ኤርምያስ 25:1-38
25 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮዓቄም+ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ይኸውም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት መላውን የይሁዳን ሕዝብ በተመለከተ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።
2 ነቢዩ ኤርምያስ የይሁዳን ሕዝብ ሁሉና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች በሙሉ አስመልክቶ* እንዲህ ሲል ተናገረ፦
3 “ከይሁዳ ንጉሥ ከአምዖን ልጅ ከኢዮስያስ 13ኛ ዓመት የግዛት ዘመን+ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ላለፉት 23 ዓመታት የይሖዋ ቃል ወደ እኔ መጣ፤ እኔም ደግሜ ደጋግሜ ነገርኳችሁ፤* እናንተ ግን አትሰሙም።+
4 ይሖዋም ደግሞ ደጋግሞ* አገልጋዮቹን ነቢያትን ሁሉ ወደ እናንተ ላከ፤ እናንተ ግን አትሰሙም ወይም ጆሯችሁን አትሰጡም።+
5 እነሱም እንዲህ ይላሉ፦ ‘እባካችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ድርጊታችሁ ተመለሱ፤+ ይህን ካደረጋችሁ ይሖዋ ለብዙ ዘመን እንድትኖሩባት ሲል ከረጅም ጊዜ በፊት ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣት ምድር ላይ ትኖራላችሁ።
6 በእጃችሁ ሥራ ታስቆጡኝ ዘንድ ሌሎች አማልክትን አትከተሉ፣ አታገልግሏቸው፣ አትስገዱላቸውም፤ አለዚያ ጥፋት አመጣባችኋለሁ።’
7 “‘እናንተ ግን እኔን አትሰሙም’ ይላል ይሖዋ። ‘ይልቁንም በራሳችሁ ላይ ጥፋት ታመጡ ዘንድ አስቆጣችሁኝ።’+
8 “ስለዚህ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘“ቃሌን ስለማትታዘዙ፣
9 የሰሜንን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ”+ ይላል ይሖዋ፤ “አገልጋዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን* እጠራለሁ፤+ በዚህች ምድር፣ በነዋሪዎቿና በዙሪያዋ ባሉ በእነዚህ ብሔራት ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ።+ ፈጽሞ አጠፋቸዋለሁ፤ እንዲሁም መቀጣጫና ማፏጫ እንዲሆኑ ብሎም ባድማ ሆነው እንዲቀሩ አደርጋለሁ።
10 የሐሴትንና የደስታን ድምፅ፣ የሙሽራንና የሙሽሪትን ድምፅ፣ የወፍጮን ድምፅና የመብራትን ብርሃን ከመካከላቸው አስቀራለሁ።+
11 መላ ምድሪቱ ትወድማለች፤ እንዲሁም አስፈሪ ቦታ ትሆናለች፤ እነዚህም ብሔራት የባቢሎንን ንጉሥ 70 ዓመት ያገለግሉታል።”’+
12 “‘ይሁንና ሰባው ዓመት ሲፈጸም+ በበደላቸው የተነሳ የባቢሎንን ንጉሥና ያንን ብሔር ተጠያቂ አደርጋለሁ’*+ ይላል ይሖዋ፤ ‘የከለዳውያንንም ምድር እስከ ወዲያኛው ባድማ አደርገዋለሁ።+
13 በምድሪቱ ላይ የተናገርኩትን ቃል ሁሉ ይኸውም ኤርምያስ በሁሉም ብሔራት ላይ የተነበየውንና በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን ነገር ሁሉ አመጣባታለሁ።
14 ብዙ ብሔራትና ታላላቅ ነገሥታት+ ባሪያዎች ያደርጓቸዋልና፤+ እኔም እንደ ድርጊታቸውና እንደ ገዛ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ።’”+
15 የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ብሎኛልና፦ “የቁጣ ወይን ጠጅ ያለበትን ይህን ጽዋ ከእጄ ውሰድ፤ እኔም ወደምልክህ ብሔራት ሁሉ ሄደህ አጠጣቸው።
16 እነሱም በመካከላቸው ከምሰደው ሰይፍ የተነሳ ይጠጣሉ፣ ይንገዳገዳሉ፣ እንደ አበደ ሰውም ይሆናሉ።”+
17 ስለዚህ ከይሖዋ እጅ ጽዋውን ወሰድኩ፤ ይሖዋ ወደላከኝም ብሔራት ሁሉ ሄጄ አጠጣኋቸው፦+
18 ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ባድማ፣ መቀጣጫና ማፏጫ እንዲሆኑ እንዲሁም ለእርግማን እንዲዳረጉ+ በመጀመሪያ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች፣+ ነገሥታቷንና መኳንንቷን አጠጣኋቸው፤
19 ከዚያም የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንና አገልጋዮቹ፣ መኳንንቱና ሕዝቡ ሁሉ፣+
20 ድብልቅ የሆነው ሕዝባቸው ሁሉ፣ የዑጽ ምድር ነገሥታት ሁሉ፣ የፍልስጤማውያን+ ምድር ነገሥታት ሁሉ፣ አስቀሎን፣+ ጋዛ፣ ኤቅሮንና ከአሽዶድ የቀሩት ሰዎች፣
21 ኤዶም፣+ ሞዓብና+ አሞናውያን፣+
22 የጢሮስ ነገሥታት ሁሉ፣ የሲዶና+ ነገሥታት ሁሉና በባሕሩ ላይ ያለው ደሴት ነገሥታት፣
23 ዴዳን፣+ ቴማ፣ ቡዝና በሰሪሳራቸው* ላይ ያለውን ፀጉር የሚላጩ ሁሉ፣+
24 የዓረብ ነገሥታት ሁሉና+ በምድረ በዳ የሚኖሩት ድብልቅ ሕዝብ ነገሥታት ሁሉ፣
25 የዚምሪ ነገሥታት ሁሉ፣ የኤላም+ ነገሥታት ሁሉና የሜዶናውያን ነገሥታት+ ሁሉ፣
26 በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉ የሰሜን ነገሥታት ሁሉ አንድ በአንድ እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ ሌሎች የዓለም መንግሥታት ሁሉ ጠጡ፤ ከእነሱም በኋላ የሼሻቅ*+ ንጉሥ ይጠጣል።
27 “አንተም እንዲህ በላቸው፦ ‘የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በመካከላችሁ ከምሰደው ሰይፍ የተነሳ ጠጡ፣ ስከሩ፣ አስታውኩ፣ ዳግመኛም ላትነሱ ውደቁ።”’+
28 ጽዋውን ከእጅህ ወስደው ለመጠጣት ፈቃደኛ ባይሆኑ እንዲህ በላቸው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በግድ ትጠጣላችሁ!
29 እነሆ፣ በመጀመሪያ የማጠፋው በስሜ የተጠራችውን ከተማ+ ከሆነ እናንተስ ከቅጣት ታመልጣላችሁ?”’+
“‘በምድር ነዋሪዎች ሁሉ ላይ ሰይፍን ስለምጠራ እናንተም ከቅጣት አታመልጡም’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
30 “አንተም ይህን ቃል ሁሉ ትተነብይላቸዋለህ፤ እንዲህም ትላቸዋለህ፦‘ይሖዋ ከላይ ሆኖ ይጮኻል፤ከቅዱስ ማደሪያውም ድምፁን ያሰማል።
በመኖሪያ ስፍራውም ላይ በኃይል ይጮኻል።
ወይን መጭመቂያውን እንደሚረግጡ ሰዎች፣በምድር ነዋሪዎች ሁሉ ላይ በድል አድራጊነት ይዘምራል።’
31 ‘ታላቅ ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ያስተጋባል፤ይሖዋ ከብሔራት ጋር ሙግት አለውና።
እሱ ራሱ በሰዎች* ሁሉ ላይ ይፈርዳል።+
ክፉዎችንም ለሰይፍ ይዳርጋል’ ይላል ይሖዋ።
32 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
‘እነሆ፣ ጥፋት ብሔራትን አንድ በአንድ ያዳርሳል፤+ታላቅ አውሎ ነፋስም ከምድር ዳርቻዎች ይነሳል።+
33 “‘በዚያም ቀን፣ ይሖዋ የገደላቸው ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ። አይለቀስላቸውም፣ አይሰበሰቡም ወይም አይቀበሩም። በምድር ላይ እንደ ፍግ ይሆናሉ።’
34 እናንተ እረኞች፣ ዋይ ዋይ በሉ፤ ጩኹም!
እናንተ በመንጋው መካከል ያላችሁ ታላላቆች፣ በአመድ ላይ ተንከባለሉ፤ምክንያቱም የምትታረዱበትና የምትበታተኑበት ጊዜ ደርሷል፤እንደ ውድ የሸክላ ዕቃ ትከሰከሳላችሁ!
35 እረኞቹ የሚሸሹበት ቦታ የለም፤በመንጋው መካከል ያሉት ታላላቆችም ማምለጫ የላቸውም።
36 አዳምጡ! የእረኞቹ ጩኸትናበመንጋው መካከል ያሉ ታላላቆች ዋይታ ይሰማል፤ይሖዋ ማሰማሪያቸውን እያወደመ ነውና።
37 ከሚነደው የይሖዋ ቁጣም የተነሳሰላማዊ የሆኑት የመኖሪያ ቦታዎች ሕይወት አልባ ሆነዋል።
38 እንደ ደቦል አንበሳ ከጎሬው ወጥቷል፤+ከጨካኙ ሰይፍናከሚነደው ቁጣው የተነሳምድራቸው የሚያስፈራ ቦታ ሆኗልና።”
የግርጌ ማስታወሻ
^ ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
^ ወይም “ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በሙሉ።”
^ ቃል በቃል “በማለዳ እየተነሳሁ ተናገርኩ።”
^ ቃል በቃል “በማለዳ እየተነሳ።”
^ ቃል በቃል “ናቡከደረጾርን።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
^ ወይም “እቀጣለሁ።”
^ በዓይንና በጆሮ መካከል ያለውን የአካል ክፍል ያመለክታል።
^ ባቤል (ባቢሎን) የምትጠራበት የሚስጥር ስም ሳይሆን አይቀርም።
^ ቃል በቃል “በሥጋ።”