ኢያሱ 20:1-9

  • የመማጸኛ ከተሞች (1-9)

20  ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦  “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘በሙሴ አማካኝነት በነገርኳችሁ መሠረት ለራሳችሁ የመማጸኛ ከተሞችን+ ምረጡ፤  ሳያስበው ወይም በድንገት* ሰው የገደለ* ግለሰብ ወደነዚህ ከተሞች መሸሽ ይችላል። እነሱም ከደም ተበቃዩ+ መሸሸጊያ ሆነው ያገለግሏችኋል።  ገዳዩ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ+ በከተማዋ በር ላይ ቆሞ+ ለከተማዋ ሽማግሌዎች ጉዳዩን ይናገር። እነሱም ወደ ከተማቸው አስገብተው መኖሪያ ይስጡት፤ እሱም አብሯቸው ይኖራል።  ደም ተበቃዩ ቢያሳድደው ሰዎቹ ነፍሰ ገዳዩን አሳልፈው አይስጡት፤ ምክንያቱም ግለሰቡ ባልንጀራውን የገደለው የቆየ ጥላቻ ኖሮት ሳይሆን በድንገት* ነው።+  ስለሆነም በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ እስኪቀርብ+ ድረስ በከተማዋ ውስጥ ይኑር፤ በዚያ ጊዜ የሚያገለግለው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስም ከዚያ መውጣት የለበትም።+ ከዚያ በኋላ ገዳዩ ሸሽቶ ወደወጣባት ከተማ መመለስ እንዲሁም ወደ ከተማውና ወደ ቤቱ መግባት ይችላል።’”+  በመሆኑም በንፍታሌም ተራራማ አካባቢ በገሊላ የምትገኘውን ቃዴሽን፣+ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ሴኬምንና+ በይሁዳ ተራራማ አካባቢ የምትገኘውን ቂርያትአርባን+ ማለትም ኬብሮንን ለዚህ ዓላማ ቀደሱ።*  ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ ባለው የዮርዳኖስ ክልል ደግሞ ከሮቤል ነገድ ርስት በአምባው ላይ በሚገኘው ምድረ በዳ ላይ ያለችውን ቤጼርን፣+ ከጋድ ነገድ ርስት በጊልያድ የምትገኘውን ራሞትን+ እንዲሁም ከምናሴ ነገድ ርስት በባሳን የምትገኘውን ጎላንን+ መረጡ።+  ሳያስበው ሰው* የገደለ ማንኛውም ግለሰብ በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት ደም ተበቃዩ አግኝቶ እንዳይገድለው ሸሽቶ እንዲሸሸግባቸው+ ለእስራኤላውያን በሙሉ ወይም በመካከላቸው ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው የተለዩት ከተሞች እነዚህ ናቸው።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ባለማወቅ።”
ወይም “ነፍስ መትቶ የገደለ።”
ወይም “ባለማወቅ።”
ወይም “ለዩ።”
ወይም “ነፍስ።”