ዕንባቆም 3:1-19

  • ነቢዩ ይሖዋ እርምጃ እንዲወስድ ጸለየ (1-19)

    • አምላክ የቀባውን ሕዝብ ያድናል (13)

    • መከራ ቢኖርም በይሖዋ መደሰት (17, 18)

3  ነቢዩ ዕንባቆም በሙሾ* ያቀረበው ጸሎት፦   ይሖዋ ሆይ፣ ስለ አንተ የተወራውን ሰምቻለሁ። ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ፍርሃት* አሳደረብኝ። በዓመታት መካከል* ሥራህን ሕያው አድርግ! በዓመታትም መካከል* ሥራህን አሳውቅ። መዓት በሚወርድበት ጊዜ ምሕረትን አስታውስ።+   አምላክ ከቴማን፣ቅዱሱም ከፋራን ተራራ መጣ።+ (ሴላ)* ግርማው ሰማያትን ሸፈነ፤+ምድርም በውዳሴው ተሞላች።   ጸዳሉ እንደ ፀሐይ ብርሃን ነው።+ ከእጁ ሁለት ጨረሮች ፈነጠቁ፤ብርታቱም በዚያ ተሰውሯል።   ቸነፈር ከፊቱ ሄደ፤+የሚያቃጥል ትኩሳትም እግር በእግር ተከተለው።   ቆመ፤ ምድርንም አንቀጠቀጠ።+ ባየም ጊዜ ብሔራትን አብረከረካቸው።+ ዘላለማዊ የሆኑት ተራሮች ተፈረካከሱ፤የጥንቶቹ ኮረብቶች ተደፉ።+ የጥንቶቹ መንገዶች የእሱ ናቸው።   በኩሻን ድንኳኖች ውስጥ ችግር አየሁ። የምድያም የድንኳን ሸራዎች ተንቀጠቀጡ።+   ይሖዋ ሆይ፣ ቁጣህ የነደደው በወንዞች ላይ ነው?በእርግጥ በወንዞች ላይ ነው? ወይስ ታላቅ ቁጣህን የገለጽከው በባሕሩ ላይ ነው?+ በፈረሶችህ ላይ ተቀምጠህ ጋልበሃልና፤+ሠረገሎችህ ድል ተቀዳጅተዋል።*+   የቀስትህ ሽፋን ተነስቷል፤ ቀስትህም ተዘጋጅቷል። ዘንጎቹ* በመሐላ ተመድበዋል።* (ሴላ) ምድሪቱን በወንዞች ከፈልክ። 10  ተራሮች አንተን ሲያዩ በሥቃይ ተንፈራገጡ።+ ዶፍ ዝናብ ጠራርጎ ሄደ። ጥልቁ በኃይል ጮኸ።+ እጁን ወደ ላይ አነሳ። 11  ፀሐይና ጨረቃ ከፍ ባለው መኖሪያ ስፍራቸው ቆሙ።+ ፍላጾችህ እንደ ብርሃን ተወረወሩ።+ ጦርህ እንደ መብረቅ አብረቀረቀ። 12  በምድር ላይ በቁጣ ዘመትክ። ብሔራትን በቁጣ ረገጥካቸው።* 13  ሕዝብህን ለመታደግ፣ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ። የክፉውን ቤት መሪ* አደቀቅክ። ቤቱ ከመሠረቱ አንስቶ እስከ አናቱ* ድረስ ተጋለጠ። (ሴላ) 14  እኔን ለመበታተን በቁጣ በተነሱ ጊዜበገዛ ራሱ መሣሪያዎች* የተዋጊዎቹን ራስ ወጋህ። እነሱ ጎስቋላውን ሰው በስውር በመዋጥ ሐሴት አድርገዋል። 15  በባሕር ውስጥ፣ በሚናወጠው ብዙ ውኃ መካከልበፈረሶችህ እየጋለብክ አለፍክ። 16  እኔ ሰማሁ፤ ሆዴም ታወከ፤ከድምፁ የተነሳ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ። አጥንቶቼም ነቀዙ፤+ከታች ያሉት እግሮቼ ተብረከረኩ። ሆኖም የጭንቀትን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ፤+ይህ ቀን ጥቃት በሚሰነዝርብን ሕዝብ ላይ ይመጣልና። 17  የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣የወይን ተክልም ፍሬ ባይሰጥ፣የወይራ ዛፍም ባያፈራ፣እርሻዎቹም* እህል ባይሰጡ፣መንጋው ከጉረኖው ቢጠፋ፣ከብቶቹም ሁሉ በረት ውስጥ ባይገኙ፣ 18  እኔ ግን በይሖዋ ሐሴት አደርጋለሁ፤አዳኜ በሆነውም አምላክ እደሰታለሁ።+ 19  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ብርታቴ ነው፤+እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤በከፍታ ስፍራዎችም ላይ ያስኬደኛል።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በሐዘን እንጉርጉሮ።”
ወይም “አክብሮታዊ ፍርሃት።”
“በእኛ ዘመን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“በእኛም ዘመን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መዳን አስገኝተዋል።”
“ቀስቶቹ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ነገዶቹ የገቧቸው ቃለ መሐላዎች ተገልጸዋል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ወቃሃቸው።”
ቃል በቃል “ራስ።”
ቃል በቃል “አንገቱ።”
ቃል በቃል “በዘንጎቹ።”
ወይም “እርከኖቹም።”