ኢያሱ 8:1-35

  • ኢያሱ በጋይ ላይ የደፈጣ ተዋጊዎችን አሰለፈ (1-13)

  • ጋይ በቁጥጥር ሥር ዋለች (14-29)

  • ሕጉ ኤባል ተራራ ላይ ተነበበ (30-35)

8  ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “አትፍራ ወይም አትሸበር።+ ተዋጊዎቹን ሁሉ ይዘህ በጋይ ላይ ዝመት። እነሆ፣ የጋይን ንጉሥ፣ ሕዝቡን፣ ከተማውንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ።+  በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ያደረግከውን ሁሉ በጋይና በንጉሥዋም ላይ አድርግ፤+ የማረካችኋቸውን ነገሮችና ከብቶቿን ግን ለራሳችሁ ውሰዱ። ከከተማዋም በስተ ጀርባ የደፈጣ ተዋጊዎችን አስቀምጥ።”  ስለዚህ ኢያሱና ተዋጊዎቹ በሙሉ ጋይን ለመውጋት ወጡ። ኢያሱም 30,000 ኃያል ተዋጊዎችን መርጦ በሌሊት ላካቸው።  እንዲህም ሲል አዘዛቸው፦ “እንግዲህ እናንተ ከከተማዋ በስተ ጀርባ አድፍጣችሁ ትጠብቃላችሁ። ከከተማዋ ብዙ አትራቁ፤ ሁላችሁም በተጠንቀቅ ጠብቁ።  እኔና አብሮኝ ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማዋ እንቀርባለን፤ እነሱም ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ሊወጉን ሲወጡ+ እኛ ከፊታቸው እንሸሻለን።  እነሱም ‘ከዚህ በፊት እንዳደረጉት አሁንም ከፊታችን እየሸሹ ነው’+ በማለት ይከታተሉናል፤ በዚህ መንገድ ከከተማዋ እንዲርቁ እናደርጋቸዋለን። እኛም ከእነሱ እንሸሻለን።  እናንተም ካደፈጣችሁበት ቦታ ተነስታችሁ ከተማዋን ትቆጣጠራላችሁ፤ አምላካችሁ ይሖዋም ከተማዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል።  ከተማዋን እንደያዛችሁም በእሳት አቃጥሏት።+ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት አድርጉ። እንግዲህ እኔ አዝዣችኋለሁ።”  ከዚያም ኢያሱ ሰዎቹን ላካቸው፤ እነሱም አድፍጠው ወደሚጠባበቁበት ቦታ ሄዱ፤ ከጋይ በስተ ምዕራብ በቤቴልና በጋይ መካከል በሚገኘው ስፍራም አደፈጡ፤ ኢያሱ ግን ያን ሌሊት እዚያው ከሕዝቡ ጋር አደረ። 10  ከዚያም ኢያሱ በማለዳ ተነስቶ ሠራዊቱን ከሰበሰበ በኋላ እሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች እየመሯቸው ወደ ጋይ ይዘዋቸው ሄዱ። 11  ከእሱም ጋር የነበሩት ተዋጊዎች በሙሉ+ ገስግሰው ወደ ከተማዋ ፊት ቀረቡ። እነሱም ከጋይ በስተ ሰሜን ሰፈሩ፤ በእነሱና በጋይ መካከልም ሸለቆ ነበር። 12  በዚህ ጊዜ ኢያሱ 5,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ወስዶ ከከተማዋ በስተ ምዕራብ በኩል በቤቴልና+ በጋይ መካከል አድፍጠው እንዲጠብቁ+ አድርጎ ነበር። 13  ሕዝቡም ዋና ሰፈሩን ከከተማዋ በስተ ሰሜን አደረገ፤+ የኋላ ደጀን የሆነውን ሠራዊት ደግሞ ከከተማዋ በስተ ምዕራብ አደረገ፤+ ኢያሱም በዚያ ሌሊት ወደ ሸለቆው* መሃል ሄደ። 14  የጋይም ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ እሱና የከተማዋ ሰዎች ማልደው በመነሳት ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት በረሃማውን ሜዳ ቁልቁል ማየት ወደሚያስችላቸው ስፍራ በፍጥነት ገሰገሱ። ሆኖም ንጉሡ ከከተማዋ በስተ ጀርባ በእሱ ላይ ያደፈጠ ሠራዊት መኖሩን አላወቀም ነበር። 15  የጋይ ሰዎችም ጥቃት በሰነዘሩ ጊዜ ኢያሱና መላው እስራኤል ድል የተመቱ በማስመሰል ወደ ምድረ በዳው የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሸሹ።+ 16  ከዚያም በከተማዋ ውስጥ የነበረው ሕዝብ በሙሉ ወጥቶ እንዲያሳድዳቸው ተጠራ፤ እነሱም ኢያሱን እያሳደዱ ከከተማዋ ርቀው ሄዱ። 17  ከጋይም ሆነ ከቤቴል እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ አንድም ወንድ አልነበረም። ከተማዋንም ወለል አድርገው ከፍተው በመሄድ እስራኤልን ማሳደዳቸውን ተያያዙት። 18  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ኢያሱን “ከተማዋን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥህ+ የያዝከውን ጦር ወደ ጋይ አቅጣጫ ሰንዝር”+ አለው። ኢያሱም ይዞት የነበረውን ጦር ወደ ከተማዋ አቅጣጫ ሰነዘረ። 19  ያደፈጠውም ሠራዊት ኢያሱ እጁን በሰነዘረበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከቦታው ተነስቶ ወደ ከተማዋ ሮጦ በመግባት ያዛት። ከዚያም በፍጥነት ከተማዋን በእሳት አያያዟት።+ 20  የጋይ ሰዎች ዞረው ሲመለከቱ የከተማዋ ጭስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደየትኛውም አቅጣጫ መሸሽ የሚችሉበት አቅም አልነበራቸውም። ወደ ምድረ በዳው እየሸሹ የነበሩትም ሰዎች ወደ አሳዳጆቻቸው ዞሩ። 21  ኢያሱና እስራኤላውያን በሙሉ፣ አድፍጦ የነበረው ሠራዊት ከተማዋን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና የከተማዋ ጭስ ወደ ላይ መውጣቱን ሲመለከቱ ወደ ኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ማጥቃት ጀመሩ። 22  ከተማዋን ተቆጣጥረው የነበሩትም ሰዎች እነሱን ለመግጠም ከከተማዋ ወጡ፤ በመሆኑም የጋይ ሰዎች በሁለቱም በኩል ባሉት እስራኤላውያን መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ፤ እነሱም ፈጇቸው፤ ከመካከላቸው የተረፈም ሆነ ያመለጠ አንድም እንኳ አልነበረም።+ 23  የጋይን ንጉሥ+ ግን ከነሕይወቱ ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት። 24  እስራኤላውያን የጋይን ነዋሪዎች በሙሉ ሜዳ ላይ ይኸውም ሲያሳድዷቸው በነበረው ምድረ በዳ ላይ ፈጇቸው፤ አንድም ሳይቀር ሁሉም በሰይፍ አለቁ። ከዚያም እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ጋይ ተመልሰው ከተማዋን በሰይፍ መቱ። 25  ወንድ ሴት ሳይል በዚያን ቀን የሞቱት የጋይ ሰዎች በጠቅላላ 12,000 ነበሩ። 26  ኢያሱም የጋይን ነዋሪዎች በሙሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ+ ጦር የሰነዘረበትን እጁን አልመለሰውም።+ 27  እስራኤላውያንም ይሖዋ ለኢያሱ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የከተማዋን ምርኮና ከብቶች ለራሳቸው ወሰዱ።+ 28  ኢያሱም ጋይን በእሳት አጋያት፤ ከተማዋንም የፍርስራሽ ክምር ሆና እንድትቀር አደረጋት፤+ እስከ ዛሬም ድረስ ባድማ ናት። 29  የጋይንም ንጉሥ እስከ ማታ ድረስ እንጨት* ላይ ሰቀለው፤ ከዚያም ኢያሱ ፀሐይ ልትጠልቅ ስትል በድኑን ከእንጨቱ ላይ እንዲያወርዱት ትእዛዝ ሰጠ።+ እነሱም በድኑን በከተማዋ በር ላይ ጣሉት፤ በእሱም ላይ ትልቅ የድንጋይ ቁልል ከመሩበት፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛል። 30  ኢያሱም በኤባል ተራራ+ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ መሠዊያ የሠራው በዚያን ጊዜ ነበር፤ 31  መሠዊያውንም የሠራው የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ለእስራኤላውያን በሰጠው ትእዛዝና በሙሴ የሕግ መጽሐፍ+ ላይ በተጻፈው “መሠዊያው የብረት መሣሪያ ካልነካው ያልተጠረበ ድንጋይ የተሠራ ይሁን”+ በሚለው መመሪያ መሠረት ነው። በዚያም ላይ የሚቃጠሉ መባዎችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን ለይሖዋ አቀረቡ።+ 32  ከዚያም በድንጋዮቹ ላይ ሙሴ በእስራኤላውያን ፊት የጻፈውን ሕግ ቅጂ+ ጻፈባቸው።+ 33  እስራኤላውያን በሙሉ፣ ሽማግሌዎቻቸው፣ አለቆቻቸውና ዳኞቻቸው የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት በሚሸከሙት በሌዋውያን ካህናት ፊት ከታቦቱ ወዲህና ወዲያ ቆመው ነበር። የባዕድ አገር ሰዎችም ሆኑ የአገሬው ተወላጆች በዚያ ነበሩ።+ የእስራኤልን ሕዝብ ለመባረክ (የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ቀደም ሲል ባዘዘው መሠረት)+ ግማሾቹ በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት፣ ግማሾቹ ደግሞ በኤባል ተራራ ፊት ለፊት ቆሙ።+ 34  ከዚህ በኋላ ኢያሱ በሕጉ መጽሐፍ+ ላይ በተጻፈው መሠረት የሕጉን ቃላት በሙሉ ይኸውም በረከቱንና+ እርግማኑን+ ድምፁን ከፍ አድርጎ አነበበ። 35  ኢያሱ፣ ሙሴ ከሰጠው ትእዛዝ ውስጥ፣ ሴቶችንና ልጆችን እንዲሁም በመካከላቸው የሚኖሩ+ የባዕድ አገር ሰዎችን+ ጨምሮ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ድምፁን ከፍ አድርጎ ያላነበበው አንድም ቃል አልነበረም።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ረባዳማው ሜዳ።”
ወይም “ዛፍ።”