ኢዮብ 23:1-17
23 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2 “ዛሬም እንኳ ብሶት ማሰማቴን አላቆምም፤*+ከመቃተቴ የተነሳ ኃይሌ ተሟጠጠ።
3 አምላክን የት እንደማገኘው ባወቅኩ!+
ወደሚኖርበት ስፍራ እሄድ ነበር።+
4 ጉዳዬን በፊቱ አቀርብ፣አፌንም በሙግት እሞላ ነበር፤
5 እሱ እንዴት እንደሚመልስልኝ ባወቅኩ፣የሚለኝንም ባስተዋልኩ ነበር።
6 ታላቅ ኃይሉን ተጠቅሞ ከእኔ ጋር ይሟገት ይሆን?
በፍጹም! ይልቁንም ያዳምጠኛል።+
7 ያን ጊዜ ቅን የሆነው ሰው ከአምላክ ጋር ስምምነት መፍጠር ይችላል፤ፈራጄም እኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በነፃ ይለቀኛል።
8 ይሁንና ወደ ምሥራቅ ብሄድ እሱ በዚያ የለም፤ተመልሼ ብመጣም ላገኘው አልችልም።
9 በስተ ግራ ሆኖ ሲሠራ ላየው አልችልም፤ከዚያም ወደ ቀኝ ይዞራል፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን አላየውም።
10 እሱ ግን የሄድኩበትን መንገድ ያውቃል።+
ከፈተነኝ በኋላ እንደጠራ ወርቅ እሆናለሁ።+
11 እግሬ የእሱን ዱካ በጥብቅ ተከትሏል፤ምንም ፈቀቅ ሳልል መንገዱን ጠብቄአለሁ።+
12 ከከንፈሩ ትእዛዝ አልራቅኩም።
የተናገረውን ቃል ከሚጠበቅብኝ* በላይ ከፍ አድርጌ ተመልክቻለሁ።+
13 ቆርጦ ከተነሳ ማን ሊቃወመው ይችላል?+
እሱ አንድ ነገር ማድረግ ከፈለገ* ከማድረግ ወደኋላ አይልም።+
14 በእኔ ላይ የተወሰነውን* ሙሉ በሙሉ ይፈጽማልና፤እንደዚህ ያሉ ብዙ ነገሮችም በእሱ ዘንድ አሉ።
15 በእሱ የተነሳ የተጨነቅኩት ለዚህ ነው፤ስለ እሱ ሳስብ ይበልጥ ፍርሃት ያድርብኛል።
16 አምላክ ራሱ ፈሪ አድርጎኛል፤ሁሉን ቻይ የሆነውም አምላክ አስደንግጦኛል።
17 ይሁን እንጂ ጨለማውም ሆነፊቴን የሸፈነው ድቅድቅ ጨለማ ዝም አላሰኘኝም።