ኢዮብ 29:1-25
29 ኢዮብ ንግግሩን* በመቀጠል እንዲህ አለ፦
2 “የቀድሞዎቹን ወራት፣አምላክ ለእኔ ጥበቃ ያደርግ የነበረበትን ዘመን ተመኘሁ!
3 ያን ጊዜ መብራቱን በራሴ ላይ ያበራ፣በእሱም ብርሃን፣ በጨለማ ውስጥ እሄድ ነበር፤+
4 ያኔ የወጣትነት ብርታት ነበረኝ፤አምላክ የቅርብ ወዳጄ ሆኖ በድንኳኔ ይገኝ ነበር፤+
5 ሁሉን ቻይ አምላክ ከእኔ ጋር ነበር፤ልጆቼም* በዙሪያዬ ነበሩ፤
6 መንገዴ በቅቤ የራሰ ነበር፤ዓለቱም ዘይት ያንዶለዱልልኝ ነበር።+
7 ወደ ከተማዋ በር እሄድ፣+በአደባባይዋም እቀመጥ ነበር፤+
8 ወጣቶች ሲያዩኝ መንገድ ይለቁልኝ፣*ሽማግሌዎችም እንኳ ተነስተው ይቆሙ ነበር።+
9 መኳንንት ከመናገር ይቆጠቡ፣እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ይጭኑ ነበር።
10 የታላላቆቹ ሰዎች ድምፅ አይሰማም ነበር፤ምላሳቸውም ከላንቃቸው ጋር ይጣበቅ ነበር።
11 ስናገር የሰማ ሁሉ ያሞግሰኝ፣ያዩኝ ሰዎችም ይመሠክሩልኝ ነበር።
12 ለእርዳታ የሚጮኸውን ድሃ፣አባት የሌለውን ልጅና ረዳት የሌለውን ሁሉ እታደግ ነበርና።+
13 ሊጠፋ ተቃርቦ የነበረው ይባርከኝ ነበር፤+የመበለቲቱንም ልብ ደስ አሰኝ ነበር።+
14 ጽድቅን እንደ ልብስ ለበስኩ፤የፍትሕ አቋሜ እንደ ቀሚስና* እንደ ጥምጥም ሆነልኝ።
15 ለዓይነ ስውሩ ዓይን፣ለአንካሳውም እግር ነበርኩ።
16 ለድሃው አባት ነበርኩ፤+የማላውቃቸውን ሰዎች ሙግት እመረምር ነበር።+
17 የክፉ አድራጊውን መንጋጋ እሰብር፣+አድኖ የያዘውንም ከጥርሱ አስጥል ነበር።
18 እንዲህ እል ነበር፦ ‘በገዛ ቤቴ* እሞታለሁ፤+የሕይወት ዘመኔም እንደ አሸዋ ይበዛል።
19 ሥሮቼ ወደ ውኃ ይዘረጋሉ፤ጠልም ሌሊቱን ሙሉ በቅርንጫፎቼ ላይ ያድራል።
20 ክብሬ ሁልጊዜ ይታደሳል፤በእጄም ያለው ደጋን ደጋግሞ ይወነጭፋል።’
21 ሰዎች በጉጉት ያዳምጡኝ፣ምክሬንም ጸጥ ብለው ይጠባበቁ ነበር።+
22 እኔ ከተናገርኩ በኋላ የሚጨምሩት ነገር አልነበረም፤ቃሌም በጆሯቸው ይንቆረቆር* ነበር።
23 ዝናብ እንደሚጠባበቁ ሰዎች እኔን ተጠባበቁ፤ቃሌንም እንደ በልግ ዝናብ+ ጠጡ።
24 በፈገግታ ባየኋቸው ጊዜ ማመን አቃታቸው፤የፊቴ ብርሃን ያጽናናቸው ነበር።*
25 እንደ መሪያቸው ሆኜ አመራር ሰጠኋቸው፤በወታደሮቹ መካከል እንዳለ ንጉሥ፣+ሐዘንተኞችንም እንደሚያጽናና ሰው ሆኜ ኖርኩ።+