ኢዮብ 16:1-22

  • ኢዮብ የሰጠው መልስ (1-22)

    • “ሁላችሁም የምታስጨንቁ አጽናኞች ናችሁ!” (2)

    • አምላክ እሱን ዒላማ እንዳደረገው ተናገረ (12)

16  ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦   “ከዚህ በፊት እንዲህ ያሉ ብዙ ነገሮች ሰምቻለሁ። ሁላችሁም የምታስጨንቁ አጽናኞች ናችሁ!+   ከንቱ* ቃላት ማብቂያ የላቸውም? እንዲህ ብለህ እንድትመልስ ያነሳሳህ ምንድን ነው?   እኔም እንደ እናንተ መናገር እችል ነበር። እናንተ በእኔ ቦታ ብትሆኑ ኖሮ፣*አሳማኝ በሆነ መንገድ ልናገራችሁ እችል ነበር፤በእናንተም ላይ ራሴን መነቅነቅ እችል ነበር።+   እንዲህ ከማድረግ ይልቅ በአፌ ቃል አበረታችሁ ነበር፤የከንፈሮቼም ማጽናኛ ባሳረፋችሁ ነበር።+   ብናገር ከሥቃዬ አልገላገልም፤+ዝም ብልስ ሥቃዬ ምን ያህል ይቀንስልኛል?   አሁን ግን አምላክ እንድዝል አድርጎኛል፤+መላ ቤተሰቤን* አጥፍቷል።   ደግሞም ያዝከኝ፤ ይህም ምሥክር ሆኖብኛል፤በመሆኑም ክሳቴ ተነስቶ በፊቴ ይመሠክራል።   ቁጣው ቦጫጨቀኝ፤ በጥላቻ ተመለከተኝ።+ ጥርሱን አፋጨብኝ። ባላጋራዬ በዓይኑ ወጋኝ።+ 10  እነሱ አፋቸውን በሰፊው ከፈቱብኝ፤+በንቀትም ጉንጬን አጮሉኝ፤ብዙ ሆነው በእኔ ላይ ተሰበሰቡ።+ 11  አምላክ ለልጆች አሳልፎ ሰጠኝ፤በክፉዎችም እጅ ላይ ገፍትሮ ጣለኝ።+ 12  ያለምንም ችግር እኖር ነበር፤ እሱ ግን ሰባበረኝ፤+ማጅራቴን ይዞ አደቀቀኝ፤ከዚያም ዒላማው አደረገኝ። 13  ቀስተኞቹ ከበቡኝ፤+ኩላሊቴን ወጋ፤+ ምንም ርኅራኄ አላሳየኝም፤ሐሞቴን መሬት ላይ አፈሰሰ። 14  እንደ ግንብ ሰንጥቆ ሰነጣጥቆ አፈራረሰኝ፤እንደ ተዋጊ ተንደርድሮ መጣብኝ። 15  ቆዳዬን ለመሸፈን ማቅ ሰፍቻለሁ፤+ክብሬንም* አፈር ውስጥ ቀብሬአለሁ።+ 16  ከለቅሶ የተነሳ ፊቴ ቀልቷል፤+ድቅድቅ ጨለማም* በዓይኖቼ ቆብ ላይ አጥልቷል፤ 17  ይሁንና እጆቼ ምንም ዓመፅ አልሠሩም፤ጸሎቴም ንጹሕ ነው። 18  ምድር ሆይ፣ ደሜን አትሸፍኚ!+ ጩኸቴም ማረፊያ ስፍራ አያግኝ! 19  አሁንም እንኳ ምሥክሬ በሰማያት አለ፤ስለ እኔ መመሥከር የሚችል በከፍታ ቦታዎች ላይ ይገኛል። 20  ጓደኞቼ በእኔ ላይ ያፌዛሉ፤+ዓይኔም ወደ አምላክ ያነባል።*+ 21  በሰውና በባልንጀራው መካከል የሚዳኝ እንደሚኖር፣በሰውና በአምላክ መካከልም የሚዳኝ ይኑር።+ 22  የሚቀሩት ዓመታት ጥቂት ናቸውና፤እኔም በማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እንደ ነፋስ ያሉ።”
ወይም “የእናንተ ነፍስ በእኔ ነፍስ ቦታ ብትሆን ኖሮ።”
ወይም “ከእኔ ጋር የሚሰበሰቡትን።”
ወይም “ብርታቴንም።” ቃል በቃል “ቀንዴንም።”
ወይም “የሞት ጥላም።”
“እንቅልፍ አጥቶ ይመለከታል” ማለትም ሊሆን ይችላል።