ኢዮብ 33:1-33

  • ኤሊሁ፣ ኢዮብ ራሱን በማመጻደቁ ወቀሰው (1-33)

    • “ቤዛ አግኝቻለሁ!” (24)

    • ወደ ወጣትነቱ ዘመን ይመለስ (25)

33  “አሁን ግን ኢዮብ፣ እባክህ ቃሌን ስማ፤የምናገረውንም ሁሉ አዳምጥ።   እባክህ ልብ በል! አፌን እከፍታለሁ፤አንደበቴም* ይናገራል።   ቃሌ የልቤን ቅንነት ይገልጻል፤+ከንፈሮቼም የማውቀውን ነገር በቅንነት ይናገራሉ።   የአምላክ መንፈስ ሠራኝ፤+ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እስትንፋስም ሕይወት ሰጠኝ።+   የምትችል ከሆነ መልስልኝ፤የመከራከሪያ ሐሳብህን በፊቴ አቅርብ፤ ቦታህንም ያዝ።   እነሆ፣ በእውነተኛው አምላክ ፊት እኔም እንደ አንተው ነኝ፤እኔም የተሠራሁት ከሸክላ ነው።+   ስለዚህ እኔን ፈርተህ ልትሸበር አይገባም፤የማሳድርብህ ጫናም ሊደቁስህ አይገባም።   ይሁንና የተናገርከውን ሰምቻለሁ፤አዎ፣ እነዚህን ቃላት ስሰማ ቆይቻለሁ፦   ‘ከበደል ነፃ ነኝ፤+ንጹሕ ነኝ፤ ጥፋትም የለብኝም።+ 10  አምላክ ግን እኔን ለመቃወም ምክንያት ይፈልጋል፤እንደ ጠላቱ ይቆጥረኛል።+ 11  እግሬን በእግር ግንድ ያስራል፤መንገዴንም ሁሉ ይመረምራል።’+ 12  ሆኖም እንዲህ ማለትህ ትክክል ስላልሆነ እመልስልሃለሁ፦ አምላክ ሟች ከሆነው ሰው እጅግ ይበልጣል።+ 13  በአምላክ ላይ የምታጉረመርመው ለምንድን ነው?+ ለተናገርከው ሁሉ መልስ ስላልሰጠህ ነው?+ 14  አምላክ ከአንዴም ሁለቴ ይናገራል፤ይሁንና ማንም አያስተውለውም፤ 15  ሰዎች ከባድ እንቅልፍ ሲይዛቸው፣በአልጋቸውም ላይ ሆነው ሲያሸልቡ፣በሕልም፣ በሌሊትም ራእይ ይናገራል።+ 16  በዚያን ጊዜ ጆሯቸውን ይከፍታል፤+መመሪያውንም እንዲገነዘቡ ያደርጋል፤* 17  ይህም ሰውን ከስህተት ይመልስ ዘንድ፣+ደግሞም ሰውን ከኩራት ይጠብቅ ዘንድ ነው።+ 18  አምላክ ነፍሱን* ከጉድጓድ* ያድናል፤+ሕይወቱ በሰይፍ* እንዳይጠፋ ይታደገዋል። 19  ደግሞም ሰው በአልጋው ላይ ሳለ በሕመም፣እንዲሁም አጥንቶቹ በሚያስከትሉበት ፋታ የሌለው ሥቃይ ተግሣጽ ይቀበላል፤ 20  በመሆኑም ሁለመናው* መብል ይጸየፋል፤ምርጥ የሆነ ምግብም ይጠላል።*+ 21  ሥጋውም መንምኖ ይጠፋል፤ተሸፍነው የነበሩት አጥንቶቹም ያገጣሉ።* 22  ነፍሱ* ወደ ጉድጓድ፣*ሕይወቱም ሊያጠፏት ወደሚሹ ትቀርባለች። 23  ለሰው ትክክል የሆነውን ነገር የሚነግረውአንድ መልእክተኛ፣*ከሺዎች መካከል አንድ ጠበቃ ቢገኝለት፣ 24  ያን ጊዜ አምላክ ሞገስ ያሳየዋል፤ እንዲህም ይላል፦‘ወደ ጉድጓድ* ከመውረድ አድነው!+ ቤዛ አግኝቻለሁ!+ 25  በወጣትነቱ ጊዜ ከነበረው የበለጠ ሥጋው ይለምልም፤*+ብርቱ ወደነበረበት የወጣትነት ዘመኑም ይመለስ።’+ 26  አምላክን ይለምናል፤+ እሱም ይቀበለዋል፤በእልልታም የአምላክን ፊት ያያል፤ደግሞም አምላክ የራሱን ጽድቅ፣ ሟች ለሆነው ሰው ይመልስለታል። 27  ግለሰቡም ለሰዎች እንዲህ ይላል፦*‘ኃጢአት ሠርቻለሁ፤+ ትክክል የሆነውንም ነገር አጣምሜአለሁ፤ሆኖም የእጄን አላገኘሁም።* 28  እሱ ነፍሴን* ወደ ጉድጓድ* ከመውረድ ታድጓታል፤+ሕይወቴም ብርሃን ታያለች።’ 29  በእርግጥም አምላክ እነዚህን ነገሮች ሁሉ፣ከሁለቴም ሦስቴ ለሰው ያደርጋል፤ 30  ይኸውም የሕይወት ብርሃን ይበራለት ዘንድ፣እሱን ከጉድጓድ* ለመመለስ ነው።+ 31  ኢዮብ፣ ልብ ብለህ ስማ! ደግሞም አዳምጠኝ! ዝም በል፤ እኔም መናገሬን እቀጥላለሁ። 32  የምትለው ካለ መልስልኝ። ትክክለኛነትህ እንዲረጋገጥ ማድረግ ስለምፈልግ ተናገር። 33  የምትለው ነገር ከሌለ ግን ስማኝ፤ዝም በል፤ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።”

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ምላሴም ከላንቃዬ ጋር።”
ቃል በቃል “ማኅተም ያደርግባቸዋል።”
ወይም “ሕይወቱን።”
ወይም “ከመቃብር።”
ወይም “በመሣሪያ (በተወንጫፊ መሣሪያ)።”
ወይም “ነፍሱም ምርጥ የሆነ ምግብ ትጠላለች።”
ቃል በቃል “ሕይወቱ።”
ወይም “ይራቆታሉ።”
ወይም “ሕይወቱ።”
ወይም “መቃብር።”
ወይም “መልአክ።”
ወይም “ወደ መቃብር።”
ወይም “ጤናማ ይሁን።”
ቃል በቃል “(እንዲህ በማለት) ይዘምራል።”
“ደግሞም አልጠቀመኝም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሕይወቴን።”
ወይም “ወደ መቃብር።”
ወይም “ነፍሱን ከመቃብር።”