ኢዩኤል 1:1-20

  • አውዳሚ የሆነ የአንበጣ መቅሰፍት (1-14)

  • “የይሖዋ ቀን ቀርቧል” (15-20)

    • ነቢዩ ወደ ይሖዋ ተጣራ (19, 20)

1  ወደ ፐቱኤል ልጅ፣ ወደ ኢዩኤል* የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው፦   “እናንተ ሽማግሌዎች ይህን ስሙ፤የአገሪቱም* ነዋሪዎች ሁሉ ልብ በሉ። በእናንተም ዘመን ይሁን በአባቶቻችሁ ዘመንእንዲህ ያለ ነገር ተከስቶ ያውቃል?+   ይህን ለልጆቻችሁ ተናገሩ፤ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፣የእነሱ ልጆች ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ይናገሩ።   ከአውዳሚ አንበጣ የተረፈውን የአንበጣ መንጋ በላው፤+ከአንበጣ መንጋ የተረፈውንም ኩብኩባ በላው፤ከኩብኩባ የተረፈውን ደግሞ የማይጠግብ አንበጣ በላው።+   እናንተ ሰካራሞች ንቁ፤+ ደግሞም አልቅሱ! እናንተ የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉጣፋጩ የወይን ጠጅ ከአፋችሁ ላይ ስለተወሰደ ዋይ ዋይ በሉ።+   ኃያል የሆነና የሕዝቡ ብዛት ስፍር ቁጥር የሌለው ብሔር ምድሬን ወሮታልና።+ ጥርሶቹ የአንበሳ ጥርሶች ናቸው፤+ መንገጭላውም የአንበሳ መንገጭላ ነው።   የወይን ተክሌን አጠፋው፤ የበለስ ዛፌንም ጉቶ አደረገው፤ቅርፊታቸውን ሙልጭ አድርጎ ልጦ ወዲያ ጣላቸው፤በቅርንጫፎቻቸው ላይ አንድም ልጥ አልቀረም።   ማቅ ለብሳ ለልጅነት ሙሽራዋ* እንደምታለቅስ ድንግል*ዋይ ዋይ በዪ።   የእህል መባና+ የመጠጥ መባ+ ከይሖዋ ቤት ተቋርጧል፤የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑት ካህናቱም ሐዘን ላይ ናቸው። 10  እርሻው ወድሟል፤ ምድሪቱ አዝናለች፤+እህሉ ወድሟልና፤ አዲሱ የወይን ጠጅ ደርቋል፤ ዘይቱም ተሟጧል።+ 11  ገበሬዎች አፍረዋል፤ የወይን አትክልት ሠራተኞች ዋይ ዋይ ይላሉ፤ይህም የሆነው ከስንዴውና ከገብሱ የተነሳ ነው፤የእርሻው መከር ጠፍቷልና። 12  ወይኑ ደርቋል፤የበለስ ዛፉም ጠውልጓል። ሮማኑ፣ ዘንባባው፣ ፖሙናበሜዳው ላይ ያለው ዛፍ ሁሉ ደርቋል፤+በሕዝቡ መካከል የነበረው ደስታ ወደ ኀፍረት ተለውጧልና። 13  እናንተ ካህናት ማቅ ልበሱ፤* ደግሞም ሐዘን ተቀመጡ፤*እናንተ በመሠዊያው ፊት የምታገለግሉ+ ዋይ ዋይ በሉ። እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች ኑ፣ ማቅ ለብሳችሁ እደሩ፤ከአምላካችሁ ቤት የእህል መባና+ የመጠጥ መባ+ ተቋርጧልና። 14  ጾም አውጁ!* የተቀደሰ ጉባኤ ጥሩ።+ ሽማግሌዎቹንና የምድሪቱን ነዋሪዎች ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ ይሖዋ ቤት ሰብስቡ፤+እርዳታም ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጩኹ። 15  ከቀኑ የተነሳ ወዮላችሁ! የይሖዋ ቀን ቀርቧልና፤+ሁሉን ከሚችለው አምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል! 16  ምግብ ከዓይናችን ፊት፣ሐሴትና ደስታም ከአምላካችን ቤት ጠፍቶ የለም? 17  ዘሮቹ* ከአካፋዎቻቸው ሥር ጠውልገዋል። ጎተራዎቹም ተራቁተዋል። ጎታዎቹ* ፈራርሰዋል፤ እህሉ ደርቋልና። 18  መንጎቹ እንኳ ሳይቀሩ ያቃስታሉ! ከብቶቹ ግራ ተጋብተው ይቅበዘበዛሉ፤ መሰማሪያ የላቸውምና! የበጎቹም መንጋ ቅጣቱን ይቀበላል። 19  ይሖዋ ሆይ፣ ወደ አንተ እጣራለሁ፤+በምድረ በዳ ያለውን የግጦሽ መሬት እሳት በልቶታልና፤በሜዳ ያሉትንም ዛፎች ሁሉ ነበልባል አቃጥሏቸዋል። 20  የዱር አራዊትም እንኳ አንተን በጉጉት ይጠባበቃሉ፤ምክንያቱም የውኃ ጅረቶቹ ደርቀዋል፤በምድረ በዳ ያለውን የግጦሽ መሬትም እሳት በልቶታል።”

የግርጌ ማስታወሻ

“ይሖዋ አምላክ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “የምድሪቱም።”
ወይም “ባሏ።”
ወይም “ወጣት ሴት።”
ቃል በቃል “ታጠቁ።”
ወይም “ደረታችሁን ምቱ።”
ቃል በቃል “ጾምን ቀድሱ።”
“የደረቁት በለሶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ከጎተራ አነስ ያለ የእህል ማስቀመጫ።