ኢሳይያስ 53:1-12

  • የይሖዋ አገልጋይ የደረሰበት ሥቃይ፣ አሟሟቱና የተቀበረበት ሁኔታ (1-12)

    • ሰዎች ናቁት፤ ደግሞም አገለሉት (3)

    • ሕመማችንንና ሥቃያችንን ተሸከመ (4)

    • “እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ” (7)

    • የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ (12)

53  ከእኛ የሰማውን* ነገር ያመነ ማን ነው?+ የይሖዋስ ክንድ+ ለማን ተገለጠ?+   እሱ በፊቱ* እንደ ቅርንጫፍ፣+ በደረቅ ምድር እንዳለ ሥር ይበቅላል። የሚያምር ቁመናም ሆነ ግርማ ሞገስ የለውም፤+ባየነውም ጊዜ መልኩ አልሳበንም።*   ሰዎች የናቁትና ያገለሉት፣+ሥቃይን ያየ፣* ሕመምንም የሚያውቅ ሰው ነበር። ፊቱ የተሰወረብን ያህል ነበር።* ሰዎች ናቁት፤ እኛም ከቁብ አልቆጠርነውም።+   በእርግጥም እሱ ራሱ ሕመማችንን ተሸከመ፤+ሥቃያችንንም ተቀበለ።+ እኛ ግን እንደተቀሰፈ፣ በአምላክ እንደተመታና እንደተጎሳቆለ አድርገን ቆጠርነው።   እሱ ግን ስለ መተላለፋችን+ ተወጋ፤+ስለ በደላችን ደቀቀ።+ በእሱ ላይ የደረሰው ቅጣት ለእኛ ሰላም አስገኘልን፤+በእሱም ቁስል የተነሳ እኛ ተፈወስን።+   ሁላችንም እንደ በጎች ተቅበዘበዝን፤+እያንዳንዳችን በየራሳችን መንገድ ሄድን፤ይሖዋም የሁላችንንም በደል እሱ እንዲሸከም አደረገ።+   ግፍ ተፈጸመበት፤+ መከራም ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነ፤+ነገር ግን አፉን አልከፈተም። እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤+በሸላቾቿ ፊት ዝም እንደምትል በግ፣እሱም አፉን አልከፈተም።+   ፍትሕ ተነፈገ፤* በአግባቡም ሳይዳኝ ተወሰደ፤ትኩረት ሰጥቶ ትውልዱን በዝርዝር ለማወቅ* የሚሞክር ማን ነው? ከሕያዋን ምድር ተወግዷልና፤+በሕዝቤ መተላለፍ የተነሳ ተመታ።*+   ምንም ዓይነት በደል* አልፈጸመም፤እንዲሁም ከአንደበቱ የማታለያ ቃል አልወጣም፤+ሆኖም በሚሞትበት ጊዜ የመቃብር ቦታውከክፉዎችና+ ከሀብታሞች*+ ጋር ይሆናል።* 10  ይሁንና እሱን ማድቀቅ የይሖዋ ፈቃድ ነበር፤* ለሕመም እንዲዳረግም ፈቅዷል። ሕይወቱን* የበደል መባ አድርገህ የምታቀርበው ከሆነ+ዘሩን ያያል፤ ዘመኑን ያስረዝማል፤+እንዲሁም በእሱ አማካኝነት ይሖዋ ደስ የሚሰኝበት ነገር* ይከናወናል።+ 11  በእሱ ላይ ከደረሰው ሥቃይ* የተነሳ፣ በሚያየው መልካም ነገር ይደሰታል። ጻድቅ አገልጋዬ+ በእውቀቱ አማካኝነትብዙ ሰዎች ጻድቅ ሆነው እንዲቆጠሩ ይረዳል፤+በደላቸውንም ይሸከማል።+ 12  ስለዚህ ከብዙዎች ጋር ድርሻውን እሰጠዋለሁ፤ምርኮውን ከኃያላን ጋር ይካፈላል፤ሕይወቱን* እስከ ሞት ድረስ አፍስሷልና፤+ከሕግ ተላላፊዎችም ጋር ተቆጥሯል፤+የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸክሟል፤+ስለ ሕግ ተላላፊዎችም ማልዷል።+

የግርጌ ማስታወሻ

“እኛ የሰማነውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“በፊቱ” የሚለው ቃል፣ ማንኛውንም ተመልካች ወይም አምላክን ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “እሱን እንድንፈልግ የሚያደርግ የተለየ መልክ አልነበረውም።”
ወይም “ሥቃይን የሚረዳ።”
“ሰዎች ፊታቸውን የሚያዞሩበት ዓይነት ሰው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ተገደለ።”
ወይም “ስለ አኗኗሩ በዝርዝር ለማወቅ።”
ወይም “ተጨቆነ።”
ወይም “ግፍ።”
ቃል በቃል “ከሀብታም ሰው።”
ወይም “በሚሞትበት ጊዜ ከክፉዎችና ከሀብታሞች ጋር እንዲሆን አንድ ሰው መቃብሩን ይሰጣል።”
ወይም “ይሁንና ይሖዋ እሱን በማድቀቅ ደስ ተሰኝቷል።”
ወይም “የይሖዋ ፈቃድ።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “በነፍሱ ላይ ከደረሰው ችግር።”
ወይም “ነፍሱን።”