ኤርምያስ 26:1-24
26 በኢዮስያስ ልጅ፣ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮዓቄም+ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ይህ ቃል ከይሖዋ ዘንድ መጣ፦
2 “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በይሖዋ ቤት ግቢ ውስጥ ቆመህ፣ ለአምልኮ* ወደ ይሖዋ ቤት ስለሚመጡት፣ በይሁዳ ከተሞች ስለሚኖሩት* ሰዎች ሁሉ ተናገር። የማዝህን ቃል ሁሉ ንገራቸው፤ አንዲትም ቃል አታስቀር።
3 ምናልባት ይሰሙና እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም በክፉ ሥራቸው የተነሳ በእነሱ ላይ ላመጣ ያሰብኩትን ጥፋት እተወዋለሁ።*+
4 እንዲህ በላቸው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የማትሰሙኝና የሰጠኋችሁን ሕግ* የማትከተሉ ከሆነ፣
5 እንዲሁም ደግሜ ደጋግሜ* ወደ እናንተ የላክኋቸውን፣ እናንተ ያልሰማችኋቸውን የአገልጋዮቼን የነቢያትን ቃል የማትቀበሉ ከሆነ፣+
6 ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፤+ ይህችንም ከተማ ለምድር ብሔራት ሁሉ እርግማን አደርጋታለሁ።’”’”+
7 ካህናቱ፣ ነቢያቱና ሕዝቡ ሁሉ ኤርምያስ በይሖዋ ቤት ይህን ቃል ሲናገር ሰሙ።+
8 በመሆኑም ኤርምያስ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ሁሉ እንዲናገር ያዘዘውን ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ ካህናቱ፣ ነቢያቱና ሕዝቡ ሁሉ ይዘው እንዲህ አሉት፦ “አንተ በእርግጥ ትሞታለህ።
9 ‘ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፤ ይህችም ከተማ ወድማ ሰው አልባ ትሆናለች’ ብለህ በይሖዋ ስም የተነበይከው ለምንድን ነው?” ሕዝቡም ሁሉ በይሖዋ ቤት በኤርምያስ ዙሪያ ተሰበሰበ።
10 የይሁዳ መኳንንት ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ ከንጉሡ ቤት* ወደ ይሖዋ ቤት መጥተው በይሖዋ ቤት ባለው በአዲሱ በር መግቢያ ተቀመጡ።+
11 ካህናቱና ነቢያቱ፣ ለመኳንንቱና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው በሞት ሊቀጣ ይገባዋል፤+ ምክንያቱም በገዛ ጆሯችሁ እንደሰማችሁት በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግሯል።”+
12 በዚህ ጊዜ ኤርምያስ ለመኳንንቱ ሁሉና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “የሰማችሁትን ቃል ሁሉ በዚህ ቤትና በዚህች ከተማ ላይ እንድተነብይ የላከኝ ይሖዋ ነው።+
13 እንግዲያው አሁን መንገዳችሁንና ድርጊታችሁን አስተካክሉ፤ የአምላካችሁንም የይሖዋን ቃል ስሙ፤ ይሖዋም በእናንተ ላይ አመጣዋለሁ ብሎ የተናገረውን ጥፋት ይተወዋል።*+
14 እኔ ግን በእጃችሁ ነኝ። መልካምና ትክክል መስሎ የታያችሁን ነገር ሁሉ አድርጉብኝ።
15 ከገደላችሁኝ በራሳችሁ፣ በዚህች ከተማና በነዋሪዎቿ ላይ የንጹሕ ሰው ደም ዕዳ እንደምታመጡ በእርግጥ እወቁ፤ ይህን ሁሉ ቃል በጆሯችሁ እንድናገር የላከኝ በእርግጥ ይሖዋ ነውና።”
16 በዚህ ጊዜ መኳንንቱና ሕዝቡ ሁሉ ካህናቱንና ነቢያቱን “ይህ ሰው የተናገረን በአምላካችን በይሖዋ ስም ስለሆነ በሞት ሊቀጣ አይገባውም” አሏቸው።
17 በተጨማሪም በምድሪቱ ከሚኖሩ ሽማግሌዎች መካከል አንዳንዶቹ ተነስተው ለተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አሉ፦
18 “የሞረሸቱ ሚክያስ+ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ+ ዘመን ትንቢት ይናገር ነበር፤ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብሎ ነበር፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
“ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፤ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤+የቤቱም* ተራራ፣ በጫካ እንዳሉ ከፍ ያሉ ቦታዎች* ይሆናል።”’+
19 “ታዲያ በዚያ ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ገደሉት? ይልቁንም ይሖዋን ፈርቶ፣ ይሖዋ እንዲራራለት አልተማጸነም? ከዚህስ የተነሳ ይሖዋ በእነሱ ላይ ሊያመጣ አስቦት የነበረውን ጥፋት አልተወውም?*+ እኛ ግን በራሳችን* ላይ ጥፋት እየጋበዝን ነው።
20 “ደግሞም በይሖዋ ስም ትንቢት የሚናገር ሌላ ሰው ነበር፤ እሱም የቂርያትየአሪም+ ሰው የሆነው የሸማያህ ልጅ ዑሪያህ ሲሆን ኤርምያስ የተናገረውን ዓይነት ቃል በመናገር በዚህች ከተማና በዚህች ምድር ላይ ተንብዮአል።
21 ንጉሥ ኢዮዓቄም፣+ ኃያል ተዋጊዎቹ ሁሉና መኳንንቱ ሁሉ እሱ የተናገረውን ቃል ሰሙ፤ ንጉሡም ሊገድለው ፈለገ።+ ዑሪያህ ይህን እንደሰማ በጣም ስለፈራ ሸሽቶ ወደ ግብፅ ሄደ።
22 በዚህ ጊዜ ንጉሥ ኢዮዓቄም የአክቦርን ልጅ ኤልናታንን+ እንዲሁም ከእሱ ጋር ሌሎች ሰዎችን ወደ ግብፅ ላከ።
23 እነሱም ዑሪያህን ከግብፅ አምጥተው ወደ ንጉሥ ኢዮዓቄም ወሰዱት፤ እሱም በሰይፍ መትቶ ገደለው፤+ አስከሬኑንም ተራ ሰዎች በሚቀበሩበት ስፍራ ጣለው።”
24 ይሁንና የሳፋን+ ልጅ አኪቃም+ ኤርምያስን ረዳው፤ በመሆኑም ኤርምያስ እንዲገደል ለሕዝቡ አልተሰጠም።+