ኢዮብ 13:1-28

  • ኢዮብ መልስ መስጠቱን ቀጠለ (1-28)

    • ‘አምላክን ባነጋግር እመርጣለሁ’ (3)

    • “ሁላችሁም የማትረቡ ሐኪሞች ናችሁ” (4)

    • “ትክክል እንደሆንኩ አውቃለሁ” (18)

    • አምላክ እንደ ጠላት የቆጠረው ለምን እንደሆነ ጠየቀ (24)

13  “አዎ፣ ዓይኔ ይህን ሁሉ አይታለች፤ጆሮዬም ሰምታ አስተውላለች።   እናንተ የምታውቁትን እኔም አውቃለሁ፤ከእናንተ አላንስም።   እኔ በበኩሌ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ራሱን ባነጋግር እመርጣለሁ፤ከአምላክ ጋር መሟገት እፈልጋለሁ።+   እናንተ ግን በውሸት ስሜን እያጠፋችሁ ነው፤ሁላችሁም የማትረቡ ሐኪሞች ናችሁ።+   ምነው ዝም ብትሉ!ጥበበኛ መሆናችሁ በዚህ ይታወቅ ነበር።+   እስቲ የመከራከሪያ ሐሳቤን ስሙ፤የከንፈሬንም አቤቱታ አዳምጡ።   ከአምላክ ጎን ቆማችሁ አግባብ ያልሆነ ነገር ታወራላችሁ?ለእሱ ብላችሁስ የማታለያ ቃል ትናገራላችሁ?   ከእሱ ጎን ትቆማላችሁ?*ወይስ ለእውነተኛው አምላክ ትሟገታላችሁ?   እሱ ቢመረምራችሁ መልካም ይሆንላችኋል?+ ሟች የሆነውን ሰው እንደምታሞኙ እሱን ታሞኛላችሁ? 10  በስውር አድልዎ ለማድረግ ብትሞክሩ፣እሱ በእርግጥ ይገሥጻችኋል።+ 11  ክብሩ ሽብር አይለቅባችሁም?የእሱ ፍርሃትስ አይወድቅባችሁም? 12  ጥበብ የተንጸባረቀባቸው* አባባሎቻችሁ ከንቱ ምሳሌዎች* ናቸው፤መከላከያዎቻችሁ* ከሸክላ እንደተሠሩ ጋሻዎች ተሰባሪ ናቸው። 13  እኔ እንድናገር በፊቴ ዝም በሉ። ከዚያ በኋላ የመጣው ይምጣብኝ! 14  ራሴን ለምን ለአደጋ አጋልጣለሁ?*ሕይወቴንስ* ለምን በእጄ እይዛለሁ? 15  ቢገድለኝ እንኳ እሱን በተስፋ እጠባበቃለሁ፤+በፊቱ ጉዳዬን አቅርቤ እከራከራለሁ።* 16  በዚህ ጊዜ እሱ አዳኜ ይሆናል፤+አምላክ የለሽ* ሰው ፈጽሞ ፊቱ አይቀርብምና።+ 17  ቃሌን በጥሞና ስሙ፤የምናገረውንም ነገር ልብ ብላችሁ አድምጡ። 18  እንግዲህ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ፤ትክክል እንደሆንኩ አውቃለሁ። 19  ከእኔ ጋር የሚሟገት ማን ነው? ዝም ብል እሞታለሁ!* 20  አምላክ ሆይ፣ ከአንተ ሁለት ነገሮች ብቻ እሻለሁ፤*በዚያን ጊዜ ራሴን ከፊትህ አልሰውርም፦ 21  ከባዱን እጅህን ከእኔ አርቅ፤አስፈሪነትህም አያስደንግጠኝ።+ 22  ጥራኝና ልመልስልህ፤አለዚያ እኔ ልናገር፤ አንተም መልስ ስጠኝ። 23  የሠራሁት በደልና ኃጢአት ምንድን ነው? መተላለፌንና ኃጢአቴን አሳውቀኝ። 24  ፊትህን የምትሰውረውና+እንደ ጠላትህ የምትቆጥረኝ ለምንድን ነው?+ 25  ነፋስ የወሰደውን ቅጠል ለማስፈራራት ትሞክራለህ?ወይስ የደረቀውን ገለባ ታሳድዳለህ? 26  ከባድ ክሶችን ትመዘግብብኛለህ፤በወጣትነቴ ለሠራኋቸው ኃጢአቶች መልስ እንድሰጥ ታደርገኛለህ። 27  እግሮቼን በእግር ግንድ አስረሃል፤መንገዴን ሁሉ ትመረምራለህ፤ዱካዬንም ሁሉ በዓይነ ቁራኛ ትከታተላለህ። 28  በመሆኑም ሰው* እንደበሰበሰ ነገር፣ብልም እንደበላው ልብስ እያለቀ ይሄዳል።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለእሱ ታደላላችሁ?”
ወይም “የማይረሱ።”
ቃል በቃል “የአመድ ምሳሌዎች።”
ቃል በቃል “የጋሻ ጉብጉባቶቻችሁ።”
ወይም “ነፍሴንስ።”
ቃል በቃል “ሥጋዬን ለምን በጥርሴ እሸከማለሁ?”
ወይም “ስለ መንገዴ እሟገታለሁ።”
ወይም “ከሃዲ።”
“መሟገት የሚችል ካለ ዝም ብዬ ሞቴን እጠብቃለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ሁለት ነገሮች ብቻ አታድርግብኝ።”
ቃል በቃል “እሱ።” ኢዮብን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።