ኢዮብ 8:1-22
8 ከዚያም ሹሃዊው+ በልዳዶስ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2 “እንዲህ የምትናገረው እስከ መቼ ነው?+
ከአፍህ የሚወጣው ቃል ብርቱ ነፋስ ነው!
3 አምላክ ፍትሕን ያዛባል?ወይስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ጽድቅን ያጣምማል?
4 ልጆችህ በእሱ ላይ ኃጢአት ሠርተው ከሆነ፣ለፈጸሙት ዓመፅ እንዲቀጡ አድርጓል፤*
5 አንተ ግን ወደ አምላክ ዞር ብትል፣+ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሞገስ እንዲያሳይህ ብትማጸን፣
6 በእርግጥ ንጹሕና ቅን ብትሆን፣+እሱ ትኩረት ይሰጥሃል፤*ወደ ትክክለኛ ቦታህም ይመልስሃል።
7 ጅማሬህ አነስተኛ ቢሆንም፣የወደፊት ሕይወትህ ታላቅ ይሆናል።+
8 እስቲ የቀድሞውን ትውልድ ጠይቅ፤አባቶቻቸው ለተገነዘቧቸው ነገሮችም ትኩረት ስጥ።+
9 እኛ የተወለድነው ገና ትናንት ስለሆነ የምናውቀው ነገር የለም፤ምክንያቱም በምድር ላይ ዘመናችን እንደ ጥላ ነው።
10 እነሱ አያስተምሩህም?ደግሞስ የሚያውቁትን ነገር* አይነግሩህም?
11 ደንገል ረግረጋማ ባልሆነ ስፍራ ያድጋል?
ሸምበቆስ ውኃ በሌለበት ቦታ ያድጋል?
12 ገና ሳያብብና ሳይቆረጥ፣ከሌላው ተክል ሁሉ በፊት ይደርቃል።
13 አምላክን የሚረሱ ሰዎች ሁሉ መጨረሻቸው እንደዚህ ነው፤*አምላክ የለሽ የሆነ* ሰው ተስፋ ይጨልማልና፤
14 የሚመካበት ነገር ከንቱ ነው፤የሚታመንበትም ነገር ከሸረሪት ድር* የማይሻል ነው።
15 እሱ ቤቱን ይደገፈዋል፤ ሆኖም ቤቱ ጸንቶ አይቆምም፤አጥብቆ ሊይዘው ይሞክራል፤ ሆኖም አይጸናም።
16 እሱ በፀሐይ ብርሃን እንደሚያድግ እርጥበት ያለው ተክል ነው፤ቅርንጫፎቹም በአትክልት ስፍራው ውስጥ ይንሰራፋሉ።+
17 ሥሩም በድንጋይ ክምር ውስጥ ይጠላለፋል፤በድንጋዮቹ መካከል ቤት ይፈልጋል።*
18 ሆኖም ከስፍራው በሚነቀልበት* ጊዜ፣ያ ስፍራ ‘ፈጽሞ አይቼህ አላውቅም’ ብሎ ይክደዋል።+
19 አዎ፣ በዚህ ሁኔታ ይጠፋል፤*+ከዚያም ሌሎች ከአፈሩ ውስጥ ይበቅላሉ።
20 በእርግጥም አምላክ ንጹሕ አቋማቸውን* የሚጠብቁትን አይጥልም፤ክፉ ሰዎችንም አይረዳም፤*
21 በመጨረሻም አፍህን በሳቅ፣ከንፈሮችህንም በእልልታ ይሞላል።
22 የሚጠሉህ ኀፍረት ይከናነባሉ፤የክፉዎችም ድንኳን ይጠፋል።”