ኢዮብ 5:1-27

  • ኤሊፋዝ ንግግሩን ቀጠለ (1-27)

    • ‘አምላክ ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኮል ይይዛቸዋል’ (13)

    • ‘ኢዮብ የአምላክን ተግሣጽ መናቅ አይኖርበትም’ (17)

5  “እስቲ ተጣራ! የሚመልስልህ ይኖራል? ከቅዱሳንስ* መካከል ወደ የትኛው ዞር ትላለህ?   ሞኝን ሰው ብስጭት ይገድለዋልና፤ማስተዋል የጎደለውንም ቅናት ይገድለዋል።   ሞኝ ሰው ሥር ሰዶ አየሁት፤ይሁንና የመኖሪያ ስፍራው በድንገት ተረገመ።   ወንዶች ልጆቹ ደህንነት ርቋቸዋል፤በከተማው በር ተረግጠዋል፤+ የሚያድናቸውም የለም።   እሱ የሰበሰበውን፣ የራበው ሰው ይበላዋል፤ከእሾህም መካከል ይወስድበታል፤ደግሞም ንብረታቸው በወጥመድ ተይዟል።   ጎጂ የሆነ ነገር ከአፈር አይበቅልምና፤ችግርም ከመሬት አይፈልቅም።   የእሳት ፍንጣሪ ወደ ላይ እንደሚወረወር፣ሰው የሚወለደው ለችግር ነው።   እኔ ብሆን ኖሮ አምላክን እለምን ነበር፤ጉዳዬንም ለአምላክ አቀርብ ነበር፤   እሱ ታላላቅና የማይመረመሩ ነገሮችን ያደርጋል፤ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ድንቅ ነገሮች ይሠራል። 10  በምድር ላይ ዝናብ ያዘንባል፤በሜዳዎችም ላይ ውኃ ይልካል። 11  ችግረኞችን ከፍ ያደርጋል፤እንዲሁም ያዘነውን ሰው መዳን እንዲያገኝ ከፍ ከፍ ያደርገዋል። 12  የብልጣ ብልጦችን ዕቅድ ያከሽፋል፤ስለዚህ የእጃቸው ሥራ አይሰምርም። 13  ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኮል ይይዛቸዋል፤+ስለሆነም የጮሌዎች ዕቅድ ይከሽፋል። 14  ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል፤ሌሊት የሆነ ይመስል እኩለ ቀን ላይ በዳበሳ ይሄዳሉ። 15  ከአፋቸው ሰይፍ ያድናል፤ድሃውንም ከብርቱው እጅ ይታደጋል፤ 16  በመሆኑም ችግረኛው ተስፋ ይኖረዋል፤የክፋት አፍ ግን ይዘጋል። 17  እነሆ፣ አምላክ የሚወቅሰው ሰው ደስተኛ ነው፤ስለዚህ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ተግሣጽ አትናቅ! 18  እሱ ሥቃይ ያመጣልና፤ ሆኖም ቁስሉን ይጠግናል፤እሱ ይሰብራል፤ ይሁንና በገዛ እጆቹ ይፈውሳል። 19  ከስድስት መቅሰፍቶች ያድንሃል፤ሰባተኛውም አይጎዳህም። 20  በረሃብ ወቅት ከሞት ይዋጅሃል፤በጦርነትም ጊዜ ከሰይፍ ኃይል ይታደግሃል። 21  ከምላስ ጅራፍ ትጠበቃለህ፤+ጥፋት ሲመጣም አትፈራም። 22  በጥፋትና በረሃብ ላይ ትስቃለህ፤የምድርንም አራዊት አትፈራም። 23  በሜዳ ያሉ ድንጋዮች አይጎዱህም፤*የዱር አራዊትም ከአንተ ጋር ሰላም ይኖራቸዋል። 24  በድንኳንህ ውስጥ አስተማማኝ ሁኔታ* እንደሚሰፍን ታውቃለህ፤የግጦሽ መሬትህን ስትቃኝም አንዳች ነገር አይጎድልብህም። 25  ብዙ ልጆች ይኖሩሃል፤ዘሮችህም በምድር ላይ እንደሚበቅል ሣር ይበዛሉ። 26  በወቅቱ እንደተሰበሰበ የእህል ነዶ፣ብርቱ እንደሆንክ ወደ መቃብር ትወርዳለህ። 27  እነሆ፣ ይህን መርምረናል፤ እውነት መሆኑንም አረጋግጠናል። ይህን ስማ፤ ደግሞም ተቀበል።”

የግርጌ ማስታወሻ

ሰብዓ ሊቃናት “ከቅዱሳን መላእክትስ” ይላል።
ወይም “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይጋባሉ (ስምምነት ያደርጋሉ)።”
ቃል በቃል “ሰላም።”