ኢያሱ 1:1-18

  • ይሖዋ ኢያሱን አበረታታው (1-9)

    • ሕጉን በለሆሳስ አንብብ (8)

  • የዮርዳኖስን ወንዝ ለመሻገር መዘጋጀት (10-18)

1  የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ከሞተ በኋላ ይሖዋ የሙሴ አገልጋይ+ የነበረውን የነዌን ልጅ ኢያሱን*+ እንዲህ አለው፦  “አገልጋዬ ሙሴ ሞቷል።+ እንግዲህ አንተም ሆንክ ይህ ሕዝብ ተነስታችሁ ዮርዳኖስን በመሻገር ለእስራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ግቡ።+  ለሙሴ በገባሁት ቃል መሠረት እግራችሁ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ እሰጣችኋለሁ።+  ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስና እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ይኸውም መላው የሂታውያን+ ምድር እንዲሁም በስተ ምዕራብ* እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር* ድረስ ይሆናል።+  በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም።+ ከሙሴ ጋር እንደነበርኩ ሁሉ ከአንተም ጋር እሆናለሁ።+ አልጥልህም ወይም አልተውህም።+  ይህን ሕዝብ ለአባቶቻቸው ልሰጣቸው ወደማልኩላቸው ምድር+ የምታስገባው አንተ ስለሆንክ ደፋርና ብርቱ ሁን።+  “ብቻ አንተ ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አገልጋዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽም። በምትሄድበት በየትኛውም ቦታ ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን እንድትችል+ ከዚህ ሕግ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበል።+  ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤+ በውስጡ የተጻፈውንም በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችል ቀንም ሆነ ሌሊት በለሆሳስ አንብበው፤*+ እንዲህ ካደረግክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።+  ደፋርና ብርቱ ሁን ብዬ አዝዤህ አልነበረም? አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ።”+ 10  ከዚያም ኢያሱ የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 11  “በሰፈሩ ውስጥ በመዘዋወር ሕዝቡን እንዲህ በማለት እዘዙ፦ ‘አምላካችሁ ይሖዋ ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ለመውረስ በሦስት ቀን ውስጥ ዮርዳኖስን ስለምትሻገሩ ስንቃችሁን አዘጋጁ።’”+ 12  ኢያሱም ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ እንዲህ አላቸው፦ 13  “የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ እንዲህ በማለት ያዘዛችሁን ቃል አስታውሱ፦+ ‘አምላካችሁ ይሖዋ እረፍት ሰጥቷችኋል፤ ይህን ምድር አውርሷችኋል። 14  ሚስቶቻችሁ፣ ልጆቻችሁና ከብቶቻችሁ ሙሴ በሰጣችሁ ከዮርዳኖስ ወዲህ ባለው ምድር* ላይ ይቀመጣሉ፤+ ሆኖም ብርቱ የሆናችሁት ተዋጊዎች በሙሉ+ የጦርነት አሰላለፍ በመከተል ወንድሞቻችሁን ቀድማችሁ ትሻገራላችሁ።+ እነሱን መርዳት ይገባችኋል፤ 15  ይሖዋ ለእናንተ እንዳደረገው ሁሉ ለወንድሞቻችሁም እረፍት እስከሚሰጣቸውና አምላካችሁ ይሖዋ የሚሰጣቸውን ምድር እስከሚወርሱ ድረስ ይህን ማድረግ ይኖርባችኋል። ከዚያም እንድትይዟትና እንድትወርሷት ወደተሰጠቻችሁ ይኸውም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ወደሰጣችሁ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ምድር ትመለሳላችሁ።’”+ 16  እነሱም ለኢያሱ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “የምታዘንን ሁሉ እንፈጽማለን፤ ወደምትልከንም ሁሉ እንሄዳለን።+ 17  ሙሴ የሚለንን ማንኛውንም ነገር እንሰማ እንደነበር ሁሉ አንተንም እንሰማለን። ብቻ አምላክህ ይሖዋ ከሙሴ ጋር እንደነበረ ሁሉ ከአንተም ጋር ይሁን።+ 18  መመሪያህን አልታዘዝም የሚልና የምትሰጠውን ትእዛዝ ሁሉ የማይሰማ ማንኛውም ሰው ይገደል።+ ብቻ አንተ ደፋርና ብርቱ ሁን።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የሆሹአን።” “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “በፀሐይ መግቢያ።”
ሜድትራንያንን ያመለክታል።
ወይም “አሰላስልበት።”
በስተ ምሥራቅ ያለውን ምድር ያመለክታል።