ዘሌዋውያን 15:1-33

  • ከብልት የሚወጣ የሚያረክስ ፈሳሽ (1-33)

15  ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦  “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብላችሁ ንገሯቸው፦ ‘አንድ ወንድ ከብልቱ* ፈሳሽ የሚወጣ ከሆነ ይህ ፈሳሽ ርኩስ ያደርገዋል።+  ሰውየው በፈሳሹ የተነሳ ርኩስ ነው፤ ፈሳሹ ከብልቱ እየፈሰሰ ቢሆንም ወይም ብልቱን ቢዘጋው ሰውየው ርኩስ ነው።  “‘ፈሳሽ የሚወጣው ሰው የተኛበት አልጋም ርኩስ ይሆናል፤ ይህ ሰው የተቀመጠበት ማንኛውም ነገርም ርኩስ ይሆናል።  የሰውየውን አልጋ የነካ ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+  እንዲሁም ፈሳሽ የሚወጣው ሰው ተቀምጦበት በነበረ ነገር ላይ የተቀመጠ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።  ፈሳሽ የሚወጣውን ሰው፣ ሰውነት የነካ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።  ፈሳሽ የሚወጣው ሰው ንጹሕ በሆነ ሰው ላይ ቢተፋ የተተፋበት ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።  ፈሳሽ የሚወጣው ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ርኩስ ይሆናል። 10  ይህ ሰው የተቀመጠበትን የትኛውንም ነገር የነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እነዚህን ነገሮች የያዘ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 11  ፈሳሽ የሚወጣው ሰው+ እጆቹን በውኃ ሳይታጠብ አንድን ሰው ቢነካ የተነካው ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 12  ፈሳሽ የሚወጣው ሰው የነካው የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ ማንኛውም የእንጨት ዕቃ ደግሞ በውኃ ይታጠብ።+ 13  “‘እንግዲህ ፈሳሹ ቢቆምና ሰውየው ከፈሳሹ ቢነጻ ንጹሕ ለመሆን ሰባት ቀን ይቁጠር፤ ልብሶቹን ይጠብ፤ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።+ 14  በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ይውሰድ፤+ እነዚህንም ይዞ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት በመቅረብ ለካህኑ ይስጥ። 15  ካህኑም አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቀርባቸዋል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሹ ለሰውየው በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል። 16  “‘አንድ ወንድ ዘር ቢፈሰው ገላውን በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 17  የፈሰሰው ዘር የነካውን ማንኛውንም ዓይነት ልብስ ወይም ቁርበት በውኃ ማጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 18  “‘አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ቢተኛና ዘሩ ቢፈስ ገላቸውን በውኃ መታጠብ አለባቸው፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናሉ።+ 19  “‘አንዲት ሴት ከሰውነቷ ደም ቢፈሳት በወር አበባዋ የተነሳ ርኩስ እንደሆነች ለሰባት ቀን ትቀጥላለች፤+ እንዲሁም እሷን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 20  በወር አበባዋ የተነሳ ርኩስ በሆነችባቸው ጊዜያት የተኛችበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል፤ እንዲሁም የተቀመጠችበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል።+ 21  አልጋዋን የነካ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 22  እሷ ተቀምጣበት የነበረውን የትኛውንም ነገር የነካ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 23  የተቀመጠችው አልጋ ላይም ይሁን ሌላ ነገር ላይ ሰውየው ያን መንካቱ እስከ ማታ ድረስ እንዲረክስ ያደርገዋል።+ 24  አንድ ወንድ ከእሷ ጋር ቢተኛና በወር አበባዋ ቢረክስ+ ሰውየው ለሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤ የተኛበት አልጋም ርኩስ ይሆናል። 25  “‘አንዲት ሴት የወር አበባዋ ከሚመጣበት ከተለመደው ጊዜ ውጭ ለብዙ ቀናት ደም ቢፈሳት+ ወይም በወር አበባዋ ወቅት ከወትሮው ረዘም ላለ ጊዜ ደም ቢፈሳት+ የወር አበባዋ በሚመጣባቸው ቀናት እንደሚሆነው ፈሳሽ በሚፈሳት ጊዜ ሁሉ ርኩስ ትሆናለች። 26  ፈሳሽ በሚፈሳት ቀናት ሁሉ የተኛችበት አልጋ በወር አበባዋ የተነሳ ርኩስ በሆነችባቸው ጊዜያት እንደተኛችበት አልጋ ይሆናል፤+ እንዲሁም የተቀመጠችበት ማንኛውም ነገር በወር አበባዋ ወቅት ርኩስ እንደሚሆን ሁሉ በዚህ ጊዜም ርኩስ ይሆናል። 27  እነዚህን ነገሮች የነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል፤ ልብሶቹንም ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 28  “‘ይሁን እንጂ ይፈሳት ከነበረው ፈሳሽ በምትነጻበት ጊዜ ለራሷ ሰባት ቀን ትቆጥራለች፤ ከዚያ በኋላ ንጹሕ ትሆናለች።+ 29  በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ትውሰድ፤+ እነዚህንም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወዳለው ወደ ካህኑ ታመጣቸዋለች።+ 30  ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ ለሚቃጠል መባ ያደርገዋል፤ ካህኑም የሚፈሳትን ርኩስ ፈሳሽ አስመልክቶ ለሴትየዋ በይሖዋ ፊት ያስተሰርይላታል።+ 31  “‘በመካከላቸው ያለውን የማደሪያ ድንኳኔን በማርከስ በርኩሰታቸው እንዳይሞቱ በዚህ መንገድ እስራኤላውያንን ከርኩሰታቸው ለዩአቸው።+ 32  “‘ፈሳሽ የሚወጣውን ወንድ፣ ዘሩ በመፍሰሱ የተነሳ ርኩስ የሆነውን ወንድ፣+ 33  በወር አበባዋ ላይ በመሆኗ ርኩስ የሆነችን ሴት፣+ ወንድም ሆነ ሴት ከሰውነቱ ፈሳሽ የሚወጣውን ማንኛውንም ሰው+ እንዲሁም ርኩስ ከሆነች ሴት ጋር የተኛን ወንድ በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው።’”

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ከሥጋው።”