ኢሳይያስ 8:1-22

  • የአሦር ወረራ (1-8)

    • ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ (1-4)

  • አትፍሩ፤ “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” (9-17)

  • ኢሳይያስና ልጆቹ ምልክት ሆነው ያገለግላሉ (18)

  • አጋንንትን ከመጠየቅ ይልቅ ሕጉን ተመልከቱ (19-22)

8  ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “አንድ ትልቅ ጽላት+ ወስደህ በብዕር* ‘ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ’* ብለህ ጻፍ።  ታማኝ ምሥክሮች የሆኑት ካህኑ ኦርዮና+ የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ደግሞ የጽሑፍ ማረጋገጫ ይስጡኝ።”*  እኔም ከነቢዪቱ* ጋር ተገናኘሁ፤* እሷም ፀነሰች፤ በኋላም ወንድ ልጅ ወለደች።+ ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “ስሙን ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ ብለህ ጥራው፤  ልጁ ‘አባዬ!’ እና ‘እማዬ!’ ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወሰዳል።”+  ይሖዋ በድጋሚ እንዲህ አለኝ፦   “ይህ ሕዝብ ቀስ ብለው የሚወርዱትን የሺሎአ* ውኃዎች ንቆ+በረጺንና በረማልያህ+ ልጅ ሐሴት ስላደረገ   እነሆ፣ ይሖዋ ብርቱ የሆኑትንና ከፍተኛ መጠን ያላቸውን የወንዙን* ውኃዎች ይኸውምየአሦርን ንጉሥና+ ክብሩን ሁሉበእነሱ ላይ ያመጣባቸዋል። እሱም የውኃ መውረጃዎቹን ሁሉ ሞልቶ ይፈስሳል፤ዳርቻዎቹንም ሁሉ ያጥለቀልቃል፤   ይሁዳንም ጠራርጎ ይሄዳል። አካባቢውን እያጥለቀለቀ በማለፍ እስከ አንገት ይደርሳል፤+አማኑኤል*+ ሆይ፣ የተዘረጉት ክንፎቹምድርህን ከዳር እስከ ዳር ይሸፍናሉ!”   እናንተ ሕዝቦች፣ ጉዳት አድርሱባቸው፤ ሆኖም ድምጥማጣችሁ ይጠፋል። ራቅ ባሉ የምድር ክፍሎች የምትኖሩ ሁሉ አዳምጡ! ለውጊያ ተዘጋጁ፤* ነገር ግን ድምጥማጣችሁ ይጠፋል!+ ለውጊያ ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ድምጥማጣችሁ ይጠፋል! 10  ዕቅድ አውጡ፤ ይሁንና ይጨናገፋል! የፈለጋችሁትን ተናገሩ፤ ሆኖም አይሳካም፤አምላክ ከእኛ ጋር ነውና!*+ 11  ይሖዋ ብርቱ እጁን በእኔ ላይ አድርጎ የዚህን ሕዝብ መንገድ እንዳልከተል ለማስጠንቀቅ እንዲህ አለኝ፦ 12  “ይህ ሕዝብ ‘ሴራ እንጠንስስ!’ ሲል እናንተ ‘በሴራው ተባበሩ!’ አትበሉ፤ እነሱ የሚያስፈራቸውን ነገር አትፍሩ፤አትንቀጥቀጡለትም። 13  ቅዱስ አድርጋችሁ ልትመለከቱ የሚገባው የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ነው፤+ልትፈሩ የሚገባው እሱን ነው፤እንዲሁም ልትንቀጠቀጡ የሚገባው ለእሱ ነው።”+ 14  እሱ እንደ መቅደስ ይሆናል፤ለሁለቱ የእስራኤል ቤቶች ግንእንደሚያሰናክል ድንጋይናእንደሚያደናቅፍ ዓለት፣+ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎችምእንደ ወጥመድና እንደ አሽክላ ይሆንባቸዋል። 15  ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ ይደናቀፋሉ፣ ይወድቃሉ፣ ይሰበራሉ፤ወጥመድ ውስጥ ገብተው ይያዛሉ። 16  በጽሑፍ የሰፈረውን ማረጋገጫ* ጠቅልለው፤ሕጉን* በደቀ መዛሙርቴ መካከል አሽገው! 17  እኔም ፊቱን ከያዕቆብ ቤት የሰወረውን+ ይሖዋን እጠባበቃለሁ፤*+ በእሱም ተስፋ አደርጋለሁ። 18  እነሆ፣ እኔና ይሖዋ የሰጠኝ ልጆች+ በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ለእስራኤል እንደተሰጡ ምልክቶችና+ ተአምራት ነን። 19  እነሱም “የሚያነበንቡትንና የሚያንሾካሹኩትን መናፍስት ጠሪዎች ወይም ጠንቋዮች ጠይቁ” ቢሏችሁ፣ አንድ ሕዝብ መጠየቅ ያለበት የራሱን አምላክ አይደለም? ስለ ሕያዋንስ ሙታንን መጠየቁ ተገቢ ነው?+ 20  ከዚህ ይልቅ ሕጉንና የማረጋገጫ ሰነዱን* መመርመር ይገባቸዋል! ከዚህ ቃል ጋር የሚስማማ ነገር ሳይናገሩ ሲቀሩ ብርሃን አይበራላቸውም።*+ 21  እያንዳንዱም ተጎሳቁሎና ተርቦ በምድሪቱ ላይ ይንከራተታል፤+ ከመራቡና ከመበሳጨቱ የተነሳ ወደ ላይ እያየ ንጉሡንና አምላኩን ይረግማል። 22  ከዚያም ወደ ምድር ይመለከታል፤ የሚያየውም ነገር ጭንቀትና ጨለማ፣ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ፣ አስቸጋሪ ወቅትና ብርሃን የሌለበት ፅልማሞት ብቻ ይሆናል።

የግርጌ ማስታወሻ

“ወደ ምርኮው ፈጥኖ መሄድ፣ ወደ ብዝበዛው ፈጥኖ መምጣት” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።
ቃል በቃል “ሟች በሆነ ሰው ብዕር።”
ወይም “ይመሥክሩልኝ፤ ቃላቸውን ይስጡልኝ።”
የኢሳይያስን ሚስት ታመለክታለች።
ቃል በቃል “ወደ ነቢዪቱ ቀረብኩ።”
ሺሎአ የውኃ ቦይ ነበር።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ኢሳ 7:14ን ተመልከት።
ወይም “ታጠቁ።”
“አምላክ ከእኛ ጋር ነው” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ኢማኑኤል የሚለው ነው። ኢሳ 7:14ንና 8:8ን ተመልከት።
ወይም “የምሥክርነት ቃል።”
ወይም “መመሪያውን፤ ትምህርቱን።”
ወይም “በጉጉት እጠብቃለሁ።”
ወይም “የምሥክርነት ቃሉን።”
ቃል በቃል “አይነጋላቸውም።”