ኢያሱ 3:1-17

  • እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ (1-17)

3  ከዚያም ኢያሱ በማለዳ ተነሳ፤ እሱም ሆነ እስራኤላውያን* በሙሉ ከሺቲም+ ተነስተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ። ወደ ማዶም ሳይሻገሩ እዚያው አደሩ።  ከሦስት ቀን በኋላም አለቆቹ+ በሰፈሩ ውስጥ በመዘዋወር  ሕዝቡን እንዲህ በማለት አዘዙ፦ “ሌዋውያን የሆኑት ካህናት+ የአምላካችሁን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ ከሰፈራችሁበት ቦታ ተነስታችሁ ታቦቱን ተከተሉት።  ሆኖም ወደ እሱ አትቅረቡ፤ በእናንተና በታቦቱ መካከል 2,000 ክንድ* ያህል ርቀት ይኑር፤ ከዚህ በፊት በዚህ አቅጣጫ ሄዳችሁ ስለማታውቁ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ።”  ኢያሱም ሕዝቡን “ይሖዋ በነገው ዕለት በመካከላችሁ ድንቅ ነገሮችን ስለሚያደርግ+ ራሳችሁን ቀድሱ”+ አላቸው።  ከዚያም ኢያሱ ካህናቱን “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንስታችሁ+ ከሕዝቡ ቀድማችሁ ሂዱ” አላቸው። በመሆኑም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት በማንሳት ከሕዝቡ ቀድመው ሄዱ።  ይሖዋም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሙሴ ጋር እንደነበርኩ ሁሉ+ ከአንተም ጋር መሆኔን እንዲያውቁ+ በዛሬው ዕለት አንተን በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።+  አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት ‘ዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ እዚያው ዮርዳኖስ ውስጥ ባላችሁበት ቁሙ’ ብለህ እዘዛቸው።”+  ኢያሱም እስራኤላውያንን “ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ስሙ” አላቸው። 10  ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ በመካከላችሁ ሕያው አምላክ እንዳለና+ እሱም ከነአናውያንን፣ ሂታውያንን፣ ሂዋውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ገርጌሻውያንን፣ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን በእርግጥ ከፊታችሁ እንደሚያባርራቸው በዚህ ታውቃላችሁ።+ 11  የምድር ሁሉ ጌታ የቃል ኪዳን ታቦት ቀድሟችሁ ወደ ዮርዳኖስ ይገባል። 12  እናንተም ከእስራኤል ነገዶች 12 ሰዎችን ይኸውም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ምረጡ፤+ 13  የምድር ሁሉ ጌታ የሆነውን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት እግር የዮርዳኖስን ውኃ ሲነካ* ከላይ የሚወርደው ውኃ ይቋረጣል፤ ውኃውም ልክ እንደ ግድብ* ቀጥ ብሎ ይቆማል።”+ 14  ስለዚህ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ለመሻገር ድንኳኑን ነቅሎ ሲነሳ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት+ ሕዝቡን ቀድመው ሄዱ። 15  ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ዮርዳኖስ ጋ ሲደርሱና እግራቸውን ውኃው ዳር ሲያጠልቁ (ወቅቱ መከር ስለነበር በመከር ጊዜ እንደሚሆነው ሁሉ የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ዳርቻውን አጥለቅልቆት ነበር)+ 16  ከላይ ይወርድ የነበረው ውኃ ቆመ። ውኃውም በሩቅ ይኸውም በጻረታን አጠገብ በምትገኘው በአዳም ከተማ እንደ ግድብ* ተቆልሎ ቆመ፤ በአረባ ወደሚገኘው ባሕር ይኸውም ወደ ጨው ባሕር* የሚወርደውም ውኃ ደረቀ። ውኃው ተቋርጦ ስለነበር ሕዝቡ ከኢያሪኮ ማዶ ወዳለው ስፍራ ተሻገረ። 17  እስራኤላውያን በሙሉ በደረቅ መሬት እስኪሻገሩ+ ይኸውም መላው ብሔር ዮርዳኖስን ተሻግሮ እስኪያበቃ ድረስ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ላይ ባሉበት ቆመው ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆች።”
ወደ 890 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “የዮርዳኖስ ውኃ ላይ ሲያርፍ።”
ወይም “ግድግዳ።”
ወይም “ግድግዳ።”
ሙት ባሕርን ያመለክታል።