ኤርምያስ 9:1-26

  • ኤርምያስ የተሰማው ጥልቅ ሐዘን (1-3ሀ)

  • ይሖዋ ይሁዳን ተጠያቂ አደረገ (3ለ-16)

  • ከጽዮን የተሰማ የሐዘን እንጉርጉሮ (17-22)

  • “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በማወቁ ይኩራራ” (23-26)

9  ምነው ራሴ በውኃ በተሞላ!ዓይኖቼ የእንባ ምንጭ በሆኑ!+ ለታረዱት ወገኖቼቀን ከሌት ባለቀስኩ ነበር።   ምነው በምድረ በዳ ለተጓዦች የሚሆን ማረፊያ ቦታ ባገኘሁ ኖሮ! በዚያን ጊዜ ሕዝቤን ትቼና ከእነሱ ተለይቼ በሄድኩ ነበር፤ሁሉም አመንዝሮች፣+የከዳተኞች ጥርቅም ሆነዋልና።   ምላሳቸውን እንደ ደጋን ወጠሩ፤በምድሪቱ ላይ ታማኝነት ሳይሆን ውሸት ሰፍኗል።+ “በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ፤እኔንም ጨርሶ አይሰሙም”+ ይላል ይሖዋ።   “እያንዳንዳችሁ ራሳችሁን ከባልንጀራችሁ ጠብቁ፤ወንድማችሁን እንኳ ሳይቀር አትመኑ። እያንዳንዱ ወንድም ከሃዲ ነውና፤+እያንዳንዱ ባልንጀራም ስም አጥፊ ነው።+   እያንዳንዱ ባልንጀራውን ያታልላል፤አንድም ሰው እውነትን አይናገርም። ምላሳቸውን ውሸት መናገር አስተምረውታል።+ ትክክል ያልሆነ ነገር በማድረግ ራሳቸውን ያደክማሉ።   የምትኖረው አታላይ በሆኑ ሰዎች መካከል ነው። አታላይ ከመሆናቸውም የተነሳ እኔን ለማወቅ እንቢተኞች ሆነዋል” ይላል ይሖዋ።   ስለዚህ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እኔ አቀልጣቸዋለሁ፤ ደግሞም እፈትናቸዋለሁ፤+ከሕዝቤ ሴት ልጅ ጋር በተያያዘ ከዚህ ሌላ ምን ማድረግ እችላለሁ?   ምላሳቸው ማታለያ የሚናገር፣ ገዳይ ፍላጻ ነው። ሰው በአፉ ለባልንጀራው ስለ ሰላም ይናገራል፤በውስጡ ግን ለማጥቃት ያደባል።”   “ታዲያ በእነዚህ ነገሮች የተነሳ ተጠያቂ ላደርጋቸው አይገባም?” ይላል ይሖዋ። “እንዲህ ዓይነቱን ሕዝብ ልበቀል* አይገባም?+ 10  በተራሮቹ የተነሳ አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይም እላለሁ፤በምድረ በዳ ባሉት ማሰማሪያዎችም የተነሳ ሙሾ አወርዳለሁ፤*ማንም ሰው እንዳያልፍባቸው በእሳት ተቃጥለዋልና፤የከብቶችም ድምፅ አይሰማም። የሰማይ ወፎችና የዱር አራዊት ሸሽተዋል፤ ከአካባቢው ጠፍተዋል።+ 11  ኢየሩሳሌምን የድንጋይ ክምር፣+ የቀበሮም ጎሬ አደርጋታለሁ፤+የይሁዳንም ከተሞች ሰው የማይኖርበት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።+ 12  ይህን ይረዳ ዘንድ ጥበበኛ የሆነ ማን ነው? ይህን ያሳውቅ ዘንድ የይሖዋ አፍ የተናገረው ለማን ነው? ምድሪቱ የጠፋችው ለምንድን ነው? ማንም እንዳያልፍባትእንደ ምድረ በዳ የተለበለበችው ለምንድን ነው?” 13  ይሖዋ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “በፊታቸው ያኖርኩትን ሕጌን* ስለተዉና ስላልተከተሉ እንዲሁም ድምፄን ስላልሰሙ ነው። 14  ከዚህ ይልቅ ግትር ሆነው የገዛ ልባቸውን+ እንዲሁም አባቶቻቸው ባስተማሯቸው መሠረት የባአልን ምስሎች ተከተሉ።+ 15  ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ይህ ሕዝብ ጭቁኝ እንዲበላ አደርጋለሁ፤ የተመረዘም ውኃ እንዲጠጣ አደርጋለሁ።+ 16  እነሱም ሆኑ አባቶቻቸው በማያውቋቸው ብሔራት መካከል እበትናቸዋለሁ፤+ ሙሉ በሙሉ እስካጠፋቸውም ድረስ ከኋላቸው ሰይፍን እሰዳለሁ።’+ 17  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘በማስተዋል ተመላለሱ። ሙሾ የሚያወርዱትን* ሴቶች ጥሩ፤+የሠለጠኑ አልቃሽ ሴቶችንም ልካችሁ አስመጡ፤ 18  ዓይኖቻችን እንባ ያጎርፉ ዘንድ፣ሽፋሽፍቶቻችንም ውኃ ያንጠባጥቡ ዘንድፈጥነው እንዲመጡና የሐዘን እንጉርጉሮ እንዲያንጎራጉሩልን ጥሯቸው።+ 19  ከጽዮን የሐዘን እንጉርጉሮ ድምፅ ተሰምቷልና፦+ “ከባድ ጥፋት ደርሶብናል! ታላቅ ኀፍረት ተከናንበናል! ምድሪቱን ጥለን ሄደናልና፤ እነሱም ቤቶቻችንን አፈራርሰዋል።”+ 20  እናንተ ሴቶች፣ የይሖዋን ቃል ስሙ። ጆሯችሁ የአፉን ቃል ያዳምጥ። ሴቶች ልጆቻችሁን ይህን የሐዘን እንጉርጉሮ አስተምሯቸው፤አንዳችሁም ለሌላው ይህን ሙሾ አስተምሩ።+ 21  ሞት በመስኮቶቻችን በኩል ገብቷልና፤ልጆቹን ከጎዳናዎቹ፣ወጣቶቹንም ከአደባባዮቹ ለመውሰድወደማይደፈሩት ማማዎቻችን ገብቷል።’+ 22  እንዲህ በል፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ሲል አውጇል፦ “የሰዎች አስከሬን በምድር ላይ ልክ እንደ ፍግ ይወድቃል፤አጫጅ አጭዶ እንደተወውም እህል ይሆናል፤የሚሰበስበው አይኖርም።”’”+ 23  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ጥበበኛው በጥበቡ አይኩራራ፤+ኃያሉ በኃያልነቱ አይኩራራ፤ባለጸጋውም በሀብቱ አይኩራራ።”+ 24  “ከዚህ ይልቅ የሚኩራራ በዚህ ነገር ይኩራራ፦ ስለ እኔ ጥልቅ ማስተዋልና እውቀት ያለው በመሆኑ+እንዲሁም በምድር ላይ ታማኝ ፍቅር የማሳየው፣ ደግሞም ፍትሕና ጽድቅ የማሰፍነው እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በማወቁ ይኩራራ፤+በእነዚህ ነገሮች ደስ እሰኛለሁና”+ ይላል ይሖዋ። 25  “እነሆ፣ እንዲህ የሚሆንበት ቀን ይመጣል” ይላል ይሖዋ፣ “የተገረዘ ቢሆንም እንኳ ያልተገረዘውን ሁሉ ተጠያቂ አደርጋለሁ፤+ 26  ግብፅን፣+ ይሁዳን፣+ ኤዶምን፣+ አሞናውያንን፣+ ሞዓብንና+ በሰሪሳራቸው* ላይ ያለውን ፀጉር የሚላጩትን በምድረ በዳ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ተጠያቂ አደርጋለሁ፤+ ብሔራት ሁሉ ያልተገረዙ ናቸውና፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው ያልተገረዘ ነው።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍሴ ልትበቀል።”
ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ አሰማለሁ።”
ወይም “መመሪያዬን፤ ትምህርቴን።”
ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ የሚያሰሙትን።”
በዓይንና በጆሮ መካከል ያለውን የአካል ክፍል ያመለክታል።