ኤርምያስ 4:1-31
4 “እስራኤል ሆይ፣ ብትመለስ” ይላል ይሖዋ፣“ወደ እኔ ብትመለስ፣አስጸያፊ ጣዖቶችህን ከፊቴ ብታስወግድተንከራታች አትሆንም።+
2 ‘በእውነት፣ በፍትሕና በጽድቅሕያው ይሖዋን!’ ብለህ ብትምል፣ብሔራት በእሱ አማካኝነት በረከት ያገኛሉ፤በእሱም ይኮራሉ።”+
3 ይሖዋ ለይሁዳ ሰዎችና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላልና፦
“ያልለማውን መሬት እረሱ፤በእሾህ መካከልም አትዝሩ።+
4 እናንተ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ለይሖዋ ተገረዙ፤የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ፤+አለዚያ በክፉ ሥራችሁ የተነሳቁጣዬ እንደ እሳት ይነድዳል፤ማንም ሊያጠፋው አይችልም።”+
5 ይህን በይሁዳ ተናገሩ፤ በኢየሩሳሌምም አውጁ።
ጩኹ፤ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ቀንደ መለከት ንፉ።+
ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዲህ በሉ፦ “አንድ ላይ ተሰብሰቡ፤ወደተመሸጉት ከተሞችም እንሽሽ።+
6 ወደ ጽዮን የሚጠቁም ምልክት* አቁሙ።
መጠለያ ፈልጉ፤ ዝም ብላችሁም አትቁሙ።”
ከሰሜን ጥፋት ብሎም ታላቅ መዓት አመጣለሁና።+
7 ጠላት እንደ አንበሳ ከጥሻው ውስጥ ወጥቷል፤+ብሔራትንም የሚያጠፋው ተነስቷል።+
ምድርሽን አስፈሪ ቦታ ሊያደርግ ከቦታው ወጥቷል።
ከተሞችሽ አንድም ሰው የማይኖርባቸው የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ።+
8 ስለዚህ ማቅ ልበሱ፤+እዘኑ፤* ዋይ ዋይም በሉ፤ምክንያቱም የሚነደው የይሖዋ ቁጣ ከእኛ አልተመለሰም።
9 “በዚያ ቀን” ይላል ይሖዋ፣ “የንጉሡ ልብናየመኳንንቱ ልብ ይቀልጣል፤*+ካህናቱም ይሸበራሉ፤ ነቢያቱም ይገረማሉ።”+
10 ከዚያም እንዲህ አልኩ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ወዮ! ሰይፍ አንገታችን ላይ ተጋድሞ* እያለ ‘ሰላም ታገኛላችሁ’+ ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ አታለሃል።”+
11 በዚያን ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይባላል፦
“የሚለበልብ ነፋስ በበረሃ ከሚገኙ ጠፍ ኮረብቶች ተነስቶወደ ሕዝቤ ሴት ልጅ* በፍጥነት ይነፍሳል፤ነፋሱ የሚነፍሰው እህል ለማዝራትም* ሆነ ለማጥራት አይደለም።
12 በእኔ ትእዛዝ ኃይለኛው ነፋስ ከእነዚህ ስፍራዎች ይመጣል።
አሁን በእነሱ ላይ ፍርድ አስተላልፋለሁ።
13 እነሆ፣ እሱ ዝናብ እንዳዘሉ ደመናት ይመጣል፤ሠረገሎቹም እንደ አውሎ ነፋስ ናቸው።+
ፈረሶቹ ከንስር ይበልጥ ፈጣኖች ናቸው።+
ጠፍተናልና ወዮልን!
14 ኢየሩሳሌም ሆይ፣ እንድትድኚ ልብሽን ከክፋት ሁሉ አጥሪ።+
እስከ መቼ በውስጥሽ ክፉ ሐሳብ ይዘሽ ትኖሪያለሽ?
15 አንድ ድምፅ ከዳን ዜናውን ይናገራልና፤+ከኤፍሬም ተራሮችም ጥፋትን ያውጃል።
16 ይህን አሳውቁ፤ አዎ ለብሔራት ተናገሩ፤በኢየሩሳሌም ላይ አውጁ።”
“ጠባቂዎች* ከሩቅ አገር እየመጡ ነው፤በይሁዳ ከተሞችም ላይ ይጮኻሉ።
17 ማሳ እንደሚጠብቁ ሰዎች ከሁሉም አቅጣጫ ይመጡባታል፤+ምክንያቱም እሷ በእኔ ላይ ዓምፃለች”+ ይላል ይሖዋ።
18 “ለተከተልሽው መንገድና ለፈጸምሽው ተግባር ዋጋሽን ትቀበያለሽ።+
የሚደርስብሽ ጥፋት ምንኛ መራራ ነው፤ወደ ልብሽ ዘልቆ ይገባልና!”
19 ወይ አበሳዬ!* ወይ አበሳዬ!
ልቤን ሥቃይ ቀስፎታል።
ልቤ በውስጤ በኃይል ይመታል።
ዝም ማለት አልችልም፤የቀንደ መለከት ድምፅ፣የጦርነት ማስጠንቀቂያ ድምፅ* ሰምቻለሁና።*+
20 በጥፋት ላይ ጥፋት መድረሱ ተወርቷል፤ምድሪቱ በሙሉ ወድማለችና።
የገዛ ድንኳኖቼ በድንገት፣የድንኳን ሸራዎቼም በቅጽበት ጠፍተዋል።+
21 ምልክቱን* የማየውናየቀንደ መለከቱን ድምፅ የምሰማው እስከ መቼ ድረስ ነው?+
22 “ሕዝቤ ሞኝ ነውና፤+እነሱ ለእኔ ትኩረት አይሰጡም።
ማስተዋል የሌላቸው ቂል ልጆች ናቸው።
ክፉ ነገር ለማድረግ ብልሃተኞች* ናቸው፤መልካም ነገር ማድረግ ግን አያውቁም።”
23 ምድሪቱን አየሁ፤ እነሆም፣ ባዶና ወና ነበረች።+
ወደ ሰማያት ተመለከትኩ፤ ብርሃናቸው ጠፍቶ ነበር።+
24 ተራሮቹን አየሁ፤ እነሆ፣ ይናወጡ ነበር፤ኮረብቶቹም ይንቀጠቀጡ ነበር።+
25 እኔም ተመለከትኩ፤ እነሆ፣ በዚያ አንድም ሰው አልነበረም፤የሰማይ ወፎችም ሁሉ ሸሽተው ነበር።+
26 እኔም አየሁ፤ እነሆ፣ የፍራፍሬ እርሻው ምድረ በዳ ሆኖ ነበር፤ከተሞቹም ሁሉ ፈራርሰው ነበር።+
ይህም የሆነው በይሖዋ፣በሚነደውም ቁጣው የተነሳ ነው።
27 ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “ምድሪቱ በሙሉ ባድማ ትሆናለች፤+ሆኖም ፈጽሜ አላጠፋትም።
28 ከዚህ የተነሳ ምድሪቱ ታዝናለች፤+በላይ ያሉት ሰማያትም ይጨልማሉ።+
ምክንያቱም እኔ ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም ወስኛለሁ፤ሐሳቤንም አለውጥም፤* ወደ ኋላም አልመለስም።+
29 ከፈረሰኞቹና ከቀስተኞቹ ድምፅ የተነሳከተማዋ በሙሉ ትሸሻለች።+
ጥሻ ውስጥ ይገባሉ፤ዓለቶቹም ላይ ይወጣሉ።+
ከተሞቹ ሁሉ ተትተዋል፤የሚኖርባቸውም ሰው የለም።”
30 ለጥፋት ተዳርገሻል፤ ታዲያ ምን ታደርጊ ይሆን?
ደማቅ ቀይ ልብስ ትጎናጸፊ፣በወርቅ ጌጣጌጦች ታጌጪናዓይኖችሽን ትኳዪ ነበር።
ይሁንና ትዋቢ የነበረው እንዲያው በከንቱ ነው፤+በፍትወት ስሜት ይከተሉሽ የነበሩት ትተውሻልና፤አሁን ሕይወትሽን* ይሿታል።+
31 እንደታመመች ሴት ድምፅ፣የመጀመሪያ ልጇንም ለመውለድ እንደምታምጥ ሴት ያለ የጭንቅ ድምፅ፣ደግሞም ትንፋሽ አጥሯት ቁና ቁና የምትተነፍሰውን የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ ሰምቻለሁና።
እሷም እጆቿን ዘርግታ+
“ወዮልኝ! ከገዳዮች የተነሳ ዝያለሁና”* ትላለች።
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”
^ ወይም “ደረታችሁን ምቱ።”
^ ወይም “መኳንንቱ ወኔ ይከዳቸዋል።”
^ ወይም “ሰይፍ ነፍሳችን ላይ ደርሶ።”
^ በሰውኛ ዘይቤ የተገለጸ ቅኔያዊ አነጋገር፤ አዘኔታን ወይም ርኅራኄን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
^ እህልን ወደ ላይ በመበተንና ለነፋስ በመስጠት ከገለባ መለየት።
^ ቃል በቃል “ተመልካቾች።” መቼ ጥቃት መሰንዘር እንዳለባቸው ለመወሰን ከተማዋን የሚቃኙ ሰዎችን ያመለክታል።
^ ቃል በቃል “አንጀቴ።”
^ “የውጊያ ሁካታ ድምፅ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ነፍሴ ሰምታለችና።”
^ ወይም “ለምልክት የሚተከለውን ምሰሶ።”
^ ወይም “ጥበበኞች።”
^ ወይም “አልጸጸትም።”
^ ወይም “ነፍስሽን።”
^ ወይም “ነፍሴ ዝላለችና።”