ኢያሱ 13:1-33
13 ኢያሱም ዕድሜው ገፍቶና አርጅቶ ነበር።+ በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አንተ ዕድሜህ ገፍቷል፤ አርጅተሃል፤ ሆኖም መወረስ* ያለበት ገና ሰፊ ምድር ይቀራል።
2 የሚቀረውም ምድር ይህ ነው፦+ የፍልስጤማውያንና የገሹራውያን+ ምድር በሙሉ
3 (ከግብፅ ፊት ለፊት ከሚገኘው ከአባይ ወንዝ ቅርንጫፍ* አንስቶ በሰሜን እስከ ኤቅሮን ወሰን ድረስ ያለው ክልል የከነአናውያን ግዛት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር)+ እንዲሁም በጋዛ፣ በአሽዶድ፣+ በአስቀሎን፣+ በጌት+ እና በኤቅሮን+ የሚኖሩትን የአምስቱን የፍልስጤም ገዢዎች+ ምድር የሚጨምር ሲሆን የአዊም+ ሰዎችንም ምድር ያካትታል፤
4 እነሱም በደቡብ በኩል ይኖሩ ነበር፤ መላው የከነአናውያን ምድር፤ የሲዶናውያን+ ይዞታ የሆነችው መአራ፣ እንዲሁም በአሞራውያን ወሰን ላይ እስከሚገኘው እስከ አፌቅ ድረስ ያለው አካባቢ፤
5 የጌባላውያን+ ምድር፣ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ያለው መላው ሊባኖስ ይኸውም በሄርሞን ተራራ ግርጌ ከሚገኘው ከበዓልጋድ አንስቶ እስከ ሌቦሃማት*+ ድረስ ያለው አካባቢ፤
6 በተራራማው አካባቢ፣ ከሊባኖስ+ እስከ ሚስረፎትማይም+ ባለው ምድር የሚኖሩት ነዋሪዎች በሙሉ እንዲሁም ሲዶናውያን+ በሙሉ ናቸው። እነሱንም ከእስራኤላውያን ፊት አባርራቸዋለሁ።+ አንተም ባዘዝኩህ መሠረት ምድሩን ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ ስጥ።+
7 እንግዲህ ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገዶችና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አከፋፍል።”+
8 የተቀረው የምናሴ ነገድ እኩሌታና ሮቤላውያን እንዲሁም ጋዳውያን የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ በሰጣቸው መሠረት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ርስታቸውን ወስደዋል፤+
9 ይህም በአርኖን ሸለቆ*+ መካከል የምትገኘውን ከተማና የመደባን አምባ በሙሉ ጨምሮ በሸለቆው ዳርቻ ላይ ከምትገኘው ከአሮዔር+ አንስቶ እስከ ዲቦን ድረስ ያለውን አካባቢ፣
10 በሃሽቦን ሆኖ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንን ከተሞች በሙሉ እስከ አሞናውያን+ ወሰን ድረስ፣
11 ጊልያድን፣ የገሹራውያንንና የማአካታውያንን+ ግዛት፣ የሄርሞንን ተራራ በሙሉ፣ ባሳንን+ በሙሉ እስከ ሳልካ+ ድረስ
12 እንዲሁም በአስታሮት እና በኤድራይ ሆኖ ይገዛ የነበረውን በባሳን ያለውን የኦግን ንጉሣዊ ግዛት በሙሉ ያጠቃልላል። (እሱም በሕይወት ከተረፉት የመጨረሻዎቹ የረፋይም ዘሮች አንዱ ነበር።)+ ሙሴም ድል አድርጎ አባረራቸው።+
13 ሆኖም እስራኤላውያን ገሹራውያንንና ማአካታውያንን ከምድራቸው አላስለቀቋቸውም፤+ ምክንያቱም ገሹራውያንና ማአካታውያን እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤል መካከል አሉ።
14 ውርስ ያልሰጠው ለሌዋውያን ነገድ ብቻ ነበር።+ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ቃል በገባላቸው መሠረት+ ለእሱ በእሳት የሚቀርቡት መባዎች የእነሱ ውርሻ ናቸው።+
15 ከዚያም ሙሴ ለሮቤላውያን ነገድ በየቤተሰባቸው ርስት ሰጣቸው፤
16 ግዛታቸውም በአርኖን ሸለቆ* ዳርቻ ላይ ከምትገኘው ከአሮዔር አንስቶ ያለው ሲሆን በሸለቆው መካከል የምትገኘውን ከተማ፣ የመደባን አምባ በሙሉ፣
17 ሃሽቦንንና በአምባው ላይ ያሉትን ከተሞቿን በሙሉ፣+ ዲቦንን፣ ባሞትበዓልን፣ ቤትበዓልመዖንን፣+
18 ያሃጽን፣+ ቀደሞትን፣+ መፋአትን፣+
19 ቂርያታይምን፣ ሲብማን፣+ በሸለቆው* አጠገብ ባለው ኮረብታ ላይ የምትገኘውን ጸሬትሻሃርን፣
20 ቤትጰኦርን፣ የጲስጋን ሸንተረሮች፣+ ቤትየሺሞትን፣+
21 በአምባው ላይ የሚገኙትን ከተሞች ሁሉ እንዲሁም በሃሽቦን+ ሆኖ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንን ንጉሣዊ ግዛት በሙሉ ያጠቃልላል። ሙሴም ይህን ንጉሥና+ በምድሪቱ ይኖሩ የነበሩትን የምድያም አለቆች፣ ኤዊን፣ ራቄምን፣ ጹርን፣ ሁርን እና ረባን+ እንዲሁም የሲሖንን መሳፍንት* ድል አድርጓቸው ነበር።
22 እስራኤላውያን በሰይፍ ከገደሏቸው መካከል ሟርተኛው+ የቢዖር ልጅ በለዓም+ ይገኝበታል።
23 የሮቤላውያን ወሰን ዮርዳኖስ ነበር፤ ከተሞቹንና መንደሮቹን ጨምሮ ይህ ግዛት ሮቤላውያን በየቤተሰባቸው የያዙት ርስት ነው።
24 በተጨማሪም ሙሴ ለጋድ ነገድ ይኸውም ለጋዳውያን በየቤተሰባቸው ርስት ሰጣቸው፤
25 ግዛታቸውም ያዜርን፣+ የጊልያድን ከተሞች በሙሉ፣ ከራባ+ ፊት ለፊት እስከምትገኘው እስከ አሮዔር የሚደርሰውን የአሞናውያንን+ ምድር እኩሌታ፣
26 ከሃሽቦን+ እስከ ራማትምጽጳ እና እስከ በጦኒም እንዲሁም ከማሃናይም+ እስከ ደቢር ወሰን ድረስ ያለውን አካባቢ፣
27 በሸለቆው ውስጥ* ደግሞ ቤትሃራምን፣ ቤትኒምራን፣+ ሱኮትን፣+ ጻፎንን እና ወሰኑ ዮርዳኖስ ሆኖ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ከኪኔሬት ባሕር*+ የታችኛው ጫፍ ጀምሮ ያለውን ቀሪውን የሃሽቦንን ንጉሥ የሲሖንን ንጉሣዊ ግዛት+ ያጠቃልላል።
28 ከተሞቹንና መንደሮቹን ጨምሮ ጋዳውያን በየቤተሰባቸው የያዙት ርስት ይህ ነው።
29 በተጨማሪም ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ይኸውም ለግማሹ የምናሴ ነገድ በየቤተሰባቸው ርስት ሰጠ።+
30 ግዛታቸውም ከማሃናይም+ አንስቶ ያለው ሲሆን ባሳንን በሙሉ፣ የባሳንን ንጉሥ የኦግን ንጉሣዊ ግዛት በሙሉ፣ በባሳን የሚገኙትን የያኢር+ የድንኳን ሰፈሮች በሙሉ፣ 60 ከተሞችን ያጠቃልላል።
31 የጊልያድ እኩሌታ እንዲሁም በባሳን የሚገኙት የኦግ ንጉሣዊ ግዛት ከተሞች ማለትም አስታሮትና ኤድራይ+ የምናሴ ልጅ ለሆነው ለማኪር+ ልጆች ይኸውም ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየቤተሰባቸው ተሰጡ።
32 ሙሴ ከዮርዳኖስ ማዶ ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ በሞዓብ በረሃማ ሜዳ የሰጣቸው ርስት ይህ ነበር።+
33 ሆኖም ሙሴ ለሌዋውያን ነገድ ርስት አልሰጠም።+ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ቃል በገባላቸው መሠረት ርስታቸው እሱ ነው።+