ዘሌዋውያን 12:1-8
-
ከወሊድ በኋላ የሚከናወን የመንጻት ሥርዓት (1-8)
12 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንዲት ሴት ብታረግዝና* ወንድ ልጅ ብትወልድ በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ሁሉ ለሰባት ቀን ትረክሳለች።+
3 ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ይገረዛል።+
4 እሷም ከደም ራሷን ለማንጻት ለቀጣዮቹ 33 ቀናት ትቆያለች። የምትነጻባቸው ቀናት እስኪያበቁ ድረስ ምንም ዓይነት ቅዱስ ነገር መንካትም ሆነ ወደ ቅዱሱ ስፍራ መግባት የለባትም።
5 “‘ሴት ልጅ ከወለደች ደግሞ በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ሁሉ ለ14 ቀን ትረክሳለች። ከደም ራሷን ለማንጻትም ለቀጣዮቹ 66 ቀናት ትቆያለች።
6 ሴትየዋ ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ ወልዳ የመንጻቷ ጊዜ ሲያበቃ ለሚቃጠል መባ እንዲሆን አንድ ዓመት ገደማ የሆነው የበግ ጠቦት፣+ ለኃጢአት መባ እንዲሆን ደግሞ አንድ የርግብ ጫጩት ወይም አንድ ዋኖስ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወደ ካህኑ ታመጣለች።
7 እሱም መባዎቹን በይሖዋ ፊት በማቅረብ ያስተሰርይላታል፤ እሷም ከሚፈሳት ደም ትነጻለች። ወንድ ልጅም ሆነ ሴት ልጅ ለወለደች ሴት የሚሠራው ሕግ ይህ ነው።
8 ሆኖም ሴትየዋ በግ ለማቅረብ አቅሟ የማይፈቅድላት ከሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ታምጣ፤+ አንዱ ለሚቃጠል መባ ሌላው ደግሞ ለኃጢአት መባ ይሆናል። ካህኑም ያስተሰርይላታል፤ እሷም ንጹሕ ትሆናለች።’”
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “ዘር ብትፀንስና።”