ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 6:1-20

  • “ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር” (1-3)

  • ወደኋላ ያሉት የአምላክን ልጅ እንደገና ይቸነክሩታል (4-8)

  • ተስፋችሁን አስተማማኝ አድርጉ (9-12)

  • አስተማማኝና ጽኑ ተስፋ አለን (13-20)

    • የአምላክ የተስፋ ቃልና መሐላ ፈጽሞ አይለወጥም (17, 18)

6  ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት አልፈን ስለሄድን+ ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር፤+ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፤ ይኸውም ከሞቱ ሥራዎች ንስሐ ስለ መግባት፣ በአምላክ ስለ ማመን፣  እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣+ ስለ ሙታን ትንሣኤና+ ስለ ዘላለማዊ ፍርድ የሚገልጹ ትምህርቶችን ደግመን አንማር።  አምላክ ከፈቀደ ይህን እናደርጋለን።  ቀደም ሲል ብርሃን በርቶላቸው የነበሩትን፣+ ሰማያዊውን ነፃ ስጦታ የቀመሱትን፣ መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን፣  መልካም የሆነውን የአምላክ ቃልና በሚመጣው ሥርዓት* የሚገኙትን በረከቶች* የቀመሱትን፣  በኋላ ግን ከእምነት ጎዳና የራቁትን+ እንደገና ወደ ንስሐ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም የአምላክን ልጅ ለራሳቸው እንደገና በእንጨት ላይ ይቸነክሩታል፤ እንዲሁም በአደባባይ ያዋርዱታል።+  በየጊዜው በላዩ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የሚጠጣና ለአራሾቹ መብል የሚሆን አትክልት የሚያፈራ መሬት ከአምላክ በረከትን ያገኛልና።  እሾህና አሜኬላ የሚያበቅል ከሆነ ግን የተተወና ለመረገም የተቃረበ ይሆናል፤ በመጨረሻም በእሳት ይቃጠላል።  ይሁን እንጂ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ምንም እንኳ እንደዚህ ብለን ብንናገርም እናንተ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይኸውም ወደ መዳን በሚያደርስ ሁኔታ ላይ እንደምትገኙ እርግጠኞች ነን። 10  አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም* ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር+ በመርሳት ፍትሕ አያዛባም። 11  ይሁንና ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነውን ተስፋ+ እስከ መጨረሻው መያዝ እንድትችሉ+ እያንዳንዳችሁ ያንኑ ትጋት እንድታሳዩ እንመኛለን፤ 12  ይህም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ነው።+ 13  አምላክ ለአብርሃም ቃል በገባለት ጊዜ ሊምልበት የሚችል ከእሱ የሚበልጥ ሌላ ማንም ስለሌለ በራሱ ስም ማለ፤+ 14  እንዲህም አለ፦ “በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም በእርግጥ አበዛዋለሁ።”+ 15  በመሆኑም አብርሃም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ ይህን የተስፋ ቃል አገኘ። 16  ሰዎች ከእነሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላቸውም እንደ ሕጋዊ ዋስትና ስለሆነ ማንኛውም ሙግት በመሐላው ይቋጫል።+ 17  በተመሳሳይም አምላክ ዓላማው ፈጽሞ የማይለወጥ መሆኑን ለተስፋው ቃል ወራሾች+ ይበልጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለማሳየት በወሰነ ጊዜ የተስፋውን ቃል በመሐላ አረጋገጠ። 18  ይህን ያደረገው መጠጊያ ለማግኘት ወደ እሱ የሸሸን እኛ፣ አምላክ ሊዋሽ በማይችልባቸው፣+ ፈጽሞ በማይለወጡት በእነዚህ ሁለት ነገሮች አማካኝነት በፊታችን ያለውን ተስፋ አጥብቀን እንድንይዝ የሚረዳንን ከፍተኛ ማበረታቻ እንድናገኝ ነው። 19  እኛ ለነፍሳችን* እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን፤+ ተስፋውም መጋረጃውን አልፈን ወደ ውስጥ እንድንገባ ያስችለናል፤+ 20  ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ለዘላለም ሊቀ ካህናት+ የሆነው ኢየሱስ+ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ስለ እኛ ወደዚያ ገብቷል።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በሚመጣው ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ኃይሎች።”
ወይም “በመርዳትም።”
ወይም “እኛ ለሕይወታችን።”