ኢያሱ 9:1-27

  • ብልህ የሆኑት ገባኦናውያን ከእስራኤላውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ፈጠሩ (1-15)

  • የገባኦናውያን ተንኮል ተጋለጠ (16-21)

  • ገባኦናውያን እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች ሆኑ (22-27)

9  ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ+ በተራራማው አካባቢ፣ በሸፌላ፣ በመላው የታላቁ ባሕር*+ ዳርቻ እንዲሁም በሊባኖስ ፊት ለፊት የነበሩት ነገሥታት ሁሉ ይኸውም ሂታውያን፣ አሞራውያን፣ ከነአናውያን፣ ፈሪዛውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን ይህን ሲሰሙ+  ኢያሱንና እስራኤልን ለመውጋት ግንባር ፈጠሩ።+  የገባኦን+ ነዋሪዎችም ኢያሱ በኢያሪኮና+ በጋይ+ ላይ ምን እንዳደረገ ሰሙ።  በመሆኑም ብልሃት ፈጠሩ፤ ስንቃቸውን ባረጁ ከረጢቶች ውስጥ ከከተቱ በኋላ ተቀዳደው ከተጠጋገኑ ያረጁ የወይን ጠጅ አቁማዳዎች ጋር በአህያዎቻቸው ላይ ጫኑ፤  በተጨማሪም ያደረጉት ነጠላ ጫማ ያለቀና የተጠጋገነ፣ የለበሱትም ልብስ ያረጀ ነበር። ለስንቅ የያዙትም ዳቦ በሙሉ የደረቀና የተፈረፈረ ነበር።  እነሱም በጊልጋል+ በሚገኘው ሰፈር ወደነበረው ወደ ኢያሱ ሄደው እሱንና የእስራኤልን ሰዎች “የመጣነው ከሩቅ አገር ነው። እንግዲህ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግቡ” አሏቸው።  ይሁን እንጂ የእስራኤል ሰዎች ሂዋውያኑን+ “ይህን ጊዜ እኮ የምትኖሩት እዚሁ አጠገባችን ይሆናል። ታዲያ ከእናንተ ጋር እንዴት ቃል ኪዳን እንገባለን?” አሏቸው።+  እነሱም መልሰው ኢያሱን “እኛ የአንተ አገልጋዮች* ነን” አሉት። ከዚያም ኢያሱ “እናንተ እነማን ናችሁ? የመጣችሁትስ ከየት ነው?” አላቸው።  በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ ለአምላክህ ለይሖዋ ስም ካለን አክብሮት የተነሳ ከሩቅ አገር የመጣን ነን፤+ ምክንያቱም ዝናውንና በግብፅ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል፤+ 10  እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ* በነበሩት በሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ይኸውም በሃሽቦን ንጉሥ በሲሖንና+ በአስታሮት በነበረው በባሳን ንጉሥ በኦግ+ ላይ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። 11  በመሆኑም ሽማግሌዎቻችንና የአገራችን ነዋሪዎች በሙሉ እንዲህ አሉን፦ ‘ለጉዟችሁ የሚሆን ስንቅ ይዛችሁ ወደ እነዚህ ሰዎች ሂዱ። ከዚያም “አገልጋዮቻችሁ እንሆናለን።+ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግቡ”+ በሏቸው።’ 12  ለስንቅ እንዲሆነን የያዝነው ይህ ዳቦ ወደዚህ ወደ እናንተ ለመምጣት ከቤታችን በወጣንበት ቀን ትኩስ ነበር። አሁን ግን ይኸው እንደምታዩት ደርቋል፤ ደግሞም ተፈርፍሯል።+ 13  እነዚህ የወይን ጠጅ አቁማዳዎች ያን ጊዜ ስንሞላቸው አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን ይኸው እንደምታዩአቸው ተቀዳደዋል።+ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችንም ረጅም መንገድ ከመጓዛችን የተነሳ አልቀዋል።” 14  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች ከስንቃቸው ላይ ጥቂት ወሰዱ፤* ስለ ጉዳዩ ግን ይሖዋን አልጠየቁም።+ 15  በመሆኑም ኢያሱ ከእነሱ ጋር በሰላም ለመኖር ተስማማ፤+ እንደማያጠፋቸውም ቃል ኪዳን ገባላቸው፤ የማኅበረሰቡም አለቆች ይህንኑ በመሐላ አጸኑላቸው።+ 16  እስራኤላውያንም ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ከገቡ ከሦስት ቀን በኋላ እነዚህ ሰዎች እዚያው በአቅራቢያቸው የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን ሰሙ። 17  ከዚያም እስራኤላውያን ተጉዘው በሦስተኛው ቀን ወደ ከተሞቻቸው ደረሱ፤ ከተሞቻቸውም ገባኦን፣+ ከፊራ፣ በኤሮት እና ቂርያትየአሪም+ ነበሩ። 18  ይሁን እንጂ የማኅበረሰቡ አለቆች በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ምለውላቸው+ ስለነበር እስራኤላውያን ጥቃት አልሰነዘሩባቸውም። ስለሆነም መላው ማኅበረሰብ በአለቆቹ ላይ ማጉረምረም ጀመረ። 19  በዚህ ጊዜ አለቆቹ በሙሉ መላውን ማኅበረሰብ እንዲህ አሉ፦ “በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ስም ስለማልንላቸው ጉዳት ልናደርስባቸው አንችልም። 20  እንግዲህ የምናደርገው ነገር ቢኖር በማልንላቸው መሐላ የተነሳ ቁጣ እንዳይመጣብን በሕይወት እንዲኖሩ መተው ብቻ ነው።”+ 21  ከዚያም አለቆቹ “በሕይወት ይኑሩ፤ ሆኖም ለማኅበረሰቡ በሙሉ እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች ይሁኑ” አሉ። አለቆቹም ይህንኑ ቃል ገቡላቸው። 22  ኢያሱም እነሱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የምትኖሩት እዚሁ አጠገባችን ሆኖ ሳለ ‘የምንኖረው ከእናንተ በጣም ርቆ በሚገኝ ቦታ ነው’ በማለት ያታለላችሁን ለምንድን ነው?+ 23  ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ የተረገማችሁ ናችሁ፤+ ለአምላኬም ቤት እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች በመሆን ምንጊዜም እንደ ባሪያ ታገለግላላችሁ።” 24  እነሱም መልሰው ኢያሱን እንዲህ አሉት፦ “ይህን ያደረግነው አምላክህ ይሖዋ አገልጋዩን ሙሴን ምድሪቱን በሙሉ ለእናንተ እንዲሰጣችሁና ነዋሪዎቿን በሙሉ ከፊታችሁ እንዲያጠፋላችሁ አዞት እንደነበር ለእኛ ለአገልጋዮችህ በግልጽ ስለተነገረን ነው።+ ስለሆነም በእናንተ የተነሳ ለሕይወታችን* በጣም ፈራን፤+ ይህን ያደረግነው በዚህ ምክንያት ነው።+ 25  ይኸው አሁን በእጅህ ነን። መልካምና ትክክል መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግብን።” 26  እሱም እንዲሁ አደረገባቸው፤ ከእስራኤላውያን እጅ አዳናቸው፤ እነሱም አልገደሏቸውም። 27  ሆኖም በዚያን ዕለት ኢያሱ አምላክ በሚመርጠው ስፍራ+ ለማኅበረሰቡና ለይሖዋ መሠዊያ እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች አደረጋቸው፤+ እነሱም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ያደርጋሉ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ሜድትራንያንን ያመለክታል።
ወይም “ባሪያዎች።”
በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።
ወይም “ጥቂት ወስደው መረመሩ።”
ወይም “ለነፍሳችን።”