ኢዮብ 11:1-20
11 ናአማታዊው ሶፋር+ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2 “ይህ ሁሉ ቃል መልስ ሳይሰጠው ሊታለፍ ይገባል?ወይስ ብዙ ማውራት አንድን ሰው ትክክለኛ ያደርገዋል?*
3 ከንቱ ንግግርህ ሰዎችን ዝም ያሰኛል?
ስታፌዝስ የሚገሥጽህ የለም?+
4 ‘ትምህርቴ የጠራ ነው፤+በፊትህም ንጹሕ ነኝ’ ትላለህና።+
5 ምነው አምላክ በተናገረህ!ከንፈሩንም በአንተ ላይ በከፈተ!+
6 በዚያን ጊዜ የጥበብን ሚስጥር ይገልጥልሃል፤ጥበብ* ፈርጀ ብዙ ናትና።
ያን ጊዜ፣ የሠራሃቸውን አንዳንድ በደሎች አምላክ እንደረሳልህ ትገነዘባለህ።
7 የአምላክን ጥልቅ ነገሮች መርምረህ ልትደርስባቸው ትችላለህ?ወይስ ሁሉን ቻይ ስለሆነው አምላክ ሁሉንም ነገር መርምረህ ልትደርስበት* ትችላለህ?
8 ጥበብ ከሰማይ ይልቅ ከፍ ትላለች። አንተ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
ከመቃብርም* ይልቅ ጥልቅ ነች። አንተ ምን ልታውቅ ትችላለህ?
9 ከምድር ይልቅ ትረዝማለች፤ከባሕርም ይልቅ ትሰፋለች።
10 እሱ በሚያልፍበት ጊዜ አንድን ሰው ይዞ ለፍርድ ካቀረበ፣ማን ሊቃወመው ይችላል?
11 አታላይ ሰዎችን ያውቃልና።
እሱ ክፉ ነገር ሲያይ ትኩረት አይሰጥም?
12 የዱር አህያ ሰው መውለድ ቢችል፣*ያን ጊዜ አእምሮ የሌለው ሰው ማስተዋል ያገኛል።
13 ምነው ልብህን ብታዘጋጅ፣እጆችህንም ወደ እሱ ብትዘረጋ!
14 እጅህ መጥፎ ነገር የሚሠራ ከሆነ አርቀው፤በድንኳኖችህም ውስጥ ክፋት አይኑር።
15 በዚያን ጊዜ ያለኀፍረት ፊትህን ቀና ታደርጋለህ፤ምንም ሳትፈራ ጸንተህ ትቆማለህ።
16 ያን ጊዜ ችግርህን ትረሳለህና፤አልፎህ እንደሄደ ውኃ አድርገህ ታስበዋለህ።
17 ሕይወትህ ከቀትር ይልቅ ብሩህ ይሆናል፤ጨለማውም እንኳ እንደ ንጋት ይሆናል።
18 ተስፋ ስላለ ልበ ሙሉ ትሆናለህ፤ዙሪያህንም ትመለከታለህ፤ ያለስጋትም ትተኛለህ።
19 የሚያስፈራህ ሳይኖር ትተኛለህ፤ብዙ ሰዎችም የአንተን ሞገስ ለማግኘት ይሻሉ።
20 የክፉዎች ዓይን ግን ይደክማል፤የሚሸሹበት ቦታም አያገኙም፤ያላቸው ብቸኛ ተስፋ ሞት* ነው።”+