ዘሌዋውያን 1:1-17

  • የሚቃጠል መባ (1-17)

1  ይሖዋም ሙሴን ጠርቶ ከመገናኛ ድንኳኑ+ እንዲህ ሲል አናገረው፦  “እስራኤላውያንን* አናግራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ከእናንተ መካከል ማንኛችሁም ከቤት እንስሳት ለይሖዋ መባ ማቅረብ ከፈለጋችሁ መባችሁን ከከብቶች ወይም ከመንጎች መካከል ማቅረብ አለባችሁ።+  “‘የሰውየው መባ ከከብቶች መካከል ተወስዶ የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ከሆነ እንከን የሌለበትን ተባዕት እንስሳ ማቅረብ ይኖርበታል።+ መባውን በራሱ ፈቃድ ተነሳስቶ+ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በይሖዋ ፊት ማቅረብ ይኖርበታል።  ለሚቃጠል መባ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ መባውም ለሰውየው ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል።  “‘ከዚያም ወይፈኑ በይሖዋ ፊት ይታረድ፤ ካህናት+ የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን ያቅርቡት፤ እንዲሁም ደሙን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በሚገኘው መሠዊያ ጎኖች ሁሉ ላይ ይርጩት።+  የሚቃጠለውም መባ መገፈፍና መቆራረጥ ይኖርበታል።+  ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም በመሠዊያው ላይ እሳት ያንድዱ፤+ በእሳቱም ላይ እንጨት ይረብርቡበት።  እነሱም ተቆራርጦ የተዘጋጀውን መባ+ ከጭንቅላቱና ከሞራው* ጋር በመሠዊያው ላይ ባለው እሳት ላይ በሚገኘው እንጨት ላይ ይደርድሩት።  ሆድ ዕቃውና እግሮቹም በውኃ ይታጠቡ፤ ካህኑም የሚቃጠል መባ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ ሙሉውን በመሠዊያው ላይ ያጭሰው።+ 10  “‘ሰውየው የሚቃጠል መባ እንዲሆን የሚያቀርበው መባ ከመንጋው+ ማለትም ከበግ ጠቦቶቹ ወይም ከፍየሎቹ መካከል የተወሰደ ከሆነ እንከን የሌለበትን ተባዕት ያቅርብ።+ 11  በስተ ሰሜን በኩል ባለው የመሠዊያው ጎን በይሖዋ ፊት ይታረድ፤ ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ይርጩት።+ 12  እሱም ጭንቅላቱንና ሞራውን* ጨምሮ እንስሳውን በየብልቱ ይቆራርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ባለው እሳት ላይ በሚገኘው እንጨት ላይ ይደረድራቸዋል። 13  ሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ ያጥባቸዋል፤ ካህኑም ሙሉውን ያቀርበዋል፤ እንዲሁም በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ይህም የሚቃጠል መባ ማለትም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ነው። 14  “‘ሆኖም ሰውየው አእዋፋትን ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርጎ የሚያቀርብ ከሆነ መባውን ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ጫጩቶች መካከል ያቀርባል።+ 15  ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል፤ እንዲሁም አንገቱ ላይ ቦጭቆ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ደሙ ግን በመሠዊያው ጎን ይንጠፍጠፍ። 16  ቋቱንና ላባዎቹንም ከለየ በኋላ ከመሠዊያው አጠገብ በስተ ምሥራቅ በኩል ወዳለው አመድ* ወደሚደፋበት ቦታ ይወርውራቸው።+ 17  ሙሉ በሙሉ ለሁለት ሳይለያየው ክንፎቹን ይዞ ይሰነጥቀዋል። ከዚያም ካህኑ በመሠዊያው ላይ ይኸውም በእሳቱ ላይ ባለው እንጨት ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ይህም የሚቃጠል መባ ማለትም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ነው።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “የእስራኤልን ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ኩላሊቱን ከሸፈነው ስብ።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “ኩላሊቱን የሸፈነውን ስብ።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “በስብ የራሰው አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”