ኢዮብ 22:1-30

  • የኤሊፋዝ ሦስተኛ ዙር ንግግር (1-30)

    • “ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል?” (2, 3)

    • ኢዮብን በስግብግብነትና ፍትሕ በማዛባት ወነጀለው (6-9)

    • ‘ወደ አምላክ ብትመለስ ትታደሳለህ’ (23)

22  ቴማናዊው ኤሊፋዝ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦   “ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል? ማስተዋል ያለውስ ሰው ምን ይፈይድለታል?+   ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አንተ ጻድቅ መሆንህ ግድ ይሰጠዋል?*ወይስ በንጹሕ አቋም* መመላለስህ እሱን ይጠቅመዋል?+   አክብሮት* ስላሳየህ ይቀጣሃል?ደግሞስ ፍርድ ቤት ያቀርብሃል?   ይህን የሚያደርገው የሠራኸው ክፋት ታላቅ ስለሆነ፣በደልህም ማብቂያ ስለሌለው አይደለም?+   ያላንዳች ምክንያት ከወንድሞችህ ላይ መያዣ ትወስዳለህና፤ሰዎችንም ልብሳቸውን ገፈህ ራቁታቸውን ታስቀራለህ።*+   ለደከመው ሰው የሚጠጣ ውኃ አልሰጠህም፤የራበውንም ሰው ምግብ ነፍገሃል።+   ምድሪቱ የኃያል ሰው ንብረት ነች፤+የታደለም ሰው ይኖርባታል።   አንተ ግን መበለቶችን ባዶ እጃቸውን ሰደሃል፤አባት የሌላቸውንም ልጆች* ክንድ ሰብረሃል። 10  ከዚህም የተነሳ በወጥመድ ተከበሃል፤+ድንገተኛ ሽብርም ያስደነግጥሃል፤ 11  በመሆኑም ማየት እንዳትችል ጨለማ ውጦሃል፤ጎርፍም አጥለቅልቆሃል። 12  አምላክ የሚኖረው ከፍ ባለው ሰማይ አይደለም? በሰማያት ያሉ ከዋክብትም ሁሉ ምን ያህል ከፍ ያሉ እንደሆኑ ተመልከት። 13  አንተ ግን እንዲህ ብለሃል፦ ‘አምላክ ምን ያውቃል? በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሊፈርድ ይችላል? 14  በሰማይ ክበብ ላይ ሲራመድ፣ማየት እንዳይችል ደመናት ይጋርዱታል።’ 15  ክፉ ሰዎች የሄዱበትን፣የጥንቱን መንገድ ተከትለህ ትሄዳለህ? 16  እነሱ ጊዜያቸው ሳይደርስ ሞት ነጥቋቸዋል፤*መሠረታቸው በጎርፍ* ተጠራርጎ ሄዷል።+ 17  እውነተኛውን አምላክ ‘አትድረስብን!’ ደግሞም ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በእኛ ላይ ምን ሊያደርግ ይችላል?’ ይላሉ። 18  ሆኖም ቤቶቻቸውን በመልካም ነገሮች የሞላው እሱ ነው። (እንዲህ ዓይነቱ ክፉ ሐሳብ ከእኔ የራቀ ነው።) 19  ጻድቅ ይህን አይቶ ይደሰታል፤ንጹሕ የሆነውም ሰው ይሳለቅባቸዋል፤ እንዲህም ይላቸዋል፦ 20  ‘ተቃዋሚዎቻችን ጠፍተዋል፤ከእነሱ የቀረውንም እሳት ይበላዋል።’ 21  እሱን እወቅ፤ ከእሱም ጋር ሰላም ይኖርሃል፤እንዲህ ካደረግክ መልካም ነገሮች ታገኛለህ። 22  ሕጉን ከአፉ ተቀበል፤ቃሉንም በልብህ አኑር።+ 23  ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ብትመለስ ትታደሳለህ፤+ክፋትን ከድንኳንህ ብታርቅ፣ 24  ወርቅህን* አፈር ውስጥ፣የኦፊርንም ወርቅ+ ዓለታማ ሸለቆ* ውስጥ ብትጥል፣ 25  ያን ጊዜ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ወርቅና*ጥራት ያለው ብር ይሆንልሃል። 26  በዚህ ጊዜ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ደስ ትሰኛለህና፤ፊትህንም ወደ አምላክ ቀና ታደርጋለህ። 27  ትለምነዋለህ፤ እሱም ይሰማሃል፤ስእለትህንም ትፈጽማለህ። 28  ለማድረግ ያሰብከው ነገር ሁሉ ይሳካልሃል፤በመንገድህም ላይ ብርሃን ይበራል። 29  በእብሪት ስትናገር ትዋረዳለህና፤ትሑት የሆነውን* ግን ያድነዋል። 30  እሱ ንጹሕ የሆኑትን ያድናል፤ስለዚህ እጅህ ንጹሕ ከሆነ በእርግጥ ትድናለህ።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ያስደስተዋል?”
ኢዮብ 2:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “አክብሮታዊ ፍርሃት።”
ቃል በቃል “የተራቆቱትን ሰዎች ልብስ ትገፋለህ።”
ወይም “ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችን።”
ወይም “ሕይወታቸው በአጭሩ ተቀጭቷል።”
ቃል በቃል “በወንዝ።”
ወይም “ያልተጣራ ወርቅህን።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “ያልተጣራ ወርቅና።”
ወይም “ቀና ብሎ የማያየውን።”