ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 1:1-14

  • አምላክ በልጁ አማካኝነት ተናገረ (1-4)

  • ልጁ ከመላእክት የላቀ ነው (5-14)

1  በጥንት ዘመን አምላክ በተለያዩ ጊዜያትና በብዙ መንገዶች በነቢያት አማካኝነት ለአባቶቻችን ተናግሯል።+  አሁን ደግሞ በእነዚህ ቀናት መጨረሻ የሁሉም ነገር ወራሽ+ አድርጎ በሾመውና የተለያዩ ሥርዓቶችን* በፈጠረበት+ በልጁ+ አማካኝነት ለእኛ ተናገረ።  እሱ የአምላክ ክብር+ ነጸብራቅና የማንነቱ ትክክለኛ አምሳያ ነው፤+ እሱም በኃያል ቃሉ ሁሉንም ነገር ደግፎ ያኖራል። እኛን ከኃጢአታችን ካነጻ+ በኋላም በሰማይ በግርማዊው ቀኝ ተቀምጧል።+  ስለዚህ ከመላእክት ስም እጅግ የላቀ ስም+ የወረሰ በመሆኑ ከእነሱ የተሻለ ሆኗል።+  ለምሳሌ፣ አምላክ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ”+ ደግሞም “አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል”+ ብሎ ከመላእክት መካከል ስለ የትኛው መልአክ ተናግሮ ያውቃል?  ሆኖም የበኩር ልጁን+ እንደገና ወደ ዓለም* የሚያመጣበትን ጊዜ በተመለከተ “የአምላክ መላእክት ሁሉ ይስገዱለት”* ይላል።  በተጨማሪም ስለ መላእክት ሲናገር “መላእክቱን መናፍስት፣ አገልጋዮቹን*+ ደግሞ የእሳት ነበልባል ያደርጋል”+ ይላል።  ስለ ልጁ ሲናገር ግን እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው፤+ የመንግሥትህ በትርም የቅንነት* በትረ መንግሥት ነው።  ጽድቅን ወደድክ፤ ዓመፅን ጠላህ። ስለዚህ አምላክ ይኸውም አምላክህ ከባልንጀሮችህ* ይበልጥ በደስታ ዘይት ቀባህ።”+ 10  ደግሞም እንዲህ ይላል፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት ጣልክ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። 11  እነሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ 12  እንደ ካባ፣ እንደ ልብስም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ደግሞም እንደ ልብስ ትለውጣቸዋለህ። አንተ ግን ያው ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።”+ 13  ይሁንና “ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ”+ ብሎ ከመላእክት መካከል ስለ የትኛው መልአክ ተናግሮ ያውቃል? 14  ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ ቅዱስ አገልግሎት* የሚያከናውኑ መናፍስት አይደሉም?+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ዘመናትን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እጅ ይንሱት።”
ቃል በቃል “ሰዎች ወደሚኖሩበት ምድር።”
ወይም “የሕዝብ አገልጋዮቹን።”
ወይም “የፍትሕ።”
በዳዊት የዘር ሐረግ የነበሩ ሌሎች ነገሥታትን ያመለክታል።
ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት።”