ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 7:1-28

  • መልከጼዴቅ፣ ልዩ የሆነ ንጉሥና ካህን (1-10)

  • የክርስቶስ ክህነት ያለው ብልጫ (11-28)

    • ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ሊያድን ይችላል (25)

7  አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ የሳሌም ንጉሥና የልዑሉ አምላክ ካህን የሆነው ይህ መልከጼዴቅ አግኝቶት ባረከው፤+  አብርሃም ደግሞ ከሁሉ ነገር አንድ አሥረኛ ሰጠው።* በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ደግሞም የሳሌም ንጉሥ ማለትም “የሰላም ንጉሥ” ነው።  አባትና እናትም ሆነ የዘር ሐረግ እንዲሁም ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን ልጅ እንዲመስል በመደረጉ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።+  እንግዲህ የቤተሰብ ራስ* የሆነው አብርሃም ምርጥ ከሆነው ምርኮ ላይ አንድ አሥረኛውን የሰጠው+ ይህ ሰው ምን ያህል ታላቅ እንደነበረ ተመልከቱ።  እርግጥ የክህነት ኃላፊነት የሚቀበሉ ከሌዊ ልጆች ወገን የሆኑት ሰዎች+ ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም ከሕዝቡ ማለትም ከገዛ ወንድሞቻቸው አሥራት እንዲሰበስቡ ሕጉ ያዛል።+  ሆኖም ከእነሱ የትውልድ ሐረግ ያልመጣው ይህ ሰው ከአብርሃም አሥራት የተቀበለ ሲሆን የተስፋ ቃል የተሰጠውን ሰው ባርኮታል።+  እንግዲህ አነስተኛ የሆነው ከእሱ በሚበልጠው እንደተባረከ ምንም ጥርጥር የለውም።  በአንድ በኩል አሥራት የሚቀበሉት ሟች የሆኑ ሰዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ግን አሥራት የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሠከረለት ሰው ነው።+  እንግዲህ አሥራት የሚቀበለው ሌዊ እንኳ በአብርሃም በኩል አሥራት ከፍሏል ማለት ይቻላል፤ 10  መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ውስጥ* ነበርና።+ 11  እንግዲህ ፍጽምና ሊገኝ የሚችለው በሌዊ ክህነት አማካኝነት ቢሆን ኖሮ+ (ክህነቱ ለሕዝቡ የተሰጠው ሕግ አንዱ ገጽታ ስለሆነ)፣ እንደ አሮን ሥርዓት ሳይሆን እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት+ ያለ ተብሎ የተነገረለት ሌላ ካህን መነሳቱ ምን ያስፈልግ ነበር? 12  ክህነቱ ስለሚለወጥ ሕጉም የግድ መለወጥ ያስፈልገዋልና።+ 13  ይህ ሁሉ ነገር የተነገረለት ሰው ከሌላ ነገድ የመጣ ነውና፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም።+ 14  ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የታወቀ ነውና፤+ ይሁንና ሙሴ ከዚህ ነገድ ካህናት እንደሚገኙ የተናገረው ነገር የለም። 15  ደግሞም እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን+ ሲነሳ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤+ 16  እሱ ካህን የሆነው በሥጋዊ ትውልድ ላይ በተመካውና ሕጉ በያዘው መሥፈርት ሳይሆን የማይጠፋ ሕይወት+ እንዲኖረው ባስቻለው ኃይል ነው። 17  “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመሥክሮለታልና።+ 18  እንግዲህ የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና ፍሬ ቢስ በመሆኑ ተሽሯል።+ 19  ሕጉ የትኛውንም ነገር ወደ ፍጽምና አላደረሰምና፤+ ወደ አምላክ የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ+ መሰጠቱ ግን ይህን ማድረግ ችሏል።+ 20  በተጨማሪም ይህ ያለመሐላ እንዳልሆነ ሁሉ 21  (ያለመሐላ ካህናት የሆኑ ሰዎች አሉና፤ እሱ ግን በመሐላ ካህን ሆኗል፤ ይህም የሆነው “ይሖዋ* ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሏል፤ ደግሞም ሐሳቡን አይለውጥም”* በማለት ስለ እሱ የተናገረው አምላክ በማለው መሐላ መሠረት ነው፤)+ 22  እንደዚሁም ኢየሱስ ለተሻለ ቃል ኪዳን ዋስትና* ሆኗል።+ 23  ከዚህም በተጨማሪ ካህናት አገልግሎታቸውን እንዳይቀጥሉ ሞት ስለሚያግዳቸው አንዱ ሌላውን እየተካ እንዲያገለግል ብዙዎች ካህናት መሆን ነበረባቸው፤+ 24  እሱ ግን ለዘላለም+ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር ክህነቱ ተተኪ የለውም። 25  ስለሆነም ለእነሱ ለመማለድ ሁልጊዜ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ የሚቀርቡትን ፈጽሞ ሊያድናቸውም ይችላል።+ 26  እኛ የሚያስፈልገን ታማኝ፣ ቅን የሆነ፣ ያልረከሰ፣+ ከኃጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው።+ 27  እነዚያ ሊቃነ ካህናት ያደርጉ እንደነበረው፣ በመጀመሪያ ለራሱ ኃጢአት ከዚያም ለሕዝቡ ኃጢአት+ በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤+ ምክንያቱም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈጽሞታል።+ 28  ሕጉ ድክመት ያለባቸውን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤+ ከሕጉ በኋላ የመጣው የመሐላ ቃል+ ግን ለዘላለም ፍጹም የተደረገውን ልጅ+ ይሾማል።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “አካፈለው።”
ወይም “ፓትሪያርክ።”
ወይም “ወደፊት የሚወለድ የአባቱ የአብርሃም ዘር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አይጸጸትም።”
ወይም “እንደ መያዣ የተሰጠ።”