ኢሳይያስ 66:1-24
66 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
“ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድር ደግሞ የእግሬ ማሳረፊያ ናት።+
ታዲያ እናንተ ምን ዓይነት ቤት ልትሠሩልኝ ትችላላችሁ?+
ደግሞስ የማርፍበት ቦታ የት ነው?”+
2 “እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሠራው እጄ ነው፤ሁሉም ወደ ሕልውና የመጡት በዚህ መንገድ ነው” ይላል ይሖዋ።+
“እኔ የማየው ትሑት የሆነውን፣መንፈሱ የተሰበረውንና በቃሌ የሚንቀጠቀጠውን* ሰው ነው።+
3 በሬን የሚያርድ፣ ሰውን እንደሚገድል ነው።+
በግን የሚሠዋ፣ የውሻን አንገት እንደሚሰብር ነው።+
ስጦታ የሚሰጥ ሰው፣ የአሳማ ደም እንደሚያቀርብ ነው!+
ነጭ ዕጣንን የመታሰቢያ መባ አድርጎ የሚያቀርብ፣+ በአስማታዊ ቃላት እንደሚባርክ* ሰው ነው።+
እነሱ የራሳቸውን መንገድ መርጠዋል፤በአስጸያፊ ነገሮችም ደስ ይሰኛሉ።*
4 ስለዚህ እነሱን የምቀጣበትን መንገድ እፈልጋለሁ፤+የፈሩትንም ያንኑ ነገር አመጣባቸዋለሁ።
ምክንያቱም ስጣራ መልስ የሰጠ ማንም አልነበረም፤ስናገር የሰማ አንድም ሰው አልነበረም።+
በዓይኔ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ማድረጋቸውን ቀጠሉ፤እኔ የማልደሰትበትንም ነገር መረጡ።”+
5 እናንተ በቃሉ የምትንቀጠቀጡ* ሰዎች ሆይ፣ የይሖዋን ቃል ስሙ፦
“በስሜ የተነሳ የሚጠሏችሁና የሚያገሏችሁ ወንድሞቻችሁ፣ ‘ይሖዋ የተከበረ ይሁን!’ ብለዋል።+
ሆኖም አምላክ ይገለጣል፤ ደስታንም ያጎናጽፋችኋል፤እነሱም ለኀፍረት ይዳረጋሉ።”+
6 ከከተማዋ ሁካታ፣ ከቤተ መቅደሱም ድምፅ ይሰማል!
ይህም ይሖዋ ለጠላቶቹ የሚገባቸውን ብድራት በሚከፍላቸው ጊዜ የሚሰማ ድምፅ ነው።
7 እሷ ገና ምጥ ሳይጀምራት ወለደች።+
ምጥ ሳይዛት በፊት ወንድ ልጅ ተገላገለች።
8 እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶ ያውቃል?
እንዲህ ያሉ ነገሮችስ ማን አይቶ ያውቃል?
አገር በአንድ ቀን ይወለዳል?
ወይስ ብሔር በአንድ ጊዜ ይወለዳል?
ሆኖም ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ወንዶች ልጆቿን ወልዳለች።
9 “ማህፀኑን ከከፈትኩ በኋላ ልጁ እንዳይወለድ አደርጋለሁ?” ይላል ይሖዋ።
“ወይስ ምጡ እንዲፋፋም ካደረግኩ በኋላ ማህፀኑን እዘጋለሁ?” ይላል አምላክሽ።
10 እናንተ የምትወዷት ሁሉ፣+ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሴት አድርጉ፤ ከእሷም ጋር ደስ ይበላችሁ።+
ለእሷ የምታዝኑ ሁሉ ከእሷ ጋር እጅግ ደስ ይበላችሁ፤
11 የሚያጽናኑ ጡቶቿን ትጠባላችሁና፤ ሙሉ በሙሉም ትረካላችሁ፤እስኪበቃችሁም ድረስ ትጠጣላችሁ፤ በክብሯም ብዛት ሐሴት ታደርጋላችሁ።
12 ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦
“እነሆ፣ ሰላምን እንደ ወንዝ፣+የብሔራትንም ክብር እንደሚያጥለቀልቅ ጅረት አፈስላታለሁ።+
እናንተም ትጠባላችሁ፤ ጀርባዋም ላይ ታዝላችኋለች፣ጭኗም ላይ ሆናችሁ ትዘላላችሁ።
13 እናት ልጇን እንደምታጽናና፣እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ፤+በኢየሩሳሌምም ትጽናናላችሁ።+
14 እናንተ ይህን ታያላችሁ፤ ልባችሁም ሐሴት ያደርጋል፤አጥንቶቻችሁ እንደ ሣር ይለመልማሉ።
የይሖዋም እጅ* በአገልጋዮቹ ዘንድ ትታወቃለች፤ጠላቶቹን ግን ያወግዛቸዋል።”+
15 “ይሖዋ፣ ብድራቱን በታላቅ ቁጣ ለመመለስ፣በእሳት ነበልባልም ለመገሠጽ+እንደ እሳት ሆኖ ይመጣልና፤+ሠረገሎቹም እንደ አውሎ ነፋስ ይመጣሉ።+
16 ይሖዋ በእሳት ፍርዱን ይፈጽማልና፤አዎ፣ በሥጋ ለባሽ* ሁሉ ላይ በሰይፍ ፍርዱን ይፈጽማል፤በይሖዋ እጅ የሚገደሉትም ብዙ ይሆናሉ።
17 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “መሃል ላይ ያለውን ተከትለው ወደ አትክልት ቦታዎቹ*+ ለመግባት ሲሉ ራሳቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፣ የአሳማ ሥጋና አስጸያፊ ነገር እንዲሁም አይጥ የሚበሉ ሁሉ+ በአንድነት ይጠፋሉ።
18 እኔ ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ፣ ከሁሉም ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎችን ለመሰብሰብ እመጣለሁ፤ እነሱም መጥተው ክብሬን ያያሉ።”
19 “በመካከላቸው ምልክት አቆማለሁ፤ ከተረፉት መካከል አንዳንዶቹን ወደ ብሔራት ይኸውም ወደ ተርሴስ፣+ ወደ ፑል እና ወደ ሉድ+ እልካለሁ። በቱባልና በያዋን+ ወዳሉት ቀስተኞች እልካቸዋለሁ። ስለ እኔ ወዳልሰሙ ወይም ክብሬን ወዳላዩ፣ ርቀው በሚገኙ ደሴቶች ውስጥ ወደሚኖሩ ሕዝቦችም እልካቸዋለሁ፤ እነሱም በብሔራት መካከል ክብሬን ያውጃሉ።+
20 የእስራኤል ልጆች በንጹሕ ዕቃ ስጦታ ይዘው ወደ ይሖዋ ቤት እንደሚያመጡ፣ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ለይሖዋ ስጦታ እንዲሆኑ ከየብሔራቱ በፈረሶች፣ በሠረገሎች፣ ጥላ ባላቸው ጋሪዎች፣ በበቅሎዎችና በፈጣን ግመሎች ጭነው ወደተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጧቸዋል”+ ይላል ይሖዋ።
21 “በተጨማሪም አንዳንዶቹን ካህናት፣ ሌሎቹን ደግሞ ሌዋውያን እንዲሆኑ እወስዳለሁ” ይላል ይሖዋ።
22 “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር+ በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ ሁሉ የእናንተም ዘርና ስማችሁ እንዲሁ ጸንቶ ይኖራል”+ ይላል ይሖዋ።
23 “ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው ወር መባቻ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው ሰንበት፣ሰው* ሁሉ በፊቴ ለመስገድ* ይመጣል”+ ይላል ይሖዋ።
24 “እነሱም ሄደው በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤በእነሱ ላይ ያሉት ትሎች አይሞቱምና፤እሳታቸውም አይጠፋም፤+ለሰዎችም* ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።”