ኢዮብ 10:1-22
10 “ሕይወቴን ተጸየፍኳት።*+
አንዳች ሳላስቀር ብሶቴን አሰማለሁ።
በታላቅ ምሬት* እናገራለሁ!
2 አምላክን እንዲህ እለዋለሁ፦ ‘በደለኛ ነህ አትበለኝ።
ከእኔ ጋር የምትሟገተው ለምን እንደሆነ ንገረኝ።
3 በክፉዎች ዕቅድ ደስ እየተሰኘህ፣የእጆችህን ሥራ መጨቆንህና መናቅህምን ይጠቅምሃል?+
4 ዓይንህ የሥጋ ለባሽ ዓይን ነው?ወይስ የምታየው ሟች የሆነ ሰው በሚያይበት መንገድ ነው?
5 ዘመንህ እንደ ሟች ሰዎች ዘመን ነው?ወይስ ዕድሜህ እንደ ሰው ዘመን ነው?+
6 ታዲያ በደልን የምትፈላልግብኝ፣ኃጢአቴንስ የምትከታተለው ለምንድን ነው?+
7 በደለኛ እንዳልሆንኩ ታውቃለህ፤+ደግሞም ማንም ከእጅህ ሊያስጥለኝ አይችልም።+
8 የገዛ እጆችህ ቀረጹኝ፤ ደግሞም ሠሩኝ፤+አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ልታጠፋኝ ነው።
9 ከሸክላ እንደሠራኸኝ እባክህ አስታውስ፤+አሁን ግን ወደ አፈር ትመልሰኛለህ።+
10 እንደ ወተት አላፈሰስከኝም?እንደ እርጎስ አላረጋኸኝም?
11 ቆዳና ሥጋ አለበስከኝ፤በአጥንትና በጅማት አያይዘህ ሠራኸኝ።+
12 ሕይወት ሰጠኸኝ፤ ታማኝ ፍቅርም አሳየኸኝ፤መንፈሴን* በእንክብካቤ ጠበቅክ።+
13 ሆኖም እነዚህን ነገሮች በስውር ለማድረግ አሰብክ።*
እነዚህ ነገሮች ከአንተ እንደመጡ አውቃለሁ።
14 ኃጢአት ብሠራ ትመለከተኛለህ፤+ከበደሌም ነፃ አታደርገኝም።
15 በደለኛ ከሆንኩ ወዮልኝ!
ንጹሕ ብሆንም እንኳ ራሴን ቀና ማድረግ አልችልም፤+ውርደትና ጉስቁልና በዝቶብኛልና።+
16 ራሴን ቀና ባደርግ እንደ አንበሳ ታድነኛለህ፤+ዳግመኛም በእኔ ላይ ኃይልህን ታሳያለህ።
17 አዳዲስ ምሥክሮችን በእኔ ላይ ታቆማለህ፤ቁጣህንም በእኔ ላይ ታበዛለህ፤በመከራ ላይ መከራ ተደራርቦብኛል።
18 ታዲያ ከማህፀን ለምን አወጣኸኝ?+
ምነው የሰው ዓይን ሳያየኝ በሞትኩ ኖሮ!
19 እንዳልተፈጠርኩ በሆንኩ ነበር!በቀጥታ ከማህፀን ወደ መቃብር በተወሰድኩ ነበር!’
20 የሕይወት ዘመኔ ጥቂት አይደለም?+ እስቲ ተወት ያድርገኝ፤ትንሽ ፋታ እንዳገኝ* ዓይኑን ከእኔ ላይ ያንሳ፤+
21 ወደማልመለስበት ስፍራ፣+ወደ ድቅድቅ ጨለማ* ምድር በቅርቡ እሄዳለሁ፤+
22 በጨለማ ወደተዋጠ፣ ፅልማሞት ወዳጠላበትናዝብርቅ ወደሰፈነበት፣ብርሃኑ እንኳ እንደ ጨለማ ወደሆነበት ምድር እሄዳለሁ።”