ኤርምያስ 30:1-24

  • ወደ ቀድሞው ሁኔታ እንደሚመለሱና እንደሚፈወሱ የተነገረ ቃል (1-24)

30  ከይሖዋ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦  “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የምነግርህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፈው።  “እነሆ፣ ተማርከው የተወሰዱትን ሕዝቤን፣ እስራኤልንና ይሁዳን የምሰበስብበት ጊዜ ይመጣል”+ ይላል ይሖዋ፤ “ደግሞም ለአባቶቻቸው ወደሰጠኋት ምድር መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ እነሱም ዳግመኛ ይወርሷታል” ይላል ይሖዋ።’”+  ይሖዋ ለእስራኤልና ለይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው።   ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የሚንቀጠቀጡ ሰዎችን ድምፅ ሰምተናል፤ሽብር ነግሦአል፤ ሰላምም የለም።   ወንድ፣ መውለድ ይችል እንደሆነ እስቲ ጠይቁ። ታዲያ ብርቱ የሆነ ወንድ ሁሉ፣ልትወልድ እንደተቃረበች ሴት+ እጁን ሆዱ* ላይ አድርጎ የማየው ለምንድን ነው? የሰዉ ሁሉ ፊት የገረጣው ለምንድን ነው?   ወዮ! ያ ቀን አስፈሪ* ነውና።+ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቀን ነው፤ለያዕቆብ የጭንቅ ጊዜ ይሆናል። ሆኖም ከዚያ ቀን ይተርፋል።”  “በዚያም ቀን፣” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ “ቀንበሩን ከአንገትህ ላይ እሰብራለሁ፤ ማሰሪያህንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህ እንግዶች* ባሪያቸው አያደርጉትም።*  እነሱም አምላካቸውን ይሖዋንና የማስነሳላቸውን ንጉሣቸውን ዳዊትን ያገለግላሉ።”+ 10  “አንተም አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፣ አትፍራ” ይላል ይሖዋ፤“እስራኤል ሆይ፣ አትሸበር።+ አንተን ከሩቅ አገር፣ዘርህንም ተማርኮ ከተወሰደበት ምድር እታደጋለሁና።+ ያዕቆብ ይመለሳል፤ ሳይረበሽም ተረጋግቶ ይቀመጣል፤የሚያስፈራቸው አይኖርም።”+ 11  “እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና” ይላል ይሖዋ። “አንተን የበተንኩባቸውን ብሔራት ሁሉ ግን ፈጽሞ አጠፋቸዋለሁ፤+ይሁን እንጂ አንተን ሙሉ በሙሉ አላጠፋህም።+ በተገቢው መጠን እገሥጽሃለሁ* እንጂበምንም ዓይነት ሳልቀጣ አልተውህም።”+ 12  ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “ስብራትሽ ፈውስ የለውም።+ ቁስልሽ የማይድን ነው። 13  የሚሟገትልሽ የለም፤ቁስልሽ በምንም መንገድ ሊድን አይችልም። ለአንቺ የሚሆን ፈውስ የለም። 14  አጥብቀው የሚወዱሽ ሁሉ ረስተውሻል።+ ከእንግዲህ አይፈልጉሽም። ከባድ በደል ስለፈጸምሽና ብዙ ኃጢአት ስለሠራሽጠላት በሚማታበት መንገድ መትቼሻለሁና፤+እንደ ጨካኝ ቀጥቼሻለሁ።+ 15  ከስብራትሽ የተነሳ የምትጮኺው ለምንድን ነው? ሕመምሽ የማይፈወስ ሆኗል! ከባድ በደል ስለፈጸምሽና ብዙ ኃጢአት ስለሠራሽ+ይህን አድርጌብሻለሁ። 16  በእርግጥ የሚውጡሽ ሁሉ ይዋጣሉ፤+ጠላቶችሽም ሁሉ በምርኮ ይወሰዳሉ።+ የሚዘርፉሽ ሁሉ ይዘረፋሉ፤የሚበዘብዙሽንም ሁሉ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣለሁ።”+ 17  “ይሁንና ጤንነትሽን እመልስልሻለሁ፤ ቁስሎችሽንም እፈውሳለሁ”+ ይላል ይሖዋ፤“እነሱ ግን የተገለለች፣ ‘ማንም የማይፈልጋት ጽዮን’ ብለውሻል።”+ 18  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ ከያዕቆብ ድንኳኖች የተማረኩትን እሰበስባለሁ፤+ለማደሪያ ድንኳኖቹም እራራለሁ። ከተማዋ በጉብታዋ ላይ ዳግም ትገነባለች፤+የማይደፈረውም ማማ በተገቢው ቦታ ላይ ይቆማል። 19  ከእነሱም የምስጋናና የሳቅ ድምፅ ይሰማል።+ እኔ አበዛቸዋለሁ፤ እነሱም ጥቂት አይሆኑም፤+ቁጥራቸው እንዲጨምር* አደርጋለሁ፤የተናቁም አይሆኑም።+ 20  ወንዶች ልጆቹ እንደቀድሞው ጊዜ ይሆናሉ፤ጉባኤውም በፊቴ ጸንቶ ይመሠረታል።+ እሱን በሚጨቁኑት ሁሉ ላይ ትኩረቴን አደርጋለሁ።+ 21  ታላቅ ግርማ የተላበሰው መሪ ከራሱ ወገን ይገኛል፤ገዢውም ከመካከሉ ይወጣል። ወደ እኔ እንዲቀርብ እፈቅድለታለሁ፤ እሱም ወደ እኔ ይቀርባል።” “አለዚያ ወደ እኔ ለመቅረብ የሚደፍር* ማን ነው?” ይላል ይሖዋ። 22  “እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤+ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ።”+ 23  እነሆ፣ የይሖዋ አውሎ ነፋስ በታላቅ ቁጣ ይነሳል፤+በክፉዎች ራስ ላይ እየተሽከረከረ የሚወርድ ኃይለኛ ነፋስ ይነፍሳል። 24  ይሖዋ የልቡን ሐሳብ ሳያከናውንና ሳይፈጽም፣የሚነደው ቁጣው አይመለስም።+ በዘመኑ መጨረሻ ይህን ትረዳላችሁ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ወገቡ።”
ቃል በቃል “ታላቅ።”
ወይም “ባዕዳን።”
ወይም “ባሪያዎቻቸው አያደርጓቸውም።”
ወይም “አርምሃለሁ።”
“እንዲከበሩ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ልቡን መያዣ አድርጎ የሚሰጥ።”