ኢሳይያስ 55:1-13

  • በነፃ እንዲበሉና እንዲጠጡ የቀረበ ግብዣ (1-5)

  • ይሖዋንና አስተማማኝ የሆነውን ቃሉን ፈልጉ (6-13)

    • የአምላክ መንገድ ከሰው መንገድ ከፍ ያለ ነው (8, 9)

    • የአምላክ ቃል መፈጸሙ የተረጋገጠ ነው (10, 11)

55  እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ+ ኑ፤ ወደ ውኃው ኑ!+ እናንተ ገንዘብ የሌላችሁ ኑና ገዝታችሁ ብሉ! አዎ፣ ኑና ያለገንዘብ፣ ያለዋጋም የወይን ጠጅና ወተት+ ግዙ።+   ምግብ ላልሆነ ነገር ለምን ገንዘባችሁን ታወጣላችሁ?እርካታ ለማያስገኝ ነገርስ ለምን ገቢያችሁን* ታባክናላችሁ? እኔን በጥሞና አዳምጡ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤+ምርጥ ምግብ በመብላትም* ሐሴት ታደርጋላችሁ።*+   ጆሯችሁን አዘንብሉ፤ ወደ እኔም ኑ።+ አዳምጡ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤*ለዳዊት ካሳየሁት የማይከስም * ታማኝ ፍቅር+ ጋር በሚስማማ ሁኔታከእናንተ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ።+   እነሆ፣ ለብሔራት ምሥክር፣+መሪና+ አዛዥ+ አድርጌዋለሁ።   እነሆ፣ የማታውቀውን ብሔር ትጠራለህ፤የማያውቅህ ብሔርም ለአምላክህ ለይሖዋና ለእስራኤል ቅዱስ ሲልወደ አንተ ሮጦ ይመጣል፤+ምክንያቱም እሱ ክብር ያጎናጽፍሃል።+   ይሖዋን በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት።+ በቅርብም ሳለ ጥሩት።+   ክፉ ሰው መንገዱን፣መጥፎ ሰውም ሐሳቡን ይተው፤+ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ፤+ይቅርታው ብዙ ነውና።*+   “ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና”+ ይላል ይሖዋ።   “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉመንገዴ ከመንገዳችሁ፣ሐሳቤም ከሐሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።+ 10  ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣ምድርን በማራስ እንድታበቅልና እንድታፈራ፣ለዘሪው ዘርን፣ ለበላተኛውም ምግብን እንድትሰጥ ሳያደርግ ወደመጣበት እንደማይመለስ ሁሉ፣ 11  ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ እንዲሁ ይሆናል።+ ደስ የሚያሰኘኝን ነገር* ያደርጋል፣+የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል እንጂያላንዳች ውጤት ወደ እኔ አይመለስም።+ 12  በታላቅ ደስታ ትወጣላችሁና፤+በሰላምም ትመለሳላችሁ።+ ተራሮቹና ኮረብቶቹ በደስታ በፊታችሁ እልል ይላሉ፤+የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ።+ 13  በቁጥቋጦ ፋንታ የጥድ ዛፍ ይበቅላል፤+በሳማም ፋንታ የአደስ ዛፍ ይበቅላል። የይሖዋ ስም እንዲገን ያደርጋል፤*+እንዲሁም ፈጽሞ የማይጠፋ የዘላለም ምልክት ይሆናል።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በብዙ ድካም ያገኛችሁትን ገንዘብ።”
ቃል በቃል “በስብ።”
ወይም “ነፍሳችሁም ምርጥ ምግብ በመብላት ሐሴት ታደርጋለች።”
ወይም “ነፍሳችሁም በሕይወት ትኖራለች።”
ወይም “እምነት የሚጣልበት፤ አስተማማኝ የሆነ።”
ወይም “በነፃ ይቅር ይላልና።”
ወይም “ፈቃዴን።”
ወይም “የይሖዋን ስም ያስጠራል።”