ኤርምያስ 20:1-18

  • ጳስኮር ኤርምያስን መታው (1-6)

  • ኤርምያስ መስበኩን ሊያቆም አልቻለም (7-13)

    • የአምላክ ቃል እንደሚነድ እሳት ነው (9)

    • ይሖዋ እንደ አስፈሪ ተዋጊ ነው (11)

  • ኤርምያስ ያሰማው እሮሮ (14-18)

20  በይሖዋ ቤት ዋና ሹም የነበረው የኢሜር ልጅ ካህኑ ጳስኮር፣ ኤርምያስ እነዚህን ነገሮች ሲተነብይ ሰማ።  ጳስኮርም ነቢዩ ኤርምያስን መታው፤ ከዚያም በይሖዋ ቤት ባለው በላይኛው የቢንያም በር በእግር ግንድ ጠረቀው።+  ይሁንና በማግስቱ ጳስኮር ኤርምያስን ከእግር ግንዱ ውስጥ ፈታው፤ በዚህ ጊዜ ኤርምያስ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ፣ ማጎርሚሳቢብ*+ ብሎ ይጠራሃል እንጂ ጳስኮር አይልህም።  ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘አንተም ሆንክ ወዳጆችህ እንድትሸበሩ አደርጋለሁ፤ እነሱም ዓይንህ እያየ በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ፤+ ይሁዳንም ሁሉ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እሱም በግዞት ወደ ባቢሎን ይወስዳቸዋል፤ በሰይፍም ይገድላቸዋል።+  የዚህችን ከተማ ሀብት ሁሉ፣ ጥሪቷን ሁሉ፣ ውድ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ እንዲሁም የይሁዳን ነገሥታት ውድ ሀብት ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ።+ እነሱም ይበዘብዟቸዋል፤ ወደ ባቢሎንም ያግዟቸዋል።+  ጳስኮር ሆይ፣ አንተና በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ በግዞት ትወሰዳላችሁ። ወደ ባቢሎን ትሄዳለህ፤ በዚያም ትሞታለህ፤ ከወዳጆችህም ሁሉ ጋር በዚያ ትቀበራለህ፤ ምክንያቱም ለእነሱ የሐሰት ትንቢት ተናግረሃል።’”+   ይሖዋ ሆይ፣ አሞኘኸኝ፤ እኔም ተሞኘሁ። አንተ በእኔ ላይ በረታህ፤ አሸነፍክም።+ እኔም ቀኑን ሙሉ መሳለቂያ ሆንኩ፤ሁሉም ያፌዙብኛል።+   በተናገርኩ ቁጥር እጮኻለሁና፤“ዓመፅና ጥፋት!” ብዬ አውጃለሁ። የይሖዋ ቃል ቀኑን ሙሉ ስድብና ፌዝ አስከትሎብኛል።+   ስለዚህ “እሱን አላነሳም፤ከእንግዲህም በስሙ አልናገርም” አልኩ።+ ይሁንና ቃሉ በልቤ ውስጥ እንዳለ፣ በአጥንቶቼም ውስጥ እንደገባ የሚነድ እሳት ሆነብኝ፤አፍኜ መያዝ አቃተኝ፤ከዚህ በላይ መቋቋም አልቻልኩም።+ 10  ብዙ መጥፎ ወሬ ሰምቻለሁና፤በዙሪያዬ ያለው ሁኔታ አሸብሮኛል።+ “አውግዙት፤ እናውግዘው!” ሰላም የሚመኝልኝ ሰው ሁሉ የእኔን ውድቀት ይጠባበቃል፦+ “ምናልባት ይታለል ይሆናል፤እኛም እናሸንፈዋለን፤ ደግሞም እንበቀለዋለን።” 11  ይሖዋ ግን እንደ አስፈሪ ተዋጊ ከእኔ ጋር ነበር።+ ከዚህም የተነሳ የሚያሳድዱኝ ሰዎች ይሰናከላሉ እንጂ አያሸንፉም።+ ስለማይሳካላቸውም ለከፍተኛ ኀፍረት ይዳረጋሉ። የሚደርስባቸው ዘላለማዊ ውርደት ፈጽሞ አይረሳም።+ 12  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን ጻድቁን ትመረምራለህ፤የውስጥ ሐሳብንና* ልብን ታያለህ።+ በእነሱ ላይ የምትወስደውን የበቀል እርምጃ እንዳይ አድርገኝ፤+ጉዳዬን ለአንተ አቅርቤአለሁና።+ 13  ለይሖዋ ዘምሩ! ይሖዋን አወድሱ! እሱ ድሃውን* ከክፉ አድራጊዎች እጅ ታድጓልና። 14  የተወለድኩበት ቀን የተረገመ ይሁን! እናቴ እኔን የወለደችበት ቀን አይባረክ!+ 15  ለአባቴ “ልጅ፣ አዎ ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል!” የሚል ምሥራች አብስሮ እጅግ ደስ ያሰኘው ሰው የተረገመ ይሁን። 16  ያ ሰው፣ ይሖዋ ያላንዳች ጸጸት እንደገለበጣቸው ከተሞች ይሁን። በማለዳ ዋይታ፣ በቀትርም የጦርነት ሁካታ ይስማ። 17  እናቴ የመቃብሬ ቦታ እንድትሆን፣ማህፀኗም ዘወትር እርጉዝ እንደሆነ ይኖር ዘንድ፣ገና በማህፀን ሳለሁ ለምን አልገደለኝም?+ 18  ችግርንና ሐዘንን እንዳይ፣ዕድሜዬም በኀፍረት እንዲያከትምለምን ከማህፀን ወጣሁ?+

የግርጌ ማስታወሻ

“ዙሪያ ገባው ሽብር” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ጥልቅ ስሜትንና።” ቃል በቃል “ኩላሊትንና።”
ወይም “የድሃውን ነፍስ።”