ኢዮብ 38:1-41

  • ይሖዋ፣ ሰው አነስተኛ ፍጡር መሆኑን ገለጸ (1-41)

    • ‘ምድር ስትፈጠር አንተ የት ነበርክ?’ (4-6)

    • የአምላክ ልጆች በደስታ እልል አሉ (7)

    • የተፈጥሮ ክስተቶችን በተመለከተ የቀረቡ ጥያቄዎች (8-32)

    • ‘ሰማያት የሚመሩባቸው ሕጎች’ (33)

38  ከዚያም ይሖዋ ከአውሎ ነፋስ ውስጥ ለኢዮብ መለሰለት፦+   “ሐሳቤን የሚሰውርናያለእውቀት የሚናገር ይህ ማን ነው?+   እስቲ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤እኔ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም ንገረኝ።   ምድርን በመሠረትኩ ጊዜ አንተ የት ነበርክ?+ ማስተዋል አለኝ የምትል ከሆነ ንገረኝ።   የምታውቅ ከሆነ፣ መለኪያዎቿን የወሰነ፣ወይስ መለኪያ ገመድ በላይዋ ላይ የዘረጋ ማን ነው?   የምድር ምሰሶዎች የተተከሉት ምን ላይ ነው?የማዕዘኗን ድንጋይ ያኖረስ ማን ነው?+   አጥቢያ ከዋክብት+ በአንድነት እልል ሲሉ፣የአምላክም ልጆች ሁሉ*+ በደስታ ሲጮኹ አንተ የት ነበርክ?   ባሕሩ ከማህፀን አፈትልኮ በወጣ ጊዜ፣በር የዘጋበት ማን ነው?+   ደመና ባለበስኩት ጊዜ፣በድቅድቅ ጨለማም በጠቀለልኩት ጊዜ፣ 10  በላዩም ድንበሬን በወሰንኩ ጊዜ፣መቀርቀሪያዎችና በሮች ባደረግኩለት ጊዜ፣+ 11  ደግሞም ‘እስከዚህ ድረስ መምጣት ትችላለህ፤ ከዚህ ግን አታልፍም፤የኩሩው ማዕበልህም ገደብ ይህ ነው’ ባልኩ ጊዜ+ አንተ የት ነበርክ? 12  ለመሆኑ ንጋትን አዘህ ታውቃለህ?ወይስ ጎህ ስፍራውን እንዲያውቅ አድርገሃል?+ 13  የማለዳ ብርሃን ወደ ምድር ዳርቻዎች እንዲሄድ፣ክፉዎችንም ከላይዋ እንዲያራግፍ ያዘዝከው አንተ ነህ?+ 14  ምድር ከማኅተም በታች እንዳለ የሸክላ ጭቃ ትለወጣለች፤ገጽታዎቿም እንደሚያምር ልብስ ጎልተው ይታያሉ። 15  የክፉዎች ብርሃን ግን ከእነሱ ተወስዷል፤ከፍ ያለው ክንዳቸውም ተሰብሯል። 16  ወደ ባሕሩ ምንጮች ወርደሃል?ወይስ ጥልቁን ውኃ መርምረሃል?+ 17  የሞት በሮች+ ተገልጠውልሃል?የድቅድቅ ጨለማንስ* በሮች አይተሃል?+ 18  ምድር ምን ያህል ሰፊ እንደሆነች አስተውለሃል?+ ይህን ሁሉ የምታውቅ ከሆነ ተናገር። 19  ብርሃን የሚኖረው በየት አቅጣጫ ነው?+ የጨለማ ስፍራስ የት ነው? 20  ወደ ክልሉ ልትወስደው ትችላለህ?ወደ ቤቱስ የሚወስደውን ጎዳና ታውቃለህ? 21  በዚያን ጊዜ ተወልደህ ስለነበር፣ዕድሜህም ትልቅ ስለሆነ* ይህን ሳታውቅ አትቀርም! 22  አመዳዩ ወደተከማቸበት መጋዘን ገብተሃል?+የበረዶውንስ ግምጃ ቤት አይተሃል?+ 23  ይህም ለመከራ ጊዜ፣ለውጊያና ለጦርነት ቀን ያስቀመጥኩት ነው።+ 24  ብርሃን* የሚሰራጨው ከየት አቅጣጫ ነው?የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ የሚነፍሰው ከየት ነው?+ 25  ለዶፍ መውረጃን፣ነጎድጓድ ለቀላቀለ ጥቁር ደመናም መንገድን ያዘጋጀ ማን ነው?+ 26  አንድም ሰው በሌለበት ቦታ፣ሰውም በማይኖርበት ምድረ በዳ የሚያዘንበው፣+ 27  የወደመውን ጠፍ መሬት የሚያረካው፣ሣርንም የሚያበቅለው ማን ነው?+ 28  ዝናብ አባት አለው?+ጠልንስ የወለደው ማን ነው?+ 29  በረዶ የሚወጣው ከማን ማህፀን ነው?የሰማዩንስ አመዳይ የወለደው ማን ነው?+ 30  ውኃዎች በድንጋይ የተሸፈኑ ያህል እንዲሆኑ፣የጥልቁ ውኃም ገጽ ግግር በረዶ እንዲሆን የሚያደርገው ማን ነው?+ 31  የኪማ ኅብረ ከዋክብትን* ገመድ ልታስር፣ወይስ የከሲል ኅብረ ከዋክብትን* ገመድ ልትፈታ ትችላለህ?+ 32  ኅብረ ከዋክብትን* በወቅቱ ልታወጣ፣ወይስ የአሽ ኅብረ ከዋክብትን* ከነልጆቹ ልትመራ ትችላለህ? 33  ሰማያት የሚመሩባቸውን ሕጎች ታውቃለህ?+ወይስ የሰማያትን* ሕጎች በምድር ላይ ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ? 34  ጎርፍ ይሸፍንህ ዘንድ፣ድምፅህን ወደ ደመናት ማንሳት ትችላለህ?+ 35  የመብረቅ ብልጭታዎችን መላክ ትችላለህ? እነሱስ አንተ ጋ ቀርበው ‘ይኸው መጥተናል!’ ይሉሃል? 36  በደመናት ውስጥ* ጥበብ ያኖረው፣+በሰማይ ለሚከናወነውስ ክስተት* ማስተዋልን የሰጠው ማን ነው?+ 37  ደመናትን ለመቁጠር የሚያስችል ጥበብ ያለው ማን ነው?ወይስ የሰማይን የውኃ ማሰሮዎች ሊደፋ የሚችል ማን ነው?+ 38  አፈሩ ቦክቶ እንዲጋገር፣የምድር ጓሎችም እንዲጣበቁ ሊያደርግ የሚችል ማን ነው? 39  ለአንበሳ አድነህ ግዳይ ልታመጣለት፣ወይስ የተራቡ የአንበሳ ግልገሎችን ልታጠግብ ትችላለህ?+ 40  እነሱ በዋሻቸው ውስጥ አድፍጠው፣ወይም በጎሬአቸው አድብተው ሳለ ይህን ልታደርግ ትችላለህ? 41  ጫጩቶቿ ወደ አምላክ ሲጮኹ፣የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፣ለቁራ መብል የሚያዘጋጅ ማን ነው?+

የግርጌ ማስታወሻ

የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።
ወይም “የሞት ጥላንስ።”
ቃል በቃል “ቀኖችህ (ብዙ ስለሆኑ)።”
“መብረቅ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
በቶረስ ኅብረ ከዋክብት የታቀፉ ፐልያዲስ የሚባሉ ከዋክብት ሊሆኑ ይችላሉ።
የኦርዮን ኅብረ ከዋክብት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ማዛሮትን።” በ2ነገ 23:5 ላይ የገባው ከዚህ ቃል ጋር ተዛማጅነት ያለው በብዙ ቁጥር የተሠራበት ቃል የዞዲያክ ኅብረ ከዋክብትን ያመለክታል።
የታላቁ ድብ ኅብረ ከዋክብት (ኧርሳ ሜጀር) ሊሆን ይችላል።
“የእሱን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“በሰው ውስጥ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ለአእምሮ” ማለትም ሊሆን ይችላል።