ኤርምያስ 23:1-40

  • መልካምና ክፉ እረኞች (1-4)

  • ‘በጻድቁ ቀንበጥ’ ሥር ያለስጋት መኖር (5-8)

  • ሐሰተኛ ነቢያት ተወገዙ (9-32)

  • “የይሖዋ ሸክም” (33-40)

23  “በማሰማሪያዬ ያሉትን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው!” ይላል ይሖዋ።+  ስለዚህ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሕዝቡን በሚጠብቁት እረኞች ላይ እንዲህ ይላል፦ “በጎቼን በትናችኋል፤ አባራችኋቸዋል፤ ትኩረትም አልሰጣችኋቸውም።”+ “ስለዚህ ከክፉ ድርጊታችሁ የተነሳ ትኩረቴን በእናንተ ላይ አደርጋለሁ” ይላል ይሖዋ።  “ከዚያም የቀሩትን በጎቼን ከበተንኩባቸው አገሮች ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤+ ወደ መሰማሪያቸውም መልሼ አመጣቸዋለሁ፤+ እነሱም ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ደግሞም ይበዛሉ።+  እኔም በሚገባ የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሳላቸዋለሁ።+ ከእንግዲህ አይፈሩም፣ አይሸበሩም እንዲሁም አንዳቸውም አይጎድሉም” ይላል ይሖዋ።  “እነሆ፣ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቀንበጥ* የማስነሳበት ጊዜ እየደረሰ ነው”+ ይላል ይሖዋ። “ንጉሥም ይገዛል፤+ በማስተዋል ይመላለሳል እንዲሁም በምድሪቱ ላይ ለፍትሕና ለጽድቅ ይቆማል።+  በእሱ ዘመን ይሁዳ ይድናል፤+ እስራኤልም ያለስጋት ይኖራል።+ የሚጠራበትም ስም ‘ይሖዋ ጽድቃችን ነው’ የሚል ይሆናል።”+  “ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ ‘የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ባወጣው ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ!’ የማይሉበት ጊዜ ይመጣል” ይላል ይሖዋ፤+  “ከዚህ ይልቅ ‘የእስራኤልን ቤት ዘሮች ከሰሜን ምድርና እነሱን ከበተነባቸው አገሮች ሁሉ ባወጣውና መልሶ ባመጣው ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ’ ይላሉ፤ እነሱም በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።”+  ነቢያቱን በተመለከተ፣ ልቤ በውስጤ ተሰብሯል። አጥንቶቼ ሁሉ እየተንቀጠቀጡ ነው። ከይሖዋና ከቅዱስ ቃሉ የተነሳእንደሰከረ ሰውናየወይን ጠጅ እንዳሸነፈው ሰው ሆንኩ። 10  ምድሪቱ በአመንዝሮች ተሞልታለችና፤+ከእርግማኑ የተነሳ ምድሪቱ አዝናለች፤+በምድረ በዳ ያሉት ማሰማሪያዎችም ደርቀዋል።+ መንገዳቸው መጥፎ ነው፤ ሥልጣናቸውንም አላግባብ ይጠቀሙበታል። 11  “ነቢዩም ሆነ ካህኑ ተበክለዋል።*+ በገዛ ቤቴ እንኳ ሳይቀር የሠሩትን ክፋት አግኝቻለሁ”+ ይላል ይሖዋ። 12  “ስለሆነም መንገዳቸው የሚያዳልጥና ጨለማ ይሆናል፤+ይገፋሉ እንዲሁም ይወድቃሉ። በሚመረመሩበት ዓመት፣ጥፋት አመጣባቸዋለሁና” ይላል ይሖዋ። 13  “በሰማርያ+ ነቢያት ላይ ደግሞ አስጸያፊ ነገር አይቻለሁ። ትንቢት የሚናገሩት በባአል አነሳሽነት ነው፤ሕዝቤ እስራኤልም እንዲባዝን አድርገዋል። 14  በኢየሩሳሌም ነቢያትም ላይ የሚዘገንኑ ነገሮች አይቻለሁ። ያመነዝራሉ፤+ በሐሰትም ይመላለሳሉ፤+ክፉ አድራጊዎችን ያደፋፍራሉ፤*ከክፋታቸውም አይመለሱም። ለእኔ ሁሉም እንደ ሰዶም፣+ነዋሪዎቿም እንደ ገሞራ+ ናቸው።” 15  ስለዚህ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በነቢያቱ ላይ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ እኔ ጭቁኝ እንዲበሉ አደርጋቸዋለሁ፤የተመረዘም ውኃ እንዲጠጡ እሰጣቸዋለሁ።+ የኢየሩሳሌም ነቢያት በምድሪቱ ሁሉ ላይ ክህደት አሰራጭተዋልና።” 16  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ትንቢት የሚተነብዩላችሁ ነቢያት የሚናገሩትን ቃል አትስሙ።+ እነሱ እያሞኟችሁ ነው።* የሚናገሩት ራእይ ከይሖዋ አፍ የወጣ ሳይሆን+ከገዛ ልባቸው የመነጨ ነው።+ 17  እነሱ እኔን ለሚንቁ ሰዎች ደግመው ደጋግመው‘ይሖዋ “ሰላም ታገኛላችሁ” ብሏል’ ይላሉ።+ ግትር የሆነ ልባቸውን የሚከተሉትን ሁሉ‘ጥፋት አይደርስባችሁም’ ይሏቸዋል።+ 18  ቃሉን ለማየትና ለመስማትከይሖዋ የቅርብ ወዳጆች ጋር የቆመ ማን ነው? ይሰማስ ዘንድ ለቃሉ ትኩረት የሰጠ ማን ነው? 19  እነሆ፣ የይሖዋ አውሎ ነፋስ በታላቅ ቁጣ ይነሳል፤እንደሚሽከረከር ኃይለኛ ነፋስ በክፉዎች ራስ ላይ እየተሽከረከረ ይወርዳል።+ 20  ይሖዋ የልቡን ሐሳብ ሳያከናውንና ሳይፈጽምቁጣው አይመለስም። በዘመኑ መጨረሻ ይህን በግልጽ ትረዳላችሁ። 21  ነቢያቱን እኔ አልላክኋቸውም፤ እነሱ ግን ሮጡ። እኔ የነገርኳቸው ነገር የለም፤ እነሱ ግን ትንቢት ተናገሩ።+ 22  ከእኔ የቅርብ ወዳጆች ጋር ቢቆሙ ኖሮሕዝቤ ቃሌን እንዲሰማ ባደረጉ ነበር፤ደግሞም ከክፉ መንገዱና ከመጥፎ ድርጊቱ እንዲመለስ ባደረጉ ነበር።”+ 23  “እኔ የቅርብ አምላክ ብቻ ነኝ? የሩቅስ አምላክ አይደለሁም?” ይላል ይሖዋ። 24  “እኔ እንዳላየው በስውር ቦታ መሸሸግ የሚችል ሰው ይኖራል?”+ ይላል ይሖዋ። “ሰማያትንና ምድርን የሞላሁት እኔ አይደለሁም?”+ ይላል ይሖዋ። 25  “‘ሕልም አይቻለሁ! ሕልም አይቻለሁ!’+ እያሉ በስሜ የሐሰት ትንቢት የሚናገሩ ነቢያትን ቃል ሰምቻለሁ። 26  የሐሰት ትንቢት ይናገሩ ዘንድ ይህ ነገር በነቢያት ልብ ውስጥ የሚኖረው እስከ መቼ ነው? እነሱ ከገዛ ልባቸው ያመነጩትን ማታለያ የሚናገሩ ነቢያት ናቸው።+ 27  አባቶቻቸው በባአል የተነሳ ስሜን እንደረሱ ሁሉ፣+ እነሱም አንዳቸው ለሌላው በሚናገሩት ሕልም አማካኝነት ሕዝቤ ስሜን እንዲረሳ ማድረግ ይፈልጋሉ። 28  ሕልም ያየ ነቢይ ሕልሙን ይናገር፤ ይሁንና ቃሌ ያለው ቃሌን በእውነት ይናገር።” “ገለባና እህል አንድ የሚያደርጋቸው ምን ነገር አለ?” ይላል ይሖዋ። 29  “ቃሌ እንደ እሳት አይደለም?”+ ይላል ይሖዋ፤ “ቋጥኝንስ እንደሚያደቅ መዶሻ አይደለም?”+ 30  “ስለዚህ እርስ በርስ ቃሌን በሚሰራረቁ ነቢያት ላይ ተነስቻለሁ” ይላል ይሖዋ።+ 31  “እነሆ፣ በምላሳቸው እየቀባጠሩ ‘እሱ እንዲህ ይላል!’ ብለው በሚናገሩ ነቢያት ላይ ተነስቻለሁ” ይላል ይሖዋ።+ 32  “እነሆ፣ ሐሰትን በሚያልሙና በሚናገሩ እንዲሁም የሐሰት ወሬ እያናፈሱና ጉራ እየነዙ ሕዝቤን በሚያስቱ ነቢያት ላይ ተነስቻለሁ” ይላል ይሖዋ።+ “ሆኖም እኔ አልላክኋቸውም ወይም አላዘዝኳቸውም። ስለዚህ ይህን ሕዝብ ምንም አይጠቅሙትም”+ ይላል ይሖዋ። 33  “ይህ ሕዝብ ወይም አንድ ነቢይ አሊያም አንድ ካህን ‘የይሖዋ ሸክም* ምንድን ነው?’ ብለው በሚጠይቁህ ጊዜ እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘“ሸክሙ እናንተ ናችሁ! እኔም እጥላችኋለሁ”+ ይላል ይሖዋ።’ 34  ነቢይ ወይም ካህን አሊያም ማንኛውም ሰው ‘ይህ የይሖዋ ሸክም* ነው!’ እያለ ቢናገር በእሱም ሆነ በቤተሰቡ ላይ ትኩረቴን አደርጋለሁ። 35  እያንዳንዳችሁ ባልንጀራችሁንና ወንድማችሁን ‘ይሖዋ የሰጠው መልስ ምንድን ነው? ይሖዋ የተናገረውስ ምንድን ነው?’ ትላላችሁ። 36  ሆኖም ከእንግዲህ የይሖዋ ሸክም* ብላችሁ አትናገሩ፤ ሸክሙ* የእያንዳንዱ ሰው የገዛ ራሱ ቃል ነውና፤ እናንተም ሕያው አምላክ የሆነውን የአምላካችንን የሠራዊት ጌታ የይሖዋን ቃል ለውጣችኋል። 37  “ነቢዩን እንዲህ ትለዋለህ፦ ‘ይሖዋ የሰጠህ መልስ ምንድን ነው? ይሖዋ የተናገረውስ ምንድን ነው? 38  “የይሖዋ ሸክም!”* ማለታችሁን የማታቆሙ ከሆነ፣ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “‘“የይሖዋ ሸክም!”* አትበሉ’ ብዬ ከነገርኳችሁ በኋላ እናንተ ‘ይህ ቃል የይሖዋ ሸክም* ነው’ በማለታችሁ፣ 39  እነሆ፣ እናንተንም ሆነ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ የሰጠኋትን ከተማ አንስቼ ከፊቴ እወረውራችኋለሁ። 40  የማይረሳ የዘላለም ኀፍረትና የዘላለም ውርደት በእናንተ ላይ አመጣለሁ።”’”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ወራሽ።”
ወይም “ከሃዲ ሆነዋል።”
ቃል በቃል “የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ።”
ወይም “በባዶ ተስፋ እየሞሏችሁ ነው።”
ወይም “ከባድ መልእክት።” የዕብራይስጡ ቃል “ከባድ መለኮታዊ ፍርድ” ወይም “ከባድ የሆነ ነገር” የሚል ሁለት ትርጉም አለው።
ወይም “ከባድ መልእክት።”
ወይም “ከባድ መልእክት።”
ወይም “ከባዱ መልእክት።”
ወይም “ከባድ መልእክት።”
ወይም “ከባድ መልእክት።”
ወይም “ከባድ መልእክት።”