ዘሌዋውያን 11:1-47

  • ንጹሕና ርኩስ እንስሳት (1-47)

11  ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦  “እስራኤላውያንን እንዲህ በሏቸው፦ ‘በምድር ላይ ካሉ ሕያዋን ፍጥረታት* መካከል እነዚህን መብላት ትችላላችሁ፦+  ሰኮናው የተሰነጠቀውንና ስንጥቁም ሙሉ በሙሉ የተከፈለውን እንዲሁም የሚያመሰኳውን ማንኛውንም እንስሳ መብላት ትችላላችሁ።  “‘ሆኖም የሚያመሰኩትን ወይም ሰኮናቸው የተሰነጠቀውን እነዚህን እንስሳት መብላት የለባችሁም፦ ግመል የሚያመሰኳ ቢሆንም ሰኮናው የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነው።+  ሽኮኮም+ መብላት የለባችሁም፤ ምክንያቱም የሚያመሰኳ ቢሆንም ሰኮናው የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነው።  ጥንቸልም ብትሆን መብላት የለባችሁም፤ ምክንያቱም የምታመሰኳ ብትሆንም ሰኮናዋ የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነች።  አሳማም+ መብላት የለባችሁም፤ ሰኮናው የተሰነጠቀና ስንጥቁ ሙሉ በሙሉ የተከፈለ ቢሆንም እንኳ አያመሰኳም። ለእናንተ ርኩስ ነው።  የእነዚህን እንስሳት ሥጋ አትብሉ ወይም በድናቸውን አትንኩ። እነዚህ ለእናንተ ርኩስ ናቸው።+  “‘በውኃዎች ውስጥ ካሉት መካከል እነዚህን መብላት ትችላላችሁ፦ በባሕርም ሆነ በወንዞች፣ በውኃዎች ውስጥ ካሉት መካከል ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ሁሉ መብላት ትችላላችሁ።+ 10  በውኃዎች ውስጥ ካሉ የሚርመሰመሱ ፍጥረታትና ሌሎች ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት* ሁሉ መካከል በባሕርና በወንዞች ውስጥ የሚገኙ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ ግን ለእናንተ አስጸያፊ ናቸው። 11  አዎ፣ እነዚህን ልትጸየፏቸው ይገባል፤ ሥጋቸውን ፈጽሞ አትብሉ፤+ በድናቸውንም ተጸየፉት። 12  በውኃዎች ውስጥ የሚኖሩ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ ለእናንተ አስጸያፊ ናቸው። 13  “‘ልትጸየፏቸው የሚገቡ በራሪ ፍጥረታት እነዚህ ናቸው፤ አስጸያፊ በመሆናቸው መበላት የለባቸውም፦ ንስር፣+ ዓሣ በል ጭላት፣ ጥቁር ጥምብ አንሳ፣+ 14  ቀይ ጭልፊት፣ ማንኛውም ዓይነት ጥቁር ጭልፊት፣ 15  ማንኛውም ዓይነት ቁራ፣ 16  ሰጎን፣ ጉጉት፣ ዓሣ አዳኝ፣ ማንኛውም ዓይነት ሲላ፣ 17  ትንሿ ጉጉት፣ ለማሚት፣ ባለ ረጅም ጆሮ ጉጉት፣ 18  ዝይ፣ ሻላ፣ ጥምብ አንሳ፣ 19  ራዛ፣ ማንኛውም ዓይነት ሽመላ፣ ጅንጅላቴና የሌሊት ወፍ። 20  በአራቱም እግሩ የሚሄድ ክንፍ ያለው የሚርመሰመስ ፍጡር* ሁሉ ለእናንተ አስጸያፊ ነው። 21  “‘በአራቱም እግራቸው ከሚሄዱ ክንፍ ካላቸው የሚርመሰመሱ ፍጥረታት መካከል መብላት የምትችሉት ከእግሮቻቸው በላይ በመሬት ላይ ለመፈናጠር የሚያገለግል የሚተጣጠፍ ቅልጥም ያላቸውን ብቻ ነው። 22  ከእነዚህም መካከል የሚከተሉትን መብላት ትችላላችሁ፦ የተለያየ ዓይነት የሚፈልስ አንበጣ፣ ሌሎች የሚበሉ አንበጦች፣+ እንጭራሪቶችና ፌንጣዎች። 23  አራት እግር ኖሯቸው ክንፍ ያላቸው ሌሎች የሚርመሰመሱ ፍጥረታት ሁሉ ለእናንተ አስጸያፊ ናቸው። 24  በእነዚህ ራሳችሁን ታረክሳላችሁ። በድናቸውን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 25  ከእነዚህ መካከል የማናቸውንም በድን የሚያነሳ ሁሉ ልብሶቹን ይጠብ፤+ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 26  “‘ሰኮናው የተሰነጠቀ፣ ስንጥቁ ግን ሙሉ በሙሉ ያልተከፈለ እንዲሁም የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ ለእናንተ ርኩስ ነው። የሚነካቸውም ሁሉ ርኩስ ይሆናል።+ 27  በአራቱም እግራቸው ከሚሄዱ ፍጥረታት መካከል በመዳፋቸው የሚሄዱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ናቸው። በድናቸውን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 28  በድናቸውን የሚያነሳ ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤+ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ እነዚህ ለእናንተ ርኩስ ናቸው። 29  “‘ለእናንተ ርኩስ የሆኑት በምድር ላይ የሚርመሰመሱ ፍጥረታት እነዚህ ናቸው፦ ፍልፈል፣ አይጥ፣+ ማንኛውም ዓይነት እንሽላሊት፣ 30  ጌኮ፣ ገበሎ፣ የውኃ እንሽላሊት፣ የአሸዋ እንሽላሊትና እስስት። 31  እነዚህ የሚርመሰመሱ ፍጥረታት ለእናንተ ርኩስ ናቸው።+ በድናቸውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 32  “‘በሚሞቱበት ጊዜ የወደቁበት ማንኛውም ነገር ይኸውም የእንጨት ዕቃም ሆነ ልብስ ወይም ቆዳ አሊያም ደግሞ በርኖስ ርኩስ ይሆናል። አገልግሎት ላይ የሚውል ማንኛውም ዕቃ ውኃ ውስጥ ይነከር፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም ይነጻል። 33  በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከወደቁ ዕቃውን ሰባብሩት፤ በውስጡ ያለውም ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል።+ 34  እንዲህ ባለ ዕቃ ውስጥ የነበረ ውኃ የነካው ማንኛውም ዓይነት ምግብ ርኩስ ይሆናል፤ በእንዲህ ዓይነቱ ዕቃ ውስጥ የነበረ የሚጠጣ ማንኛውም ዓይነት መጠጥም ርኩስ ይሆናል። 35  በድናቸው የወደቀበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል። መጋገሪያ ምድጃም ይሁን አነስተኛ ምድጃ ይሰበር። እነዚህ ነገሮች ርኩስ ናቸው፤ ለእናንተም ርኩስ ይሆናሉ። 36  ምንጭና የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ብቻ ንጹሕ ይሆናሉ፤ ይሁንና በድኑን የነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል። 37  በድናቸው በሚዘራ ዘር ላይ ቢወድቅ ዘሩ ንጹሕ ነው። 38  ይሁንና በዘሩ ላይ ውኃ ተደርጎበት ሳለ የበድናቸው አንዱ ክፍል ዘሩ ላይ ቢወድቅ ዘሩ ለእናንተ ርኩስ ይሆናል። 39  “‘እንድትበሉ ከተፈቀደላችሁ እንስሳ አንዱ ቢሞት የእንስሳውን በድን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 40  ከበድኑ የበላ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ በድኑን ያነሳ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 41  በምድር ላይ የሚርመሰመስ ማንኛውም ፍጥረት አስጸያፊ ነው።+ መበላት የለበትም። 42  በሆዱ የሚሳብን ማንኛውም ፍጥረት፣ በአራቱም እግሩ የሚሄድን ማንኛውም ፍጥረት ወይም ብዙ እግሮች ያሉትን በምድር ላይ የሚርመሰመስ ማንኛውም ፍጥረት መብላት የለባችሁም፤ ምክንያቱም አስጸያፊ ናቸው።+ 43  በምድር ላይ በሚርመሰመስ በማንኛውም ፍጥረት ራሳችሁን* አስጸያፊ አታድርጉ፤ በእነሱም ራሳችሁን በመበከል አትርከሱ።+ 44  እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝና፤+ እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ+ እናንተም ራሳችሁን ልትቀድሱና ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።+ በምድር ላይ በሚንቀሳቀስ በማንኛውም የሚርመሰመስ ፍጥረት ራሳችሁን* አታርክሱ። 45  አምላካችሁ መሆኔን ለማስመሥከር ከግብፅ ምድር መርቼ ያወጣኋችሁ እኔ ይሖዋ ነኝና፤+ እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ+ እናንተም ቅዱሳን መሆን አለባችሁ።+ 46  “‘እንስሳትን፣ የሚበርሩ ፍጥረታትን፣ በውኃዎች ውስጥ የሚንቀሳቀስን ማንኛውም ዓይነት ሕያው ፍጡር* እንዲሁም በምድር ላይ የሚርመሰመስን ፍጡር* ሁሉ በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፤ 47  ርኩስ የሆነውንና ንጹሕ የሆነውን እንዲሁም ለመብል የሚሆነውንና ለመብል የማይሆነውን ሕያው ፍጡር ለመለየት ሕጉ ይህ ነው።’”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ከየብስ እንስሳት።”
ወይም “ነፍሳት።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍሳችሁን።”
ወይም “ነፍሳችሁን።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”