ኢሳይያስ 51:1-23

  • ጽዮን ተመልሳ እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ ትሆናለች (1-8)

  • ጽዮንን የሠራው ኃያል አምላክ የተናገረው ማጽናኛ (9-16)

  • የይሖዋ የቁጣ ጽዋ (17-23)

51  “እናንተ ጽድቅን የምትከታተሉ፣ይሖዋንም የምትፈልጉ ስሙኝ። ተፈልፍላችሁ የወጣችሁበትን ዓለት፣ተቆፍራችሁ የወጣችሁበትንም ካባ ተመልከቱ።   አባታችሁን አብርሃምን፣የወለደቻችሁንም* ሣራን+ ተመልከቱ። እሱ በጠራሁት ጊዜ ብቻውን ነበርና፤+እኔም ባረክሁት፤ ደግሞም አበዛሁት።+   ይሖዋ ጽዮንን ያጽናናታልና።+ ፍርስራሾቿን ሁሉ ያጽናናል፤+ምድረ በዳዋንም እንደ ኤደን፣+በረሃማ ሜዳዋንም እንደ ይሖዋ የአትክልት ስፍራ ያደርጋል።+ በእሷም ውስጥ ሐሴትና ታላቅ ደስታእንዲሁም ምስጋናና ደስ የሚያሰኝ መዝሙር ይገኛሉ።+   ሕዝቤ ሆይ፣ በጥሞና አዳምጡኝ፤አንተም የእኔ ብሔር፣ ጆሮህን ስጠኝ።+ ሕግ ከእኔ ይወጣልና፤+የፍትሕ እርምጃዬም ለሕዝቦች እንደ ብርሃን ጸንቶ እንዲቆም አደርጋለሁ።+   ጽድቄ ቀርቧል።+ ማዳኔ ወደ እናንተ ይመጣል፤+ክንዴም በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል።+ ደሴቶች በእኔ ተስፋ ያደርጋሉ፤+ክንዴንም* ይጠባበቃሉ።   ዓይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሱ፤ወደታችም ወደ ምድር ተመልከቱ። ሰማያት እንደ ጭስ በነው ይጠፋሉና፤ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፤ነዋሪዎቿም እንደ ትንኝ ይረግፋሉ። ማዳኔ ግን ለዘላለም ይኖራል፤+ጽድቄም ፈጽሞ አይከስምም።*+   እናንተ ጽድቅን የምታውቁ፣ሕጌንም* በልባችሁ ያኖራችሁ ሰዎች፣+ ስሙኝ። ሟች የሆኑ ሰዎች የሚሰነዝሩትን ትችት አትፍሩ፤ስድባቸውም አያሸብራችሁ።   ብል እንደ ልብስ ይበላቸዋልና፤የልብስ ብል* እንደ ሱፍ ጨርቅ ይበላቸዋል።+ ሆኖም ጽድቄ ለዘላለም፣ማዳኔም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።”+   የይሖዋ ክንድ ሆይ፣+ተነስ! ተነስ! ብርታትንም ልበስ! ከረጅም ጊዜ በፊት፣ በጥንቶቹ ትውልዶች ዘመን እንደሆነው ተነስ። ረዓብን*+ ያደቀከው፣ግዙፉንም የባሕር ፍጥረት የወጋኸው አንተ አይደለህም?+ 10  ባሕሩን፣ የተንጣለለውን የጥልቁን ውኃ ያደረቅከው አንተ አይደለህም?+ የተቤዠሃቸው ሰዎች እንዲሻገሩ ጥልቁን ባሕር መንገድ ያደረግከው አንተ አይደለህም?+ 11  ይሖዋ የዋጃቸው ይመለሳሉ።+ በእልልታ ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤+ማብቂያ የሌለውንም ደስታ እንደ አክሊል ይጎናጸፋሉ።+ ሐሴት ያደርጋሉ፤ ታላቅ ደስታም ያገኛሉ፤ሐዘንና ሲቃም ከእነሱ ይሸሻሉ።+ 12  “የማጽናናችሁ እኔ ራሴ ነኝ።+ ሟች የሆነውን ሰው፣እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ የምትፈሪው ለምንድን ነው?+ 13  ሰማያትን የዘረጋውንና+ የምድርን መሠረት የጣለውንሠሪህን ይሖዋን+ የምትረሳው ለምንድን ነው? ደግሞም ጨቋኙ* ሊያጠፋህ የተዘጋጀ ይመስልከእሱ ቁጣ የተነሳ ቀኑን ሙሉ በፍርሃት ተውጠህ ነበር። ታዲያ አሁን የጨቋኙ ቁጣ የት አለ? 14  በሰንሰለት ታስሮ ያጎነበሰው እስረኛ ቶሎ ይፈታል፤+ሞትን አያይም፤ ወደ ጉድጓድም አይወርድም፤የሚበላውም ነገር አያጣም። 15  ባሕሩን የማናውጥና ኃይለኛ ማዕበል የማስነሳ፣+እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ፤ስሙ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው።+ 16  ሰማያትን እዘረጋና የምድርን መሠረት እጥል ዘንድ፣+ጽዮንንም ‘አንቺ ሕዝቤ ነሽ’+ እል ዘንድቃሌን በአፍህ አኖራለሁ፤በእጄም ጥላ እጋርድሃለሁ።+ 17  ከይሖዋ እጅ የቁጣውን ጽዋ የጠጣሽኢየሩሳሌም ሆይ፣ ተነሺ! ተነሺ! ቁሚ።+ ዋንጫውን ጠጥተሻል፤የሚያንገዳግደውን ጽዋ ጨልጠሻል።+ 18  ከወለደቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ መካከል አንድም የሚመራት የለም፤ካሳደገቻቸውም ወንዶች ልጆች ሁሉ መካከል እጇን ይዞ የወሰዳት ማንም የለም። 19  እነዚህ ሁለት ነገሮች ደርሰውብሻል። ማን ያስተዛዝንሻል? ጥፋትና ውድመት እንዲሁም ረሃብና ሰይፍ መጥቶብሻል!+ ማንስ ያጽናናሻል?+ 20  ወንዶች ልጆችሽ ራሳቸውን ስተዋል።+ በመረብ እንደተያዘ የዱር በግበየመንገዱ ማዕዘን ላይ* ይተኛሉ። የይሖዋ ቁጣ፣ የአምላክሽም ተግሣጽ ሙሉ በሙሉ ወርዶባቸዋል።” 21  ስለዚህ አንቺ የተጎሳቆልሽና ያለወይን ጠጅ የሰከርሽ ሴት ሆይ፣እባክሽ ይህን ስሚ። 22  ለሕዝቡ የሚሟገተው ጌታሽና አምላክሽ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ የሚያንገዳግደውን ጽዋ፣+ ይኸውም ዋንጫውን፣የቁጣዬን ጽዋ ከእጅሽ እወስዳለሁ፤ከእንግዲህ ዳግመኛ አትጠጪም።+ 23  ጽዋውን ‘በላይሽ ላይ እንድንሻገር አጎንብሺልን!’ ባሉሽ፣*አንቺን በሚያሠቃዩት እጅ ላይ አደርገዋለሁ፤+ አንቺም ጀርባሽን እንደ መሬት፣እንደሚሄዱበትም መንገድ አደረግሽላቸው።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “አምጣ የወለደቻችሁንም።”
ወይም “ኃይሌንም።”
ወይም “አይንኮታኮትም።”
ወይም “መመሪያዬንም፤ ትምህርቴንም።”
“ትል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “እንዳትንቀሳቀስ ያገደህ።”
ቃል በቃል “በመንገዶቹ ሁሉ ራስ ላይ።”
ወይም “ነፍስሽን ‘በላይሽ ላይ እንድንሻገር አጎንብሺልን!’ ባሏት።”