ አይደለም። የማዳን ሥራዬ እስከ ምድር ዳርቻ ይደርስ ዘንድ+ለብሔራት ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ።”+  እስራኤልን የሚቤዠው፣ የእስራኤል ቅዱስ የሆነው ይሖዋ፣+ እጅግ ለተናቀውና*+ በሕዝብ ለተጠላው የገዢዎች አገልጋይ እንዲህ ይላል፦ “ታማኝ በሆነው በይሖዋ፣+አንተንም በመረጠህ+ በእስራኤል ቅዱስ የተነሳነገሥታት አይተው ይነሳሉ፤መኳንንትም ይሰግዳሉ።”   ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሞገስ* በማሳይበት ዘመን መልስ ሰጥቼሃለሁ፤+በመዳንም ቀን ረድቼሃለሁ፤+ለሰዎች ቃል ኪዳን አድርጌ እሰጥህ ዘንድ ጠብቄሃለሁ፤+ይህም ምድሪቱን ዳግመኛ እንድታቋቁም፣የወደመውን ርስታቸውን መልሰህ እንድታወርሳቸው፣+   እስረኞቹን ‘ኑ ውጡ!’+ በጨለማ ያሉትንም+ ‘ራሳችሁን ግለጡ!’ እንድትል ነው። በየመንገዱ ዳር ይመገባሉ፤በተበላሹ መንገዶችም* ሁሉ አጠገብ መሰማሪያ ያገኛሉ። 10  አይራቡም፤ አይጠሙም፤+ሐሩርም ሆነ ፀሐይ አያቃጥላቸውም።+ ምሕረት የሚያደርግላቸው ይመራቸዋልና፤+የውኃ ምንጮች ወዳሉበትም ይወስዳቸዋል።+ 11  ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤አውራ ጎዳናዎቼም ከፍ ያሉ ይሆናሉ።+ 12  እነሆ፣ እነዚህ ከሩቅ ይመጣሉ፤+እነሆም፣ እነዚህ ከሰሜንና ከምዕራብ፣እነዚህ ደግሞ ከሲኒም ምድር ይመጣሉ።”+ 13  እናንተ ሰማያት፣ እልል በሉ፤ አንቺም ምድር፣ ሐሴት አድርጊ።+ ተራሮች በደስታ እልል ይበሉ።+ ይሖዋ ሕዝቡን አጽናንቷልና፤+ለተጎሳቆሉት ሕዝቦቹም ምሕረት ያሳያል።+ 14  ጽዮን ግን “ይሖዋ ትቶኛል፤+ ይሖዋም ረስቶኛል”+ ትላለች። 15  እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለች?ከማህፀኗ ለወጣውስ ልጅ አትራራም? እነዚህ ሴቶች ቢረሱ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም።+ 16  እነሆ፣ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ። ግንቦችሽ ምንጊዜም በፊቴ ናቸው። 17  ወንዶች ልጆችሽ ፈጥነው ይመለሳሉ። ያፈራረሱሽና ያወደሙሽ አንቺን ለቀው ይሄዳሉ። 18  ዓይንሽን አንስተሽ ዙሪያሽን ተመልከቺ። ሁሉም በአንድነት እየተሰበሰቡ ነው።+ ወደ አንቺም እየመጡ ነው። “በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል ይሖዋ፣“አንቺም ሁሉንም እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤እንደ ሙሽራም ትጎናጸፊያቸዋለሽ። 19  ስፍራዎችሽ ባድማና ወና፣ ምድርሽም የወደመ ቢሆንም+አሁን በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ቦታው በጣም ይጠባቸዋል፤+የዋጡሽም+ ከአንቺ ይርቃሉ።+ 20  የወላድ መሃን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱት ወንዶች ልጆች፣ጆሮሽ እየሰማ ‘ይህ ቦታ በጣም ጠቦናል። የምንኖርበት በቂ ስፍራ ስጪን’ ይላሉ።+ 21  አንቺም በልብሽ እንዲህ ትያለሽ፦‘እኔ ልጆቼን በሞት ያጣሁና መሃንእንዲሁም በምርኮ የተወሰድኩና እስረኛ የሆንኩ ሴት ሆኜ ሳለእነዚህን ልጆች የወለደልኝ ማን ነው? ያሳደጋቸውስ ማን ነው?+ እነሆ፣ እኔ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤+ታዲያ እነዚህ ከየት መጡ?’”+ 22  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ እጄን ለብሔራት አነሳለሁ፤ምልክቴንም * ለሕዝቦች ከፍ አደርጋለሁ።+ ወንዶች ልጆችሽን በክንዳቸው* ይዘው ያመጧቸዋል፤ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ይሸከሟቸዋል።+ 23  ነገሥታት ይንከባከቡሻል፤+ልዕልቶቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ። በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤+የእግርሽንም አቧራ ይልሳሉ፤+አንቺም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቂያለሽ፤እኔን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም።”+ 24  በምርኮ የተያዙ ሰዎች ከኃያል ሰው እጅ ሊወሰዱ ይችላሉ?ወይስ በጨቋኝ እጅ የወደቁ ምርኮኞችን የሚታደጋቸው ይኖራል? 25  ይሖዋ ግን እንዲህ ይላል፦ “በኃያል ሰው የተማረኩ ሰዎችም እንኳ ከእጁ ላይ ይወሰዳሉ፤+በጨቋኝ እጅ የወደቁ ሰዎችንም የሚታደጋቸው ይኖራል።+ አንቺን የሚቃወሙትን እቃወማለሁ፤+ወንዶች ልጆችሽንም አድናቸዋለሁ። 26  በደል የሚፈጽሙብሽን የገዛ ሥጋቸውን እንዲበሉ አደርጋቸዋለሁ፤ልክ እንደ ጣፋጭ ወይን ጠጅ የገዛ ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ። ሰውም* ሁሉ እኔ ይሖዋአዳኝሽና+ የምቤዥሽ፣+የያዕቆብም ኃያል አምላክ እንደሆንኩ ያውቃል።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ከማህፀን ጀምሮ።”
ወይም “ሆኖም ይሖዋ ፍትሕ ያሰፍንልኛል።”
ወይም “ወሮታዬንም።”
ወይም “በነፍስ ለተናቀውና።”
ወይም “በጎ ፈቃድ።”
“በተራቆቱ ኮረብቶችም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶዬንም።”
ቃል በቃል “በእቅፋቸው።”
ቃል በቃል “ሥጋም።”