ዘሌዋውያን 14:1-57

  • ከሥጋ ደዌ የመንጻት ሥርዓት (1-32)

  • በደዌ የተበከለ ቤት የሚነጻበት ሥርዓት (33-57)

14  ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “የሥጋ ደዌ ያለበት አንድ ሰው መንጻቱን ለማረጋገጥ ካህኑ ፊት እንዲቀርብ+ በሚደረግበት ዕለት የሚኖረው ሕግ ይህ ነው።  ካህኑ ከሰፈሩ ውጭ ወጥቶ ሰውየውን ይመረምረዋል። የሥጋ ደዌ ይዞት የነበረው ሰው ከሥጋ ደዌው ከዳነ  ካህኑ ሰውየው ራሱን ለማንጻት በሕይወት ያሉ ሁለት ንጹሕ ወፎችን፣ የአርዘ ሊባኖስ እንጨት፣ ደማቅ ቀይ ማግና ሂሶጵ እንዲያመጣ ያዘዋል።+  እንዲሁም ካህኑ አንደኛዋ ወፍ ከወራጅ ውኃ የተቀዳ ውኃ ባለበት የሸክላ ዕቃ ውስጥ እንድትታረድ ትእዛዝ ይሰጣል።  በሕይወት ያለችውን ወፍ ደግሞ ከአርዘ ሊባኖስ እንጨቱ፣ ከደማቁ ቀይ ማግና ከሂሶጱ ጋር ወስዶ ከወራጅ ውኃ በተቀዳው ውኃ ላይ በታረደችው ወፍ ደም ውስጥ ይንከራቸው።  ከዚያም ራሱን ከሥጋ ደዌ በሚያነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፤ ሰውየውም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል፤ በሕይወት ያለችውንም ወፍ ሜዳ ላይ ይለቃታል።+  “ራሱን የሚያነጻውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ ፀጉሩንም በሙሉ ይላጭ፤ ገላውንም በውኃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። ይህን ካደረገ በኋላ ወደ ሰፈሩ መግባት ይችላል፤ ሆኖም ለሰባት ቀን ከድንኳኑ ውጭ ይቀመጣል።  በሰባተኛው ቀን በራሱ ላይ ያለውን ፀጉር፣ ጺሙንና ቅንድቡን በሙሉ ይላጭ። ፀጉሩን በሙሉ ከተላጨ በኋላ ልብሶቹን ያጥባል እንዲሁም ገላውን በውኃ ይታጠባል፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል። 10  “በስምንተኛው ቀን እንከን የሌለባቸውን ሁለት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ዓመት ገደማ የሆናትን እንከን የሌለባት አንዲት እንስት የበግ ጠቦት፣+ የእህል መባ እንዲሆን በዘይት የተለወሰ ሦስት አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄትና+ አንድ የሎግ መስፈሪያ* ዘይት ያመጣል፤+ 11  ሰውየው ንጹሕ መሆኑን የሚያስታውቀው ካህንም ራሱን የሚያነጻውን ሰው ከመባዎቹ ጋር በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት ያቀርበዋል። 12  ካህኑም አንደኛውን የበግ ጠቦት ወስዶ ከአንዱ የሎግ መስፈሪያ ዘይት ጋር በማድረግ የበደል መባ እንዲሆን ያቀርበዋል፤+ እነዚህንም የሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዘውዛቸዋል።+ 13  ከዚያም የበግ ጠቦቱን የኃጢአት መባውና የሚቃጠል መባው ዘወትር በሚታረዱበት ቦታ+ ይኸውም ቅዱስ በሆነ ስፍራ ያርደዋል፤ ምክንያቱም እንደ ኃጢአት መባው ሁሉ የበደል መባውም የካህኑ ድርሻ ነው።+ ይህ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው።+ 14  “ካህኑም ከበደል መባው ደም ላይ የተወሰነውን ይወስዳል፤ ከዚያም ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል። 15  ካህኑም ከአንዱ የሎግ መስፈሪያ ዘይት+ ላይ የተወሰነውን በራሱ የግራ እጅ መዳፍ ላይ ያንቆረቁረዋል። 16  ከዚያም የቀኝ እጁን ጣት በግራ እጁ መዳፍ ላይ ባለው ዘይት ውስጥ ይነክራል፤ ከዘይቱም የተወሰነውን በይሖዋ ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጨዋል። 17  በእጁም መዳፍ ላይ ከቀረው ዘይት ላይ የተወሰነውን ወስዶ ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል፤ በበደል መባው ደም ላይ ደርቦ ይቀባዋል። 18  ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ የቀረውን ዘይት ራሱን በሚያነጻው ሰው ራስ ላይ ያፈሰዋል፤ ለሰውየውም በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል።+ 19  “ካህኑ ለኃጢአት መባ የሚሆነውን እንስሳ ይሠዋል፤+ ራሱን ከርኩሰቱ ለሚያነጻውም ሰው ያስተሰርይለታል፤ ከዚያም ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን እንስሳ ያርዳል። 20  ካህኑም የሚቃጠለውን መባና የእህሉን መባ+ በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፤ ለሰውየውም ያስተሰርይለታል፤+ እሱም ንጹሕ ይሆናል።+ 21  “ሆኖም ሰውየው ድሃ ከሆነና ይህን ለማቅረብ አቅሙ ካልፈቀደለት ለራሱ ማስተሰረያ እንዲሆንለት ለሚወዘወዝ መባ አንድ የበግ ጠቦት የበደል መባ አድርጎ ያመጣል፤ በተጨማሪም ለእህል መባ እንዲሆን በዘይት የተለወሰ አንድ አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄት፣ አንድ የሎግ መስፈሪያ ዘይት 22  እንዲሁም ከሁለት ዋኖሶች ወይም ከሁለት የርግብ ጫጩቶች አቅሙ የቻለውን ያቀርባል፤ አንደኛው ለኃጢአት መባ ሌላኛው ደግሞ ለሚቃጠል መባ ይሆናል።+ 23  መንጻቱን ለማረጋገጥም በስምንተኛው ቀን+ እነዚህን ይዞ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት ወዳለው ወደ ካህኑ ይመጣል።+ 24  “ካህኑም ለበደል መባ እንዲሆን የቀረበውን የበግ ጠቦትና+ አንዱን የሎግ መስፈሪያ ዘይት ይወስዳል፤ እነዚህንም የሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዘውዛቸዋል።+ 25  ከዚያም ለበደል መባ እንዲሆን የቀረበውን የበግ ጠቦት ያርዳል፤ ከበደል መባው ደም ላይ የተወሰነውን ወስዶ ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል።+ 26  ካህኑም ከዘይቱ የተወሰነውን በራሱ የግራ እጅ መዳፍ ላይ ያንቆረቁረዋል።+ 27  በግራ እጁ መዳፍ ላይ ካለው ዘይት የተወሰነውን በቀኝ እጁ ጣት በይሖዋ ፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 28  በእጁ መዳፍ ላይ ካለው ዘይት የተወሰነውን ወስዶ የበደል መባውን ደም በቀባበት ቦታ ላይ ማለትም ራሱን በሚያነጻው ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ በቀኝ እጁ አውራ ጣት እንዲሁም በቀኝ እግሩ አውራ ጣት ላይ ይቀባል። 29  ከዚያም በእጁ መዳፍ ላይ የቀረውን ዘይት ራሱን በሚያነጻው ሰው ራስ ላይ ያፈሰዋል፤ ይህን የሚያደርገው በይሖዋ ፊት እንዲያስተሰርይለት ነው። 30  “ካህኑም ሰውየው አቅሙ ፈቅዶ ካመጣቸው ዋኖሶች ወይም የርግብ ጫጩቶች መካከል አንዱን ያቀርባል፤+ 31  አቅሙ ፈቅዶ ካመጣቸውም መካከል አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ+ አድርጎ ከእህል መባው ጋር ያቀርባል፤ ካህኑም ራሱን ለሚያነጻው ሰው በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል።+ 32  “የሥጋ ደዌ የነበረበትን ሆኖም መንጻቱን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ አቅሙ የማይፈቅድለትን ሰው በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው።” 33  ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 34  “ርስት አድርጌ ወደምሰጣችሁ+ ወደ ከነአን ምድር+ በምትገቡበት ጊዜ በምድራችሁ ውስጥ የሚገኝን አንድ ቤት በደዌ ብበክለው+ 35  የቤቱ ባለቤት ወደ ካህኑ መጥቶ ‘አንድ የሚበክል ነገር ቤቴ ውስጥ ታይቷል’ በማለት ይንገረው። 36  ካህኑም ቤቱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ርኩስ ነው እንዳይል የሚበክለውን ነገር ለመመርመር ወደ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ በሙሉ እንዲያወጡ ትእዛዝ ይሰጣል፤ ከዚያም ካህኑ ቤቱን ለመመርመር ወደ ውስጥ ይገባል። 37  እሱም ብክለቱ የታየበትን ቦታ ይመረምራል፤ በቤቱም ግድግዳ ላይ ወደ ቢጫነት ያደላ አረንጓዴ ወይም ቀላ ያለ የተቦረቦረ ምልክት ቢታይና ይህም ከላይ ወደ ውስጥ ዘልቆ የገባ ከሆነ 38  ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ደጃፉ ወጥቶ ቤቱን ለሰባት ቀን ያሽገዋል።+ 39  “ከዚያም ካህኑ በሰባተኛው ቀን ተመልሶ በመምጣት ቤቱን ይመረምረዋል። ቤቱን የበከለው ነገር በግድግዳው ላይ ተስፋፍቶ ከሆነ 40  ካህኑ ትእዛዝ ይሰጣል፤ የተበከሉትም ድንጋዮች ተሰርስረው መውጣትና ከከተማዋ ውጭ ወዳለ ርኩስ የሆነ ስፍራ መጣል አለባቸው። 41  ከዚያም ቤቱ ከውስጥ በኩል በደንብ እንዲፈቀፈቅ ያደርጋል፤ ተፈቅፍቆ የተነሳው ልስንና ምርጊትም ከከተማዋ ውጭ በሚገኝ ርኩስ የሆነ ስፍራ ይደፋ። 42  ባወጧቸውም ድንጋዮች ቦታ ሌሎች ድንጋዮችን ያስገቡ፤ ቤቱም በአዲስ ምርጊት እንዲለሰን ያድርግ። 43  “ድንጋዮቹ ተሰርስረው ከወጡና ቤቱ ተፈቅፍቆ ዳግመኛ ከተለሰነ በኋላ ብክለቱ እንደገና ተመልሶ በቤቱ ላይ ከታየ 44  ካህኑ ገብቶ ይመረምረዋል። ብክለቱ በቤቱ ውስጥ ተስፋፍቶ ከሆነ ይህ በቤቱ ላይ የወጣ አደገኛ ደዌ+ ነው። ቤቱ ርኩስ ነው። 45  ቤቱ ይኸውም ድንጋዮቹ፣ እንጨቶቹ፣ ልስኑና ምርጊቱ እንዲፈርስ ያደርጋል፤ ከከተማዋ ውጭ በሚገኝ ርኩስ የሆነ ስፍራም እንዲጣል ያደርጋል።+ 46  ሆኖም ቤቱ ታሽጎ+ በነበረበት በየትኛውም ቀን ወደዚያ ቤት የገባ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤+ 47  እዚያ ቤት ውስጥ የተኛ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ እንዲሁም እዚያ ቤት ውስጥ የበላ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል። 48  “ይሁንና ካህኑ መጥቶ ሲያየው ቤቱ ከተለሰነ በኋላ ብክለቱ በቤቱ ውስጥ ካልተስፋፋ ቤቱ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል፤ ምክንያቱም ብክለቱ ጠፍቷል። 49  ቤቱንም ከርኩሰት* ለማንጻት ሁለት ወፎች፣ የአርዘ ሊባኖስ እንጨት፣ ደማቅ ቀይ ማግና ሂሶጵ ይወስዳል።+ 50  አንደኛዋንም ወፍ ከወራጅ ውኃ የተቀዳ ውኃ ባለበት የሸክላ ዕቃ ውስጥ ያርዳታል። 51  ከዚያም የአርዘ ሊባኖስ እንጨቱን፣ ሂሶጱን፣ ደማቁን ቀይ ማግና በሕይወት ያለችውን ወፍ ወስዶ በታረደችው ወፍ ደምና ከወራጅ ውኃ በተቀዳው ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፤ ወደ ቤቱም ሰባት ጊዜ ይርጨው።+ 52  ቤቱንም በወፏ ደም፣ ከወራጅ ውኃ በተቀዳው ውኃ፣ በሕይወት ባለችው ወፍ፣ በአርዘ ሊባኖስ እንጨቱ፣ በሂሶጱና በደማቁ ቀይ ማግ ከርኩሰት* ያነጻዋል። 53   በሕይወት ያለችውንም ወፍ ከከተማዋ ውጭ ወደ ሜዳ ይለቃታል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፤ ቤቱም ንጹሕ ይሆናል። 54  “ከማንኛውም ዓይነት የሥጋ ደዌ፣ በራስ ቆዳ ወይም በጢም ላይ ከሚወጣ ቁስል፣+ 55  በልብስ+ ወይም በቤት+ ላይ ከሚወጣ ደዌ፣ 56  ከእባጭ፣ ከእከክና ከቋቁቻ+ ጋር በተያያዘ 57   አንድ ነገር ርኩስ ወይም ንጹሕ መሆኑን ለመወሰን የሚያገለግለው ሕግ ይህ ነው።+ የሥጋ ደዌን በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ሦስት አሥረኛ ኢፍ 6.6 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሎግ 0.31 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ አሥረኛ ኢፍ 2.2 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ከኃጢአት።”
ቃል በቃል “ከኃጢአት።”