ኤርምያስ 18:1-23

  • በሸክላ ሠሪው እጅ ውስጥ ያለ ጭቃ (1-12)

  • ይሖዋ ለእስራኤል ጀርባውን ሰጠ (13-17)

  • በኤርምያስ ላይ የተጠነሰሰ ሴራና እሱ ያቀረበው ልመና (18-23)

18  ከይሖዋ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦  “ተነሥተህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፤+ እኔም በዚያ ቃሌን አሰማሃለሁ።”  ስለዚህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ወረድኩ፤ እሱም በሸክላ መዘውሮቹ ላይ እየሠራ ነበር።  ሆኖም ሸክላ ሠሪው በጭቃ እየሠራ የነበረው ዕቃ እጁ ላይ ተበላሸ። በመሆኑም ሸክላ ሠሪው ተስማሚ ሆኖ ባገኘው መንገድ* መልሶ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው።  ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “‘የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ይህ ሸክላ ሠሪ እንዳደረገው እኔም በእናንተ ላይ ማድረግ አልችልም?’ ይላል ይሖዋ። ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፣ እነሆ፣ በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ ጭቃ፣ እናንተም በእኔ እጅ እንዲሁ ናችሁ።+  አንድን ብሔር ወይም አንድን መንግሥት እንደምነቅል፣ እንደማፈርስና እንደማጠፋ በተናገርኩ ጊዜ፣+  ያ ብሔር እኔ ያወገዝኩትን ክፉ ነገር ቢተው፣ ሐሳቤን ለውጬ በእሱ ላይ ላመጣው ያሰብኩትን ጥፋት እተወዋለሁ።*+  ሆኖም አንድን ብሔር ወይም አንድን መንግሥት እንደምገነባውና እንደምተክለው በተናገርኩ ጊዜ፣ 10  በፊቴ ክፉ የሆነውን ነገር ቢያደርግና ድምፄን ባይሰማ እኔም ሐሳቤን ለውጬ ለእሱ አደርገዋለሁ ብዬ ያሰብኩትን መልካም ነገር እተወዋለሁ።’* 11  “አሁንም ለይሁዳ ሰዎችና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እባክህ እንዲህ በላቸው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በእናንተ ላይ ጥፋት ለማምጣት እየተዘጋጀሁ ነው፤* በእናንተም ላይ ክፉ ነገር እየጠነሰስኩ ነው። እባካችሁ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ተግባራችሁንም አስተካክሉ።”’”+ 12  እነሱ ግን እንዲህ አሉ፦ “ይህ ያበቃለት ጉዳይ ነው!+ እኛ እንደሆነ በራሳችን ሐሳብ እንሄዳለን፤ እያንዳንዳችንም ግትር የሆነውን ክፉ ልባችንን እንከተላለን።”+ 13  ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እስቲ ራሳችሁ ብሔራትን ጠይቁ። እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቷል? የእስራኤል ድንግል እጅግ የሚሰቀጥጥ ነገር አድርጋለች።+ 14  የሊባኖስ ዓለታማ ተረተር በረዶ ተለይቶት ያውቃል? ወይስ ከሩቅ ስፍራ የሚፈስሱት ቀዝቃዛ ውኃዎች ይደርቃሉ? 15  ሕዝቤ ግን እኔን ረስቶኛል።+ ለማይረባ ነገር መሥዋዕት ያቀርባሉና፤+ሰዎችም በመንገዳቸው፣ በጥንቶቹ ጎዳናዎች እንዲሰናከሉ+ደግሞም ባልተስተካከሉና ባልተደለደሉ* ተለዋጭ መንገዶች እንዲሄዱ ያደርጋሉ፤ 16  ስለዚህ ምድራቸው አስፈሪ ቦታ፣+ለዘላለምም ማፏጫ ትሆናለች።+ በዚያ የሚያልፍ ሁሉ በፍርሃት አፍጥጦ ይመለከታል፤ ራሱንም ይነቀንቃል።+ 17  እንደ ምሥራቅ ነፋስ በጠላት ፊት እበትናቸዋለሁ። በሚጠፉበት ቀን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም።”+ 18  እነሱም እንዲህ አሉ፦ “ኑ፣ በኤርምያስ ላይ እናሲር፤+ ሕጉ* ከካህናት፣ ምክር ከጠቢባን ወይም ቃሉ ከነቢያት አይጠፋምና። ኑና በአንደበታችን እናጥቃው፤* የሚናገረውንም ቃል አንስማ።” 19  ይሖዋ ሆይ፣ ትኩረትህን ወደ እኔ አድርግ፤ተቃዋሚዎቼ የሚናገሩትንም ስማ። 20  ስለ መልካም ነገር ክፉ መመለስ አግባብ ነው? እነሱ ጉድጓድ ቆፍረውልኛልና።*+ ቁጣህ ከእነሱ እንዲመለስ፣ ስለ እነሱ መልካም ነገር ለመናገር ምን ያህል ጊዜ በፊትህ እንደቆምኩ አስብ። 21  ስለዚህ ወንዶች ልጆቻቸውን ለረሃብ ዳርጋቸው፤ለሰይፍ ኃይል አሳልፈህ ስጣቸው።+ ሚስቶቻቸው የወላድ መሃንና መበለት ይሁኑ።+ ወንዶቻቸው በገዳይ መቅሰፍት ይሙቱ፤ወጣቶቻቸው በጦር ሜዳ በሰይፍ ተመተው ይውደቁ።+ 22  በድንገት ወራሪዎችን ስታመጣባቸውከየቤታቸው ጩኸት ይሰማ። እኔን ለመያዝ ጉድጓድ ቆፍረዋልና፤ለእግሮቼም ወጥመድ ዘርግተዋል።+ 23  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግንእኔን ለመግደል የጠነሰሱትን ሴራ ሁሉ በሚገባ ታውቃለህ።+ በደላቸውን አትሸፍን፤ኃጢአታቸውንም ከፊትህ አትደምስስ። በቁጣ ተነሳስተህ እርምጃ ስትወስድባቸው+በፊትህ ይሰናከሉ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ሸክላ ሠሪው በዓይኑ ፊት ትክክል መስሎ በታየው መንገድ።”
ወይም “ላመጣው ባሰብኩት ጥፋት እጸጸታለሁ።”
ወይም “ባሰብኩት መልካም ነገር እጸጸታለሁ።”
ቃል በቃል “እየሠራሁ ነው።”
ወይም “ባልተሠሩ።”
ወይም “መመሪያው፤ ትምህርቱ።”
ቃል በቃል “በምላስ እንምታው።”
ወይም “ለነፍሴ ጉድጓድ ቆፍረዋልና።”