ኤርምያስ 51:1-64

  • በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት (1-64)

    • ባቢሎን በድንገት በሜዶናውያን እጅ ትወድቃለች (8-12)

    • መጽሐፉ ኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ ተወረወረ (59-64)

51  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በባቢሎንና+ በሌብቃማይ* ነዋሪዎች ላይአጥፊ ነፋስ አስነሳለሁ።   እህል የሚያዘሩ* ሰዎችን ወደ ባቢሎን እሰዳለሁ፤እነሱም ያዘሯታል፤ ምድሯንም ባዶ ያደርጋሉ፤በጥፋት ቀን ከሁሉም አቅጣጫ ይመጡባታል።+   ቀስተኛው ደጋኑን አይወጥር።* በተጨማሪም ማንም ሰው ጥሩሩን ለብሶ አይነሳ። ለወጣቶቿ ምንም ዓይነት ርኅራኄ አታሳዩ።+ ሠራዊቷን ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ።   እነሱም በከለዳውያን ምድር ታርደው፣በጎዳናዎቿም ላይ ክፉኛ ቆስለው ይወድቃሉ።+   እስራኤልና ይሁዳ ከአምላካቸው፣ ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ተለይተው መበለት አልሆኑም።+ ምድራቸው* ግን በእስራኤል ቅዱስ ፊት በበደል ተሞልታለች።   ከባቢሎን መካከል ሸሽታችሁ ውጡ፤ሕይወታችሁን* አድኑ።+ በእሷ በደል የተነሳ አትጥፉ። ይህ የይሖዋ የበቀል ጊዜ ነውና። ላደረገችው ነገር የእጇን ይከፍላታል።+   ባቢሎን በይሖዋ እጅ ያለች የወርቅ ጽዋ ነበረች፤ምድርን ሁሉ አሰከረች። ብሔራት ወይን ጠጇን ጠጥተው ሰከሩ፤+ብሔራት ያበዱት ለዚህ ነው።+   ባቢሎን በድንገት ወድቃ ተሰበረች።+ ዋይ ዋይ በሉላት!+ ለሕመሟ የሚሆን በለሳን ውሰዱላት፤ ምናልባት ትፈወስ ይሆናል።”   “ባቢሎንን ለመፈወስ ሞክረን ነበር፤ እሷ ግን ልትፈወስ አልቻለችም። ትታችኋት ሂዱ፤ እያንዳንዳችንም ወደ ገዛ ምድራችን እንሂድ።+ ፍርዷ እስከ ሰማያት ደርሷልና፤እስከ ደመናት ድረስ ከፍ ብሏል።+ 10  ይሖዋ ፍትሕ አስፍኖልናል።+ ኑ፣ የአምላካችንን የይሖዋን ሥራ በጽዮን እንናገር።”+ 11  “ፍላጻዎቻችሁን አሹሉ፤+ ክብ የሆኑትን ጋሻዎች አንሱ።* ይሖዋ የሜዶናውያንን ነገሥታት መንፈስ አነሳስቷል፤+ምክንያቱም ባቢሎንን ለማጥፋት አስቧል። ይህ የይሖዋ በቀል ይኸውም ስለ ቤተ መቅደሱ የሚወስደው የበቀል እርምጃ ነውና። 12  የባቢሎንን ቅጥሮች ለማጥቃት ምልክት* አቁሙ።+ ጥበቃውን አጠናክሩ፤ ጠባቂዎችን አቁሙ። ሽምቅ ተዋጊዎችን አዘጋጁ። ይሖዋ በባቢሎን ነዋሪዎች ላይ የጦር ስልት ነድፏልና፤በእነሱ ላይ የተናገረውንም ቃል ይፈጽማል።”+ 13  “አንቺ በብዙ ውኃዎች ላይ የምትኖሪ፣+በሀብትም የበለጸግሽ ሆይ፣+መጨረሻሽ ቀርቧል፤ አላግባብ የምታገኚው ትርፍ ገደቡ ላይ ደርሷል።+ 14  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ሲል በራሱ* ምሏል፦‘እንደ አንበጣ ብዛት ባላቸው ሰዎች እሞላሻለሁ፤እነሱም በአንቺ ላይ በድል አድራጊነት ይጮኻሉ።’+ 15  ምድርን በኃይሉ የሠራው፣ፍሬያማ የሆነችውን መሬት በጥበቡ የመሠረተውና+ሰማያትን በማስተዋሉ የዘረጋው እሱ ነው።+ 16  ድምፁን ሲያሰማበሰማያት ያሉ ውኃዎች ይናወጣሉ፤ደመና* ከምድር ዳርቻዎች ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርጋል። በዝናብ ጊዜ መብረቅን ያበርቃል፤*ነፋሱንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።+ 17  እያንዳንዱ ሰው ማስተዋልና እውቀት የጎደለው ድርጊት ይፈጽማል። እያንዳንዱ አንጥረኛ፣ በተቀረጸው ምስል የተነሳ ኀፍረት ይከናነባል፤+ከብረት የተሠራው ምስሉ* ሐሰት ነውና፤በውስጣቸውም መንፈስ* የለም።+ 18  እነሱ ከንቱና*+ መሳለቂያ ናቸው። የሚመረመሩበት ቀን ሲመጣ ይጠፋሉ። 19  የያዕቆብ ድርሻ ግን እንደነዚህ ነገሮች አይደለም፤እሱ የርስቱን በትር ጨምሮየሁሉ ነገር ሠሪ ነውና።+ ስሙ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው።”+ 20  “አንቺ ለእኔ እንደ ቆመጥ፣ እንደ ጦር መሣሪያም ነሽ፤በአንቺ ብሔራትን አደቃለሁ። በአንቺ መንግሥታትን አወድማለሁ። 21  በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን አደቃለሁ። በአንቺ የጦር ሠረገላውንና ነጂውን አደቃለሁ። 22  በአንቺ ወንድንና ሴትን አደቃለሁ። በአንቺ ሽማግሌንና ልጅን አደቃለሁ። በአንቺ ወጣቱንና ወጣቷን አደቃለሁ። 23  በአንቺ እረኛንና መንጋውን አደቃለሁ። በአንቺ ገበሬንና ጥማድ ከብቶቹን አደቃለሁ። በአንቺ ገዢዎችንና የበታች ገዢዎችን አደቃለሁ። 24  ደግሞም በጽዮን፣ በፊታችሁ ለሠሩት ክፋት ሁሉባቢሎንንና የከለዳውያን ምድር ነዋሪዎችን በሙሉ ዋጋቸውን እከፍላቸዋለሁ”+ ይላል ይሖዋ። 25  “አንቺ ምድርን ሁሉ ያጠፋሽ፣+አጥፊ ተራራ ሆይ፣ እነሆ እኔ በአንቺ ላይ ተነስቻለሁ”+ ይላል ይሖዋ። “በአንቺ ላይ እጄን እዘረጋለሁ፤ ከቋጥኞችም ላይ አንከባልልሻለሁ፤የተቃጠለም ተራራ አደርግሻለሁ።” 26  “ሰዎች የማዕዘን ድንጋይም ሆነ የመሠረት ድንጋይ ከአንቺ አይወስዱም፤ምክንያቱም አንቺ ለዘላለም ባድማ ትሆኛለሽ”+ ይላል ይሖዋ። 27  “በምድሪቱ ላይ ምልክት* አቁሙ።+ በብሔራት መካከል ቀንደ መለከት ንፉ። በእሷ ላይ እንዲዘምቱ ብሔራትን መድቡ።* የአራራት፣+ የሚኒ እና የአሽከናዝ መንግሥታት+ እሷን እንዲወጉ ሰብስቧቸው። በላይዋም ወታደሮችን የሚመለምል መኮንን ሹሙባት። ፈረሶችንም እንደ ኩብኩባ ስደዱባት። 28  ብሔራትን፣ የሜዶንን+ ነገሥታት፣ ገዢዎቿን፣ የበታች ገዢዎቿን ሁሉናበእያንዳንዳቸው ግዛት ሥር ያለውን ምድር ሁሉበእሷ ላይ እንዲዘምቱ መድቧቸው።* 29  ምድርም ትናወጣለች፤ ትንቀጠቀጣለችም፤ይሖዋ የባቢሎንን ምድር አስፈሪ ቦታና ሰው አልባ ለማድረግበባቢሎን ላይ ያሰበው ሐሳብ ይፈጸማልና።+ 30  የባቢሎን ተዋጊዎች መዋጋት አቁመዋል። በምሽጎቻቸው ውስጥ ይቀመጣሉ። ጉልበት ከድቷቸዋል።+ እንደ ሴት ሆነዋል።+ መኖሪያዎቿ በእሳት ነደዋል። መቀርቀሪያዎቿ ተሰብረዋል።+ 31  ከተማው በየአቅጣጫው እንደተያዘች ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገርአንዱ መልእክተኛ ሲሮጥ ከሌላው መልእክተኛ ጋር፣አንዱም ወሬ ነጋሪ ሲሮጥ ከሌላው ወሬ ነጋሪ ጋር ይገናኛል፤+ 32  መልካዎቹ* እንደተያዙ፣+የደንገል ጀልባዎቹ በእሳት እንደተቃጠሉናወታደሮቹ እንደተሸበሩ ሊነግሩት ይሯሯጣሉ።” 33  የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “የባቢሎን ሴት ልጅ እንደ አውድማ ናት። ይህ በኃይል የምትረገጥበት ጊዜ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ የመከር ወቅት ይደርስባታል።” 34  “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* ዋጠኝ፤+ጨርሶ ግራ አጋባኝ። እንደ ባዶ ዕቃ አደረገኝ። እንደ ትልቅ እባብ ዋጠኝ፤+የእኔን መልካም ነገሮች በልቶ ሆዱን ሞላ። በውኃም ጠራርጎ አስወገደኝ። 35  የጽዮን ነዋሪ ‘በእኔና በአካሌ ላይ የተፈጸመው ግፍ በባቢሎን ላይ ይድረስ!’ ትላለች።+ ኢየሩሳሌም ‘ደሜም በከለዳውያን ምድር ነዋሪዎች ላይ ይሁን!’ ትላለች።” 36  ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ እኔ እሟገትልሻለሁ፤+ደግሞም እበቀልልሻለሁ።+ ባሕሯን አደርቃለሁ፤ የውኃ ጉድጓዶቿንም ደረቅ አደርጋለሁ።+ 37  ባቢሎንም የድንጋይ ቁልል፣+የቀበሮዎች ጎሬ፣+አስፈሪ ቦታና ማፏጫ ትሆናለች፤የሚኖርባትም አይገኝም።+ 38  ሁሉም በአንድነት እንደ ደቦል አንበሳ ያገሳሉ። እንደ አንበሳ ግልገሎች ያጉረመርማሉ።” 39  “ፍላጎታቸው በኃይል ሲነሳሳ እጅግ ደስ እንዲሰኙድግሳቸውን አዘጋጅላቸዋለሁ፤ እንዲሰክሩም አደርጋለሁ፤+ከዚያም ጨርሶ ላይነቁእስከ ወዲያኛው ያንቀላፋሉ”+ ይላል ይሖዋ። 40  “እንደ ጠቦቶች፣እንደ አውራ በጎችም ከፍየሎች ጋር ወደሚታረዱበት ቦታ አወርዳቸዋለሁ።” 41  “ሼሻቅ* እንዴት ተማረከች!+የምድር ሁሉ ‘ውዳሴ’ እንዴት ተያዘች!+ ባቢሎን በብሔራት መካከል ምንኛ አስፈሪ ቦታ ሆነች! 42  ባሕሩ ባቢሎንን አጥለቅልቋታል። በማዕበሉ ብዛት ተሸፍናለች። 43  ከተሞቿ አስፈሪ ቦታ እንዲሁም ውኃ የሌለበት ምድርና በረሃ ሆነዋል። ማንም ሰው የማይኖርበትና አንድም ሰው የማያልፍበት ምድር ሆነዋል።+ 44  ትኩረቴን በባቢሎን በሚገኘው በቤል+ ላይ አደርጋለሁ፤የዋጠውንም ከአፉ አስተፋዋለሁ።+ ብሔራት ከእንግዲህ ወደ እሱ አይጎርፉም፤የባቢሎንም ቅጥር ይፈርሳል።+ 45  ሕዝቤ ሆይ፣ ከመካከሏ ውጡ!+ ከሚነደው የይሖዋ ቁጣ+ ሕይወታችሁን* ለማትረፍ ሽሹ!+ 46  በምድሪቱ ላይ በሚሰማው ወሬ ልባችሁ አይሸበር፤ በፍርሃትም አትዋጡ። በምድሪቱ ላይ ዓመፅ ስለመኖሩ፣ገዢም በገዢ ላይ ስለመነሳቱ፣ በአንደኛው ዓመት አንድ ወሬ ይሰማል፤በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ሌላ ወሬ ይናፈሳል። 47  ስለዚህ፣ እነሆ ትኩረቴንበባቢሎን የተቀረጹ ምስሎች ላይ የማደርግበት ጊዜ ይመጣል። ምድሪቱ በሙሉ ኀፍረት ትከናነባለች፤የታረዱባትም ሰዎች ሁሉ በመካከሏ ይወድቃሉ።+ 48  ሰማያትና ምድር እንዲሁም በውስጣቸው ያሉት ሁሉበባቢሎን የተነሳ እልል ይላሉ፤+አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና”+ ይላል ይሖዋ። 49  “ባቢሎን ተጠያቂ የሆነችው ታርደው ለወደቁት እስራኤላውያን ብቻ አይደለም፤+ከዚህ ይልቅ ከመላው ምድር የመጡ ሰዎችም በባቢሎን ታርደው ወድቀዋል። 50  እናንተ ከሰይፍ ያመለጣችሁ፣ መንገዳችሁን ቀጥሉ፤ ፈጽሞ አትቁሙ!+ በሩቅ ቦታ ሆናችሁ ይሖዋን አስታውሱ፤ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡ።”+ 51  “ዘለፋውን ስለሰማን በኀፍረት ተውጠናል። ባዕድ ሰዎች* በይሖዋ ቤት ባሉት ቅዱስ ስፍራዎች ላይ ስለተነሱውርደት ፊታችንን ሸፍኖታል።”+ 52  “ስለዚህ፣ እነሆ ትኩረቴንበተቀረጹ ምስሎቿ ላይ የማደርግበት ጊዜ ይመጣል” ይላል ይሖዋ፤“በምድሪቱም ሁሉ፣ የቆሰሉት ሰዎች ያቃስታሉ።”+ 53  “ባቢሎን ወደ ሰማያት ብትወጣ፣+ከፍ ያሉ ምሽጎቿንም ብታጠናክር እንኳ፣እሷን የሚያጠፉ ከእኔ ዘንድ ይመጡባታል”+ ይላል ይሖዋ። 54  “ስሙ! ከባቢሎን ጩኸት፣+ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ይሰማል፤+ 55  ይሖዋ ባቢሎንን ያጠፋልና፤ታላቅ ድምፅዋን ጸጥ ያሰኛል፤ሞገዳቸውም እንደ ብዙ ውኃዎች ያስተጋባል። የድምፃቸው ጩኸት ይሰማል። 56  በባቢሎን ላይ አጥፊ ይመጣልና፤+ተዋጊዎቿ ይያዛሉ፤+ቀስቶቻቸው ይሰባበራሉ፤ይሖዋ የሚበቀል አምላክ ነውና።+ በእርግጥ ብድራትን ይመልሳል።+ 57  መኳንንቷንና ጥበበኞቿን፣ገዢዎቿንና የበታች ገዢዎቿን እንዲሁም ተዋጊዎቿን አሰክራለሁ፤+እነሱም ጨርሶ ላይነቁእስከ ወዲያኛው ያንቀላፋሉ”+ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ የሆነው ንጉሥ። 58  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎን ቅጥር ሰፊ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ይፈርሳል፤+በሮቿ ረጃጅም ቢሆኑም በእሳት ይጋያሉ። ሰዎቹ በከንቱ ይደክማሉ፤ብሔራትም እሳት ለሚበላው ነገር ራሳቸውን እንዲሁ ያደክማሉ።”+ 59  የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የማህሴያህ ልጅ፣ የነሪያህ+ ልጅ ሰራያህ ከንጉሡ ጋር ወደ ባቢሎን በተጓዘ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ ለእሱ የሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፤ ሰራያህ የቤተ መንግሥት አስተዳዳሪ ነበር። 60  ኤርምያስ በባቢሎን ላይ የሚመጣውን ጥፋት ሁሉ፣ ደግሞም በባቢሎን ላይ ስለሚደርሰው ነገር የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ በአንድ መጽሐፍ ላይ ጻፈው። 61  በተጨማሪም ኤርምያስ ሰራያህን እንዲህ አለው፦ “ባቢሎን ስትደርስና ከተማዋን ስታይ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ይህን ቃል ሁሉ አንብብ። 62  ከዚያም እንዲህ በል፦ ‘ይሖዋ ሆይ፣ ይህች ስፍራ እንደምትጠፋና ሰውም ሆነ እንስሳ፣ አንድም የሚኖርባት እንደማይገኝ፣ እንዲሁም ለዘላለም ባድማ እንደምትሆን ተናግረሃል።’+ 63  ይህን መጽሐፍ አንብበህ ከጨረስክ በኋላም መጽሐፉን ከድንጋይ ጋር አስረህ ኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ ወርውረው። 64  ከዚያም እንዲህ በል፦ ‘ባቢሎን በእሷ ላይ ከማመጣው ጥፋት የተነሳ እንዲህ ትሰምጣለች፤ ዳግመኛም አትነሳም፤+ እነሱም ይዝላሉ።’”+ የኤርምያስ ቃል እዚህ ላይ ያበቃል።

የግርጌ ማስታወሻ

የከለዳውያን ምድር የምትጠራበት የሚስጥር ስም ሳይሆን አይቀርም።
እህልን ወደ ላይ በመበተንና ለነፋስ በመስጠት ከገለባ መለየት።
ቃል በቃል “አይርገጥ።”
የከለዳውያንን ምድር ያመለክታል።
ወይም “ነፍሳችሁን።”
“የፍላጻ ኮሮጆዎቹን ሙሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”
ወይም “በነፍሱ።”
ወይም “ተን።”
“ለዝናብ መውጫ ያዘጋጃል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቀልጦ የተሠራው ሐውልቱ።”
ወይም “እስትንፋስ።”
ወይም “ዋጋ ቢስና።”
ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”
ቃል በቃል “ቀድሱ።”
ቃል በቃል “ቀድሷቸው።”
ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።
ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ባቤል (ባቢሎን) የምትጠራበት የሚስጥር ስም ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “ነፍሳችሁን።”
ወይም “እንግዶች።”