ኢያሱ 17:1-18
17 ከዚያም ዕጣው+ ለምናሴ+ ነገድ ወጣ፤ ምክንያቱም እሱ የዮሴፍ የበኩር ልጅ ነበር።+ የጊልያድ አባት የሆነው የምናሴ የበኩር ልጅ ማኪር+ ጦረኛ ሰው ስለነበር ጊልያድን እና ባሳንን+ ወሰደ።
2 ለቀሩት የምናሴ ዘሮችም በየቤተሰባቸው ይኸውም ለአቢዔዜር+ ልጆች፣ ለሄሌቅ ልጆች፣ ለአስሪዔል ልጆች፣ ለሴኬም ልጆች፣ ለሄፌር ልጆችና ለሸሚዳ ልጆች ዕጣ ወጣ። የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ዘሮች ወንዶቹ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ።+
3 ሆኖም የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የጊልያድ ልጅ፣ የሄፌር ልጅ ሰለጰአድ+ ሴቶች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሴቶች ልጆቹም ስም ማህላ፣ ኖኅ፣ ሆግላ፣ ሚልካ እና ቲርጻ ነበር።
4 እነሱም ወደ ካህኑ አልዓዛር፣+ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱና ወደ አለቆቹ ቀርበው “ይሖዋ በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን ሙሴን አዞት ነበር” አሏቸው።+ ስለዚህ ኢያሱ ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስት ሰጣቸው።+
5 ምናሴ በዮርዳኖስ ማዶ* ከነበሩት ከጊልያድና ከባሳን በተጨማሪ አሥር ድርሻዎች ወጡለት፤+
6 ምክንያቱም የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንዶች ልጆቹ መካከል ርስት ተሰጥቷቸው ነበር፤ የጊልያድም ምድር የቀሩት የምናሴ ዘሮች ርስት ሆነ።
7 የምናሴ ወሰን ከአሴር አንስቶ ከሴኬም+ ፊት ለፊት እስከምትገኘው እስከ ሚክመታት+ ድረስ ነበር፤ ወሰኑ በስተ ደቡብ* በኩል የኤንታጱአ ነዋሪዎች እስከሚገኙበት ምድር ይዘልቃል።
8 የታጱአ+ ምድር የምናሴ ሆነች፤ በምናሴ ወሰን ላይ የምትገኘው የታጱአ ከተማ ግን የኤፍሬም ዘሮች ነበረች።
9 ወሰኑ ወደ ቃና ሸለቆ ይኸውም ከሸለቆው በስተ ደቡብ ቁልቁል ይወርዳል። በምናሴ ከተሞች መካከል የሚገኙ የኤፍሬም ከተሞች የነበሩ ሲሆን+ የምናሴ ወሰን በሸለቆው ሰሜናዊ ክፍል አድርጎ ባሕሩ ጋ ሲደርስ ያበቃል።+
10 በስተ ደቡብ በኩል ያለው የኤፍሬም፣ በስተ ሰሜን በኩል ያለው ደግሞ የምናሴ ነበር፤ ባሕሩም የእሱ ወሰን ነበር፤+ እነሱም* በስተ ሰሜን እስከ አሴር፣ በስተ ምሥራቅ ደግሞ እስከ ይሳኮር ይደርሱ ነበር።
11 በይሳኮርና በአሴር ግዛቶች ውስጥ ለምናሴ የተሰጡት የሚከተሉት ናቸው፦ ቤትሼንና በሥሯ* ያሉት ከተሞች፣ ይብለአምና+ በሥሯ ያሉት ከተሞች፣ የዶር+ ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉት ከተሞች እንዲሁም የኤንዶር+ ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉት ከተሞች፣ የታአናክ+ ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉት ከተሞች፣ የመጊዶ ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉት ከተሞች፣ ሦስቱ ኮረብታማ አካባቢዎች።
12 ሆኖም የምናሴ ዘሮች እነዚህን ከተሞች መውረስ አልቻሉም፤ ከነአናውያን ይህን ምድር ላለመልቀቅ ቆርጠው ነበር።+
13 እስራኤላውያን እያየሉ በሄዱ ጊዜ ከነአናውያንን የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው፤+ ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ አላባረሯቸውም።*+
14 የዮሴፍ ዘሮችም ኢያሱን “አንድ ዕጣና+ አንድ ድርሻ ብቻ ርስት አድርገህ የሰጠኸን ለምንድን ነው?* ይሖዋ እስካሁን ድረስ ስለባረከን የሕዝባችን ቁጥር በዝቷል”+ አሉት።
15 ኢያሱም “ቁጥራችሁ ይህን ያህል ብዙ ከሆነ የኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ በጣም ስለሚጠብባችሁ ወደ ጫካው በመውጣት በፈሪዛውያንና+ በረፋይም+ ምድር የሚገኘውን አካባቢ ለራሳችሁ መንጥሩ” አላቸው።
16 ከዚያም የዮሴፍ ዘሮች እንዲህ አሉት፦ “ተራራማው አካባቢ አይበቃንም፤ ደግሞም በሸለቆው* ምድር ማለትም በቤትሼን+ እና በሥሯ* በሚገኙት ከተሞች እንዲሁም በኢይዝራኤል ሸለቆ+ ውስጥ* የሚኖሩት ከነአናውያን በሙሉ የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው የጦር ሠረገሎች* አሏቸው።”+
17 በመሆኑም ኢያሱ ለዮሴፍ ቤት ይኸውም ለኤፍሬምና ለምናሴ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ብዙ ሕዝብ ናችሁ፤ ታላቅ ኃይልም አላችሁ። ድርሻችሁ አንድ ዕጣ ብቻ አይሆንም፤+
18 ከዚህ ይልቅ ተራራማው አካባቢ የእናንተ ይሆናል።+ አካባቢው ጫካ ቢሆንም ትመነጥሩታላችሁ፤ የግዛታችሁም ወሰን ይሆናል። ምክንያቱም ከነአናውያን የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው የጦር ሠረገሎች* ያሏቸውና ብርቱዎች ቢሆኑም እንኳ ከምድሩ ታባርሯቸዋላችሁ።”+