ኢዮብ 40:1-24

  • ይሖዋ ያቀረባቸው ተጨማሪ ጥያቄዎች (1-24)

    • ኢዮብ መልስ እንደሌለው አምኖ ተቀበለ (3-5)

    • “የእኔን ፍትሕ ትጠራጠራለህ?” (8)

    • አምላክ የብሄሞትን ጉልበት ገለጸ (15-24)

40  ይሖዋ በመቀጠል ኢዮብን እንዲህ አለው፦   “ስህተት የሚፈላልግ ሰው፣ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ሊሟገት ይገባል?+ አምላክን መውቀስ የሚፈልግ እሱ መልስ ይስጥ።”+   ኢዮብ ለይሖዋ እንዲህ በማለት መለሰ፦   “እነሆ፣ እኔ የማልረባ ሰው ነኝ።+ ምን ልመልስልህ እችላለሁ? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።+   አንዴ ተናግሬአለሁ፤ ከአሁን በኋላ ግን የምሰጠው መልስ የለም፤ሁለተኛ ጊዜም ተናገርኩ፤ ከዚህ በኋላ ግን አልናገርም።”   ከዚያም ይሖዋ ከአውሎ ነፋስ ውስጥ ለኢዮብ መለሰለት፦+   “እባክህ፣ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤እኔ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም ንገረኝ።+   የእኔን ፍትሕ ትጠራጠራለህ?* አንተ ትክክል ሆነህ ትገኝ ዘንድ እኔን ትኮንናለህ?+   ክንድህ የእውነተኛውን አምላክ ክንድ ያህል ኃያል ነው?+ወይስ ድምፅህ እንደ እሱ ድምፅ ሊያንጎደጉድ ይችላል?+ 10  እስቲ ራስህን በክብርና በግርማ አስጊጥ፤ደግሞም ታላቅነትና ሞገስ ተላበስ። 11  ቁጣህ ገንፍሎ ይፍሰስ፤ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ ዝቅ አድርገው። 12  ትዕቢተኛውን ሰው ሁሉ አይተህ አዋርደው፤ክፉዎችንም በቆሙበት ስፍራ ጨፍልቃቸው። 13  ሁሉንም በአፈር ውስጥ ደብቃቸው፤እነሱንም* በሰዋራ ቦታ እሰራቸው፤ 14  ያን ጊዜ ቀኝ እጅህ ልታድንህ እንደምትችል፣እኔ ራሴ አምኜ እቀበላለሁ።* 15  አንተን እንደፈጠርኩ፣ የፈጠርኩትን ብሄሞትን* ተመልከት። እንደ በሬ ሣር ይበላል። 16  በወገቡ ውስጥ ያለውን ጉልበት፣በሆዱም ጡንቻዎች ውስጥ ያለውን ኃይል ተመልከት! 17  ጅራቱን እንደ አርዘ ሊባኖስ ያጠነክረዋል፤የወርቹም ጅማቶች እርስ በርስ የተጠላለፉ ናቸው። 18  አጥንቶቹ የመዳብ ቱቦዎች ናቸው፤እግሮቹ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው። 19  እሱ ከአምላክ የፍጥረት ሥራዎች መካከል አውራ ነው፤በሰይፍ ሊቀርበው የሚችለው ሠሪው ብቻ ነው። 20  የዱር እንስሳት ሁሉ የሚፈነጩባቸው ተራሮችመብሉን ያበቅሉለታልና። 21  በውኃ ላይ በሚያድጉ ዕፀዋት ጥላ ሥር፣ረግረጋማ በሆነ ቦታ በሚገኙ ቄጠማዎችም ሥር ይተኛል። 22  በውኃ ላይ የሚያድጉ ዕፀዋት በጥላቸው ይጋርዱታል፤በሸለቆ* ውስጥ የሚገኙ የአኻያ ዛፎችም ይከቡታል። 23  ወንዙ ቢናወጥ አይፈራም። ዮርዳኖስ+ ወደ እሱ ቢጎርፍ አይሸበርም። 24  ዓይኖቹ እያዩ ሊይዘው የሚችል አለ?ወይስ በአፍንጫው መንጠቆ* ሊያስገባ የሚችል ይኖራል?

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ዋጋ ታሳጣለህ?”
ቃል በቃል “ፊታቸውንም።”
ወይም “አመሰግንሃለሁ።”
ጉማሬ ሊሆን ይችላል።
ወይም “በደረቅ ወንዝ።”
ቃል በቃል “ወጥመድ።”