ዕዝራ 9:1-15

  • እስራኤላውያን ከሌሎች ብሔራት ጋር መጋባታቸው (1-4)

  • ዕዝራ ያቀረበው የንስሐ ጸሎት (5-15)

9  እነዚህ ነገሮች እንደተጠናቀቁ መኳንንቱ ወደ እኔ መጥተው እንዲህ አሉኝ፦ “የእስራኤል ሕዝብ፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ በምድሪቱ ከሚኖሩት ሕዝቦች ይኸውም ከከነአናውያን፣ ከሂታውያን፣ ከፈሪዛውያን፣ ከኢያቡሳውያን፣ ከአሞናውያን፣ ከሞዓባውያን፣ ከግብፃውያንና+ ከአሞራውያን+ እንዲሁም አስጸያፊ ከሆኑት ልማዶቻቸው+ ራሳቸውን አልለዩም።  ከእነሱም ሴቶች ልጆች መካከል ለራሳቸውና ለወንዶች ልጆቻቸው ሚስቶች ወስደዋል።+ በመሆኑም ቅዱስ ዘር+ የሆኑት እነዚህ ሰዎች በምድሪቱ ከሚኖሩት ሕዝቦች ጋር ተቀላቅለዋል።+ ይህን ታማኝነት የጎደለው ድርጊት በመፈጸም ግንባር ቀደም የሆኑት መኳንንቱና የበታች ገዢዎቹ ናቸው።”  እኔም ይህን ስሰማ እጀ ጠባቤንና መደረቢያዬን ቀደድኩ፤ ፀጉሬንና ጺሜን ነጨሁ፤ በጣም ከመደንገጤም የተነሳ በተቀመጥኩበት ደርቄ ቀረሁ።  ምሽት ላይ እስከሚቀርበው የእህል መባ+ ድረስ እንደደነገጥኩ በዚያ ተቀምጬ ሳለሁ ለእስራኤል አምላክ ቃል አክብሮታዊ ፍርሃት ያላቸው* ሰዎች ሁሉ፣ በግዞት ተወስደው የነበሩት ሰዎች በፈጸሙት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት የተነሳ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ።  ከዚያም ምሽት ላይ የእህል መባው+ በሚቀርብበት ጊዜ እጀ ጠባቤና መደረቢያዬ እንደተቀደደ ራሴን አዋርጄ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ፤ በጉልበቴም ተንበርክኬ እጆቼን ወደ አምላኬ ወደ ይሖዋ ዘረጋሁ።  እንዲህም አልኩ፦ “አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ ፊቴን ወደ አንተ ቀና ማድረግ አሳፈረኝ፤ አሸማቀቀኝ፤ ምክንያቱም አምላኬ ሆይ፣ የፈጸምናቸው ስህተቶች በአናታችን ላይ ተቆልለዋል፤ በደላችንም ከመብዛቱ የተነሳ እስከ ሰማይ ደርሷል።+  ከአባቶቻችን ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ የፈጸምነው በደል ታላቅ ነው፤+ በሠራናቸውም ስህተቶች የተነሳ ይኸው ዛሬ እንደሚታየው እኛም ሆንን ነገሥታታችንና ካህናታችን በሌሎች አገሮች ነገሥታት እጅ ወድቀን ለሰይፍ፣+ ለምርኮ፣+ ለብዝበዛና+ ለውርደት ተዳርገናል።+  አሁን ግን አምላካችን ይሖዋ ቀሪዎች እንዲተርፉና በቅዱስ ስፍራው አስተማማኝ ቦታ* እንድናገኝ በማድረግ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ሞገስ አሳይቶናል፤+ አምላካችን ሆይ፣ ይህን ያደረግከው ዓይኖቻችን እንዲበሩና ከተጫነብን የባርነት ቀንበር ትንሽ እንድናገግም ነው።  ባሪያዎች+ ብንሆንም እንኳ አምላካችን ባሪያዎች ሆነን እንድንቀር አልተወንም፤ ከዚህ ይልቅ በፋርስ ነገሥታት ፊት ታማኝ ፍቅሩን አሳየን፤+ ይህን ያደረገውም ዳግም አገግመን የአምላካችንን ቤት ከወደቀበት እንድናነሳና የፈራረሱትን ቦታዎች መልሰን እንድንገነባ+ እንዲሁም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የድንጋይ ቅጥር* እንድናገኝ ሲል ነው። 10  “አሁን ግን አምላካችን ሆይ፣ ከዚህ በኋላ ምን ማለት እንችላለን? ምክንያቱም ትእዛዛትህን ተላልፈናል፤ 11  በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካኝነት የሰጠኸንን የሚከተለውን ትእዛዝ አላከበርንም፦ ‘ትወርሷት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በነዋሪዎቿ ርኩሰት የተነሳ የረከሰች ናት፤ ምክንያቱም በምድሪቱ የሚኖሩት ሰዎች በአስጸያፊ ድርጊቶቻቸው ምድሪቱን ከዳር እሰከ ዳር በርኩሰታቸው ሞልተዋታል።+ 12  ስለሆነም ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ፤+ እንዲሁም ይበልጥ እየበረታችሁ እንድትሄዱ፣ የምድሪቱን መልካም ነገር እንድትበሉና ምድሪቱን የልጆቻችሁ ዘላለማዊ ርስት ማድረግ እንድትችሉ ፈጽሞ የእነሱን ሰላምና ብልጽግና አትፈልጉ።’+ 13  በተጨማሪም በመጥፎ ሥራዎቻችንና በፈጸምነው ታላቅ በደል ምክንያት ይህ ሁሉ ደረሰብን፤ አንተ ግን አምላካችን ሆይ፣ እንደ ጥፋታችን መጠን አልቀጣኸንም፤+ ከዚህ ይልቅ እኛ እዚህ ያለነው እንድንተርፍ ፈቀድክ።+ 14  ታዲያ ትእዛዛትህን እንደገና መተላለፍና እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ከሚፈጽሙ ሕዝቦች ጋር በጋብቻ መዛመድ ይገባናል?+ አንተስ አንድም ሰው ሳታስቀር ወይም ሳታስተርፍ ፈጽሞ እስክታጠፋን ድረስ ልትቆጣ አይገባህም? 15  የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጻድቅ ነህ፤+ ምክንያቱም እኛ ከጥፋት ተርፈን እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በሕይወት አለን። እንዲህ ያለ ነገር አድርጎ በፊትህ መቆም የማይቻል ቢሆንም ይኸው ከነበደላችን በፊትህ ቀርበናል።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “የተንቀጠቀጡ።”
ቃል በቃል “ካስማ።”
ወይም “ከለላ የሚሆን ቅጥር።”