ኢዩኤል 2:1-32

  • የይሖዋ ቀንና ታላቅ ሠራዊት (1-11)

  • ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ የቀረበ ጥሪ (12-17)

    • “ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” (13)

  • ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጠው ምላሽ (18-32)

    • “መንፈሴን አፈሳለሁ” (28)

    • በሰማይና በምድር የሚከናወኑ ድንቅ ነገሮች (30)

    • “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” (32)

2  “በጽዮን ቀንደ መለከት ንፉ!+ በቅዱሱ ተራራዬ ላይ ቀረርቶ አሰሙ። የአገሪቱ* ነዋሪዎች በሙሉ ይንቀጥቀጡ፤የይሖዋ ቀን ቀርቧልና!+ ቀኑ ደፍ ላይ ነው!   የጨለማና የጭጋግ ቀን፣+የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤+በተራሮች ላይ እንደፈነጠቀ የማለዳ ወጋገን ነው። ስፍር ቁጥር የሌለውና ኃያል የሆነ ሕዝብ ይመጣል፤+ከዚህ በፊት እንደ እሱ ያለ ፈጽሞ ታይቶ አያውቅም፤ወደፊትም ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስእንደ እሱ ያለ አይኖርም።   ከፊቱ ያለውን እሳት ይበላዋል፤ከኋላው ያለውንም ነበልባል ያቃጥለዋል።+ ከፊቱ ያለው ምድር እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ ነው፤+ከኋላው ያለው ግን ወና ምድረ በዳ ነው፤ከእሱም የሚያመልጥ አይኖርም።   መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፤እንደ ጦር ፈረሶችም ይጋልባሉ።+   በተራሮች አናት ላይ ሲዘሉ የሚሰማው ድምፅ እንደ ሠረገሎች ድምፅ፣+ገለባንም እንደሚበላ የሚንጣጣ የእሳት ነበልባል ድምፅ ነው። ለጦርነት እንደተሰለፈ+ ኃያል ሕዝብ ናቸው።   ከእነሱም የተነሳ ሕዝቦች ይጨነቃሉ። የሰውም ፊት ሁሉ ይቀላል።   እንደ ተዋጊዎች በፍጥነት ጥቃት ይሰነዝራሉ፤እንደ ወታደሮች ቅጥር ላይ ይወጣሉ፤እያንዳንዱም የራሱን መንገድ ይዞ ይሄዳል፤አቅጣጫቸውንም አይቀይሩም።   እርስ በርሳቸው አይገፋፉም፤እያንዳንዱ ሰው መንገዱን ይዞ ይገሰግሳል። አንዳንዶቹ በመሣሪያ* ተመተው ቢወድቁ እንኳሌሎቹ አይፍረከረኩም።   ወደ ከተማዋ እየተጣደፉ ይገባሉ፤ በቅጥርም ላይ ይሮጣሉ። ቤቶችም ላይ ይወጣሉ፤ እንደ ሌባ በመስኮት ይገባሉ። 10  ምድሪቱ በፊታቸው ትንቀጠቀጣለች፤ ሰማያትም ይናወጣሉ። ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፤+ከዋክብትም ብርሃናቸውን መስጠት አቁመዋል። 11  ይሖዋ በሠራዊቱ+ ፊት ድምፁን በኃይል ያሰማል፤ ሠራዊቱ ስፍር ቁጥር የለውም።+ ቃሉን የሚፈጽመው ኃያል ነውና፤የይሖዋ ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነው።+ ማንስ ሊቋቋመው ይችላል?”+ 12  “አሁንም ቢሆን” ይላል ይሖዋ፣“በጾም፣+ በለቅሶና በዋይታ በሙሉ ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ።+ 13  ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤+ወደ አምላካችሁ ወደ ይሖዋም ተመለሱ፤እሱ ሩኅሩኅና* መሐሪ፣ ለቁጣ የዘገየና+ ታማኝ ፍቅሩ የበዛ ነውና፤+ሊያመጣ ያሰበውንም ጥፋት መለስ ብሎ ያጤናል።* 14  ደግሞም ተመልሶ ጉዳዩን እንደገና በማጤን፣*+ለአምላካችሁ ለይሖዋ የእህል መባና የመጠጥ መባ ማቅረብ ትችሉ ዘንድበረከት ያስቀርላችሁ እንደሆነ ማን ያውቃል? 15  በጽዮን ቀንደ መለከት ንፉ! ጾም አውጁ፤* የተቀደሰ ጉባኤ ጥሩ።+ 16  ሕዝቡን ሰብስቡ፤ ጉባኤውን ቀድሱ።+ ሽማግሌዎቹን ሰብስቡ፤ ልጆቹንና ጡት የሚጠቡትን ሕፃናት ሰብስቡ።+ ሙሽራው ከውስጠኛው ክፍል፣ ሙሽሪትም ከጫጉላ ቤት ይውጡ። 17  የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑት ካህናቱበበረንዳውና በመሠዊያው መካከል+ ሆነው ያልቅሱ፤ እንዲህም ይበሉ፦ ‘ይሖዋ ሆይ፣ ለሕዝብህ እዘን፤ርስትህ መሳለቂያ እንዲሆን አታድርግ፤ብሔራትም አይግዟቸው። ሕዝቦች “አምላካቸው የት አለ?” ለምን ይበሉ?’+ 18  ያን ጊዜ ይሖዋ ለምድሩ ይቀናል፤ለሕዝቡም ይራራል።+ 19  ይሖዋ ለሕዝቡ መልስ ይሰጣል፦ ‘እነሆ እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅና ዘይት እልክላችኋለሁ፤እናንተም በሚገባ ትጠግባላችሁ፤+ከእንግዲህ በብሔራት መካከል ለነቀፋ አልዳርጋችሁም።+ 20  የሰሜኑን ሠራዊት ከእናንተ አርቃለሁ፤ደረቅና ወና ወደሆነ ጠፍ መሬት እበትነዋለሁ፤ፊቱ ወደ ምሥራቁ ባሕር፣*ኋላውም ወደ ምዕራቡ ባሕር* ይሆናል። ግማቱ ወደ ላይ ይወጣል፤ክርፋቱም ወደ ላይ መውጣቱን ይቀጥላል፤+አምላክ ታላላቅ ነገሮች ያደርጋልና።’ 21  ምድር ሆይ፣ አትፍሪ። ደስ ይበልሽ፤ ሐሴትም አድርጊ፤ ይሖዋ ታላላቅ ነገሮች ያደርጋልና። 22  እናንተ የዱር እንስሳት፣ አትፍሩ፤በምድረ በዳ ያሉት መሰማሪያዎች ይለመልማሉና፤+ዛፎችም ፍሬ ያፈራሉ፤+የበለስ ዛፉና የወይን ተክሉ ጥሩ ምርት ይሰጣሉ።+ 23  እናንተ የጽዮን ልጆች ሆይ፣ በአምላካችሁ በይሖዋ ተደሰቱ፤ ሐሴትም አድርጉ፤+እሱ የፊተኛውን ዝናብ በተገቢው መጠን ይሰጣችኋልና፤በእናንተም ላይ ዝናቡን ያዘንባል፤እንደቀድሞውም የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ ይሰጣችኋል።+ 24  አውድማዎቹ በእህል ይሞላሉ፤መጭመቂያዎቹም በአዲስ የወይን ጠጅና በዘይት ተሞልተው ያፈሳሉ።+ 25  ደግሞም በመካከላችሁ የሰደድኩት ታላቁ ሠራዊቴይኸውም የአንበጣ መንጋው፣ ኩብኩባው፣ የማይጠግበው አንበጣና አውዳሚው አንበጣሰብላችሁን ለበሉባቸው ዓመታት ማካካሻ እሰጣችኋለሁ።+ 26  እስክትጠግቡ ድረስ ትበላላችሁ፤+ደግሞም ድንቅ ነገሮችን ያደረገላችሁንየአምላካችሁን የይሖዋን ስም ታወድሳላችሁ፤+ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አያፍርም።+ 27  እናንተም እኔ በእስራኤል መካከል እንደሆንኩ+እንዲሁም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ እንደሆንኩ፣+ ከእኔም በቀር ሌላ እንደሌለ ታውቃላችሁ! ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አያፍርም። 28  ከዚያ በኋላ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤+ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፤ወጣቶቻችሁም ራእዮችን ያያሉ።+ 29  በዚያ ቀን በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀርመንፈሴን አፈሳለሁ። 30  በሰማያትና በምድር ድንቅ ነገሮች አሳያለሁ፤*ደም፣ እሳትና የጭስ ዓምድ ይታያል።+ 31  ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን+ ከመምጣቱ በፊትፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።+ 32  የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤+ይሖዋ እንደተናገረው በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም የሚድኑ+ ይኸውምይሖዋ የሚጠራቸው ከጥፋት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የምድሪቱ።”
ወይም “በተወንጫፊ መሣሪያዎች።”
ወይም “ቸርና።”
ወይም “ሊያመጣ ባሰበውም ጥፋት ይጸጸታል።”
ወይም “በመጸጸት።”
ቃል በቃል “ጾምን ቀድሱ።”
ሙት ባሕርን ያመለክታል።
ሜድትራንያን ባሕርን ያመለክታል።
ወይም “ምልክቶች አሳያለሁ።”