ኢዮብ 30:1-31

  • ኢዮብ የደረሰበትን ሁኔታ ገለጸ (1-31)

    • የማይረቡ ሰዎች አፌዙበት (1-15)

    • አምላክ ምንም እየረዳው እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር (20, 21)

    • ‘ቆዳዬ ጠቆረ’ (30)

30  “አሁን ግን ከእኔ በዕድሜ የሚያንሱ፣በእኔ ላይ ይስቃሉ፤+አባቶቻቸው መንጋዬን ከሚጠብቁ ውሾች ጋር እንዲሆኑፈቃደኛ አልነበርኩም።   የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይፈይድልኝ ነበር? እነሱ ጉልበት ከድቷቸዋል።   ከችጋርና ከረሃብ የተነሳ ዝለዋል፤በወደመ እና ወና በሆነ ደረቅ ምድርያገኟትን ነገር ያላምጣሉ።   በቁጥቋጦዎች አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚል ተክል ይሰበስባሉ፤ምግባቸው የክትክታ ዛፍ ሥር ነው።   ከማኅበረሰቡ ተባረዋል፤+ሰዎችም ሌባ ላይ እንደሚጮኹ ይጮኹባቸዋል።   በሸለቆዎች* ተዳፋት ላይ፣መሬት ላይ ባሉ ጉድጓዶች ውስጥና በዓለቶች መካከል ይኖራሉ።   ከቁጥቋጦዎች ውስጥ ይጮኻሉ፤በሳማዎችም መካከል ይከማቻሉ።   ማመዛዘን የጎደላቸውና የአልባሌ ሰዎች ልጆች ናቸው፤ከምድሪቱ ላይ ተባረዋል።*   አሁን ግን በዘፈኖቻቸው ሳይቀር ይሳለቁብኛል፤+የእነሱ መሳለቂያ* ሆኛለሁ።+ 10  ይጸየፉኛል፤ ከእኔም ርቀዋል፤+በፊቴ ከመትፋት ወደኋላ አይሉም።+ 11  ምክንያቱም አምላክ ትጥቅ አስፈትቶኛል፤* ደግሞም አዋርዶኛል፤እነሱ በፊቴ እንዳሻቸው ይሆናሉ።* 12  በቀኜ በኩል እንደ አድመኛ ተነስተውብኛል፤እንድሸሽ አድርገውኛል፤በመንገዴም ላይ ለጥፋት የሚዳርግ መሰናክል አስቀምጠዋል። 13  መንገዶቼን ያፈርሳሉ፤መከራዬንም ያባብሳሉ፤+የሚገታቸውም የለም።* 14  ሰፊ ክፍተት ባለው ቅጥር እንደሚመጣ ሰው መጡ፤በፍርስራሹ መካከል እየገሰገሱ ገቡ። 15  በሽብር ተዋጥኩ፤ክብሬ በነፋስ እንደሚወሰድ ተወስዷል፤የመዳን ተስፋዬም እንደ ደመና እልም ብሎ ጠፍቷል። 16  አሁን ሕይወቴ* ከውስጤ ተሟጠጠች፤+የጉስቁልና ዘመን+ ያዘኝ። 17  ከባድ ሕመም በሌሊት አጥንቶቼን ይበሳል፤*+የሚመዘምዘኝ ሥቃይ እረፍት አይሰጠኝም።+ 18  ልብሴ በታላቅ ኃይል ተበላሸ፤*እንደ ልብሴ አንገትጌ አንቆ ያዘኝ። 19  አምላክ ጭቃ ውስጥ ጥሎኛል፤አፈርና አመድ ሆንኩ። 20  እርዳታ ለማግኘት ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አንተ ግን አትመልስልኝም፤+በፊትህ ቆምኩ፤ አንተ ግን ዝም ብለህ ታየኛለህ። 21  በጭካኔ በእኔ ላይ ተነሳህ፤+በእጅህ ብርታት አጠቃኸኝ። 22  ወደ ላይ አንስተህ በነፋስ ወሰድከኝ፤ከዚያም በአውሎ ነፋስ አንገላታኸኝ።* 23  በሕይወት ያለ ሁሉ ወደሚሰበሰብበት ቤት፣ወደ ሞት እንደምታወርደኝ አውቃለሁና። 24  ይሁንና የተሰበረ ሰው አደጋ ደርሶበት ለእርዳታ ሲጮኽ፣እጁን የሚያነሳበት ሰው አይኖርም።*+ 25  መከራ ላይ ለወደቁ ሰዎች* አላለቀስኩም? ለድሃውስ አላዘንኩም?*+ 26  መልካም ነገር በተስፋ ብጠባበቅም ክፉ ነገር ደረሰ፤ብርሃን ብጠባበቅም ጨለማ መጣ። 27  ውስጤ ያለማቋረጥ ተናወጠ፤የጉስቁልናም ዘመን መጣብኝ። 28  በሐዘን ተውጬ እመላለሳለሁ፤+ የፀሐይ ብርሃንም የለም። በጉባኤ መካከል ቆሜ እርዳታ ለማግኘት እጮኻለሁ። 29  የቀበሮዎች ወንድም፣የሰጎንም ሴቶች ልጆች ባልንጀራ ሆንኩ።+ 30  ቆዳዬ ጠቁሮ ተቀረፈ፤+ከሙቀቱ* የተነሳ አጥንቶቼ ነደዱ። 31  በገናዬ ለሐዘን ብቻ ዋለ፤ዋሽንቴም* ለለቅሶ ሆነ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በደረቅ ወንዞች።”
ቃል በቃል “ተገርፈው (ተባረዋል)።”
ቃል በቃል “ምሳሌ፤ መተረቻ።”
ቃል በቃል “የደጋኔን አውታር አላልቶብኛል።”
ወይም “ልጓሙን ይፈታሉ።”
“የሚረዳቸው ሳይኖር መከራዬን ያባብሳሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሴ።”
ቃል በቃል “በሌሊት አጥንቶቼ ተቦርቡረዋል።”
“የደረሰብኝ ከባድ መከራ ሰውነቴን አበላሸው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“በኃይል አላትመህ በታተንከኝ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በፍርስራሽ ክምር (ላይ እጁን የሚያነሳ አይኖርም)።”
ወይም “የመከራ ቀን ለገጠማቸው ሰዎች።”
ወይም “ነፍሴስ ለድሃው አላዘነችም?”
“ከትኩሳቱ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “እምቢልታዬም።”