ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 13:1-25

  • መደምደሚያ ላይ የቀረበ ማሳሰቢያና ሰላምታ (1-25)

    • “እንግዳ መቀበልን አትርሱ” (2)

    • ‘ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር ይሁን’ (4)

    • “አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ” (7, 17)

    • የምስጋና መሥዋዕት አቅርቡ (15, 16)

13  እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ።+  እንግዳ መቀበልን* አትርሱ፤+ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ ሳያውቁት መላእክትን አስተናግደዋልና።+  በእስር ላይ ያሉትን ከእነሱ ጋር ታስራችሁ እንዳላችሁ አድርጋችሁ በማሰብ+ ሁልጊዜ አስታውሷቸው፤+ እናንተም ራሳችሁ ገና በሥጋ ያላችሁ በመሆናችሁ* እንግልት እየደረሰባቸው ያሉትን አስቡ።  ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን፤+ አምላክ ሴሰኞችንና* አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋልና።+  አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤+ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።+ እሱ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” ብሏልና።+  ስለዚህ በሙሉ ልብ “ይሖዋ* ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።+  የአምላክን ቃል የነገሯችሁን በመካከላችሁ ሆነው አመራር የሚሰጡትን አስቡ፤+ ደግሞም ምግባራቸው ያስገኘውን ውጤት በሚገባ በማጤን በእምነታቸው ምሰሏቸው።+  ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ለዘላለምም ያው ነው።  በልዩ ልዩና እንግዳ በሆኑ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን በምግብ* ሳይሆን በአምላክ ጸጋ ቢጠናከር መልካም ነውና፤ በዚህ የተጠመዱ ምንም አልተጠቀሙም።+ 10  እኛ መሠዊያ ያለን ሲሆን በድንኳኑ ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት ከመሠዊያው ላይ ወስደው መብላት አይፈቀድላቸውም።+ 11  ምክንያቱም ሊቀ ካህናቱ የእንስሳቱን ደም የኃጢአት መባ አድርጎ ወደ ቅዱሱ ስፍራ* የሚወስደው ሲሆን ሥጋው ግን ከሰፈሩ ውጭ ይቃጠላል።+ 12  ስለዚህ ኢየሱስም ሕዝቡን በገዛ ራሱ ደም ለመቀደስ+ ከከተማው በር ውጭ መከራ ተቀበለ።+ 13  እንግዲህ እኛም እሱ የተሸከመውን ነቀፋ ተሸክመን ከሰፈር ውጭ እሱ ወዳለበት እንሂድ፤+ 14  በዚህ ቋሚ ከተማ የለንምና፤ ከዚህ ይልቅ ወደፊት የምትመጣዋን ከተማ በጉጉት እንጠባበቃለን።+ 15  ስለዚህ በኢየሱስ አማካኝነት የውዳሴ መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ እናቅርብ፤+ ይህም ስሙን በይፋ የምናውጅበት+ የከንፈራችን ፍሬ ነው።+ 16  በተጨማሪም መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤+ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና።+ 17  ተግተው ስለሚጠብቋችሁና* ይህን በተመለከተ ስሌት ስለሚያቀርቡ+ በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ+ እንዲሁም ተገዙ፤+ ይህን የምታደርጉት ሥራቸውን በደስታ እንጂ በሐዘን እንዳያከናውኑ ነው፤ አለዚያ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በሐዘን ይሆናል፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል። 18  ለእኛ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ምክንያቱም ሐቀኛ* ሕሊና እንዳለን እናምናለን፤ ደግሞም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።+ 19  በተለይ ደግሞ ወደ እናንተ በፍጥነት ተመልሼ እንድመጣ ትጸልዩልኝ ዘንድ አሳስባችኋለሁ። 20  እንግዲያው ታላቅ የበጎች እረኛ+ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ የዘላለማዊውን ቃል ኪዳን ደም ይዞ ከሞት እንዲነሳ ያደረገው የሰላም አምላክ 21  ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ እሱ በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ነገር እንድናደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ያነሳሳናል። ለእሱ ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን። 22  እንግዲህ ወንድሞች፣ የጻፍኩላችሁ ደብዳቤ አጭር ስለሆነ ይህን የማበረታቻ ቃል በትዕግሥት እንድታዳምጡ አሳስባችኋለሁ። 23  ወንድማችን ጢሞቴዎስ መፈታቱን እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ቶሎ ከመጣ አብረን መጥተን እናያችኋለን። 24  በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ሁሉና ለቀሩት ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጣሊያን+ ያሉት ሰላምታ ልከውላችኋል። 25  የአምላክ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን።”
“ከእነሱ ጋር መከራ የምትቀበሉ ያህል ሆናችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከምግብ ጋር የተያያዙ ደንቦችን ያመለክታል።
ቅድስተ ቅዱሳኑን ያመለክታል።
ወይም “ነፍሳችሁን ተግተው ስለሚጠብቁና።”
ቃል በቃል “ጥሩ።”