ኢዮብ 19:1-29
19 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2 “እናንተ ሰዎች ነፍሴን የምታበሳጯት፣*+በቃላት የምትደቁሱኝስ+ እስከ መቼ ነው?
3 ይኸው አሥር ጊዜ ገሠጻችሁኝ፤*ከባድ በደል ስትፈጽሙብኝ አላፈራችሁም።+
4 ስህተት ብፈጽምም እንኳ፣የሠራሁት ስህተት ከእኔ ጋር ይኖራል።
5 በእኔ ላይ የደረሰው ነቀፋ ተገቢ እንደሆነ አድርጋችሁ በመከራከር፣በእኔ ላይ ራሳችሁን ከፍ ከፍ ብታደርጉ፣
6 ያሳተኝ አምላክ እንደሆነ እወቁ፤በማጥመጃ መረቡም ይዞኛል።
7 እነሆ ‘ግፍ ተፈጸመብኝ!’ ብዬ ብጮኽም መልስ አላገኘሁም፤+እርዳታ ለማግኘት ብጣራም ፍትሕ የለም።+
8 መንገዴን በድንጋይ ግንብ ዘጋ፤ እኔም ማለፍ አልቻልኩም፤ጎዳናዬንም በጨለማ ጋረደ።+
9 ክብሬን ገፎኛል፤አክሊሉንም ከራሴ ላይ አንስቷል።
10 እስክጠፋ ድረስ በሁሉም አቅጣጫ አፈራረሰኝ፤ተስፋዬን እንደ ዛፍ ነቀለው።
11 ቁጣው በእኔ ላይ ነደደ፤እንደ ጠላቱም ቆጠረኝ።+
12 ሠራዊቱ በአንድነት መጥተው ከበቡኝ፤በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ።
13 የገዛ ወንድሞቼን ከእኔ አራቀ፤የሚያውቁኝም ሰዎች ጥለውኝ ሄዱ።+
14 የቅርብ ወዳጆቼ ትተውኛል፤*በደንብ የማውቃቸውም ሰዎች ረሱኝ።+
15 በቤቴ ያሉ እንግዶችና+ ሴቶች ባሪያዎቼ እንደ መጤ ቆጠሩኝ፤እንደ ባዕድ አገር ሰው ተመለከቱኝ።
16 አገልጋዬን ጠራሁት፤ እሱ ግን አልመለሰልኝም፤እንዲራራልኝ በአንደበቴ ለመንኩት።
17 ሚስቴ ትንፋሼን እንኳ ተጸየፈችው፤+ለገዛ ወንድሞቼም* መጥፎ ጠረን ሆንኩባቸው።
18 ትናንሽ ልጆች እንኳ ናቁኝ፤ስነሳ በእኔ ላይ ያላግጣሉ።
19 የቅርብ ወዳጆቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፤+የምወዳቸውም ሰዎች በእኔ ላይ ተነሱ።+
20 አጥንቶቼ ከቆዳዬና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ፤+ከሞት ለጥቂት* ተረፍኩ።
21 ወዳጆቼ ሆይ፣ ማሩኝ፤ እባካችሁ ማሩኝ፤የአምላክ እጅ መታኛለችና።+
22 አምላክ እንዳሳደደኝ የምታሳድዱኝ ለምንድን ነው?+ያለፋታ የምታጠቁኝስ* ለምንድን ነው?+
23 ምነው ቃሌ በተጻፈ!ምነው በመጽሐፍ ላይ በሰፈረ!
24 ምነው በብረት ብዕርና በእርሳስ፣በዓለቱ ላይ ለዘላለም በተቀረጸ!
25 የሚዋጀኝ*+ ሕያው እንደሆነ በሚገባ አውቃለሁና፤ከጊዜ በኋላ መጥቶ በምድር ላይ ይቆማል።
26 ቆዳዬ በዚህ መንገድ ቢጠፋም፣ገና በሥጋ እያለሁ አምላክን አየዋለሁ፤
27 እኔ ራሴ እሱን እመለከተዋለሁ፤የሌላ ሰው ዓይን ሳይሆን የገዛ ዓይኖቼ ያዩታል።+
ይሁንና በውስጤ እንደዛልኩ ይሰማኛል!*
28 የችግሩ መንስኤ እኔ ጋ እያለ፣
‘የምናሳድደው እንዴት ነው?’ ትላላችሁና።+
29 እናንተ ራሳችሁ ሰይፉን ፍሩ፤+ሰይፉ በበደል ላይ ቅጣት ያመጣልና፤ፈራጅ መኖሩን ልታውቁ ይገባል።”+